ትንቢተ ኤርምያስ 51
51
በባቢሎን ላይ ተጨማሪ ቅጣት
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ በባቢሎን ላይና በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ የሚያቃጥልና የሚያጠፋ ነፋስን አስነሣለሁ። 2በባቢሎንም ላይ ተሳዳቢ ሰዎችን እሰድዳለሁ፤ እነርሱም ይሰድቧታል፤ ምድርዋንም ባዶ ያደርጋሉ፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ለባቢሎን ወዮላት” የሚል ይጨምራል። በመከራም ቀን በዙሪያዋ ይከብቡአታል። 3በቀስት ወርዋሪው ላይ፥ በጥሩርም በሚነሣው ላይ ቀስተኛው ቀስቱን ይገትር፤ ለጐበዛዝቷ አትዘኑ፤ ሠራዊቷንም ሁሉ አጥፉ። 4የተገደሉት በከለዳውያን ምድር ይወድቃሉ፤ የቈሰሉትም በውጭ ይወድቃሉ።
5“ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ላይ በተሠራው በደል የተሞላች ብትሆንም፥ እስራኤል መበለት አልሆነችም፤ ይሁዳም ከአምላኩ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ አልራቀም። 6ከባቢሎን መካከል ሽሹ፤ እያንዳንዳችሁም ነፍሳችሁን አድኑ፤ በበደልዋ አትጥፉ፤ የእግዚአብሔር በቀል ጊዜ ነውና፥ እርሱም ብድራቷን ይከፍላታልና። 7ባቢሎን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ምድርን ሁሉ ያሰከረች የወርቅ ጽዋ ነበረች፤ አሕዛብም ከጠጅዋ ጠጥተዋል፤ ስለዚህ አሕዛብ ተንገዳግደዋል። 8ባቢሎን በድንገት ወድቃ ተሰባብራለች፤ አልቅሱላት፤ ትፈወስም እንደ ሆነ ለቍስልዋ መድኀኒት ውሰዱላት። 9ባቢሎንን ፈወስናት፥ እርስዋ ግን አልተፈወሰችም፤ ፍርድዋ እስከ ሰማይ ደርሶአልና፥ እስከ ከዋክብትም ድረስ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ እንተዋት፤ ሁላችንም ወደ ሀገራችን እንሂድ። 10እግዚአብሔር ፍርዳችንን አውጥቶአል፤ ኑ በጽዮን የአምላካችን የእግዚአብሔርን ሥራ እንናገር።
11“ፍላጾችን አዘጋጁ፤ ጕራንጕሬዎችንም ሙሉ፤#ዕብ. “ጋሻዎችንም አዘጋጁ” ይላል። እግዚአብሔር ያጠፋት ዘንድ ቍጣው በባቢሎን ላይ ነውና የሜዶንን ንጉሥ መንፈስ አስነሥቶአል፤ የእግዚአብሔር በቀል የመቅደሱ በቀል#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የሕዝቡ በቀል” ይላል። ነውና። 12በባቢሎን ቅጥሮች ላይ ዓላማውን አንሡ፤ ከጕራንጕሬአችሁ ጋር ጽኑ፤ ተመልካቾችን አቁሙ፤ መሣሪያችሁን አዘጋጁ። እግዚአብሔር በባቢሎን በሚኖሩት ላይ የተናገረውን ያደርግ ዘንድ ጀምሮአልና። 13አንቺ በብዙ ውኃ አጠገብ የተቀመጥሽ፥ በመዝገብም የበለጠግሽ ሆይ! እንደ ስስትሽ መጠን ፍጻሜሽ ደርሶአል። 14የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራሱ ምሎአል፦ በእውነት ሰዎችን እንደ አንበጣ እሞላብሻለሁ፤ እነርሱም እየሮጡ ይወርዱብሻል።”
15ምድርን በኀይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ፥ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። 16ድምፁን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይታወካሉ፤ ከምድርም ዳር ደመናትን ያወጣል፤ ለዝናብም ጊዜ መብረቅን ያደርጋል፤ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል። 17ሰው ሁሉ ዕውቀትን አጥቶአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ሐሰተኞች ጣዖታትን ሠርተዋልና፥ እስትንፋስም የላቸውምና። 18ሥራቸው ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርም በጐበኛቸው ጊዜ ይጠፋሉ። 19የያዕቆብ ዕድል ፋንታ እንደ እነዚህ አይደለም፤ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና። እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው። ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
20“አንቺ የጦር መሣሪያን በተንሽብኝ፤ እኔም ሕዝቡን እበትንብሻለሁ፤ ከአንቺም ነገሥታትን አስወግዳለሁ። 21በአንቺ ፈረሱንና ፈረሰኛውን እበትናለሁ፤ በአንቺም ሰረገላውንና በላዩ የሚቀመጠውን እበትናለሁ። 22በአንቺም ወንድና ሴትን እበትናለሁ፤ በአንቺም ሽማግሌውንና ብላቴናውን እበትናለሁ፤#“በአንቺም ሽማግሌውንና ብላቴናውን እበትናለሁ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በአንቺም ጐልማሳውንና ቆንጆዪቱን እበትናለሁ፤ 23በአንቺም እረኛውንና መንጋውን እበትናለሁ፤ በአንቺም አራሹንና ጥማዱን እበትናለሁ፤ በአንቺም አለቆችንና መሳፍንትን እበትናለሁ። 24በጽዮን በዐይናችሁ ፊት ስለ ሠሩት ክፋታቸው ሁሉ በባቢሎንና በከለዳውያን ምድር የሚኖሩትን ሁሉ እበቀላለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
25“አንተ ምድርን ሁሉ የምታጠፋ አጥፊ ተራራ ሆይ! እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እጄንም እዘረጋብሃለሁ፤ ከድንጋዮቹም ላይ አንከባልልሃለሁ፤ የተቃጠለም ተራራ አደርግሃለሁ። 26ከአንተም ለማዕዘን የሚሆን ድንጋይንና ለመሠረት የሚሆን ድንጋይን አይወስዱም፤ ለዘለዓለምም አጠፋሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
27“በምድር ላይ ዓላማን አንሡ፤ በአሕዛብም መካከል መለከትን ንፉ፤ አሕዛብንም ለዩባት፤ የአራራትንና የሚኒን#“የሚኒን” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። የአስከናዝንም መንግሥታት እዘዙባት፤ ጦረኞችንም በላይዋ አቁሙ፤ ብዛታቸው እንደ አንበጣ የሆኑ ፈረሶችን በላይዋ አውጡ። 28አሕዛብንም፥ የሜዶንንም ነገሥታት፥ አለቆችንም፥ መሳፍንትንም ሁሉ፥ የግዛታቸውንም ምድር ሁሉ ለዩባት። 29ማንም እንዳይቀመጥባት የባቢሎንን ምድር ባድማ ያደርጋት ዘንድ የእግዚአብሔር ዐሳብ በባቢሎን ላይ ጸንቶአልና ምድር ተናወጠች፤ ታመመችም። 30የባቢሎን ተዋጊዎች መዋጋትን ትተዋል፤ በአምባዎቻቸውም ውስጥ ተቀምጠዋል፤ ኀይላቸውም ጠፍቶአል፤ እንደ ሴቶችም ሆነዋል፤ ማደሪያዎችዋም ነድደዋል፤ መወርወሪያዎችዋም ተሰብረዋል። 31ለባቢሎን ንጉሥ ይነግር ዘንድ ሯጩ ሯጩን ለመገናኘት፤ መልእክተኛውም መልእክተኛውን ለመገናኘት ይሮጣል፤ ከተማዋ ከዳር እስከ ዳር ተይዛለችና፤ 32መሻገሪያዎችዋም ተይዘዋልና፥ ቅጥርዋም በእሳት ተቃጥሎአልና፥ ሰልፈኞችም ተማርከዋልና።”
33የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “የባቢሎን ንጉሥ ቤት እንደ ተረገጠ አውድማ ናት፤ ጥቂት ቈይታ የመከር ጊዜ ይደርስባታል። 34የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላኝ፤ ከፋፈለኝም፤ እንደ ባዶ ዕቃም አደረገኝ፤ እንደ ዘንዶም ዋጠኝ፤ ከሚጣፍጠውም#ዕብ. “እኔንም ጣለኝ” የሚል ይጨምራል። ሥጋዬ ሆዱን ሞላ። 35በጽዮን የምትኖር በእኔ ላይ የተደረገ ግፍና ሥቃይ በባቢሎን ላይ ይሁን ትላለች፤ ኢየሩሳሌምም ደሜ በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ ይሁን ትላለች።” 36ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ የሚገፋሽን እፈርድበታለሁ፤ በቀልሽንም እበቀልልሻለሁ፤ ባሕርዋንም ድርቅ አደርገዋለሁ፤ ምንጭዋንም አደርቃለሁ። 37ባቢሎንም ባድማና የቀበሮ ማደሪያ፥ ማፍዋጫም ትሆናለች፤#“የቀበሮ ማደሪያ፥ ማፍዋጫም ትሆናለች” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። የሚቀመጥባትም ሰው አይገኝም። 38በአንድነትም እንደ አንበሶች ያገሣሉ፤ እንደ አንበሳም ደቦሎች ያጕረመርማሉ። 39በሞቃቸው ጊዜ እንዲዝሉ፥ የዘለዓለምም እንቅልፍ እንዲተኙ መጠጥን አጠጣቸዋለሁ፤ አሰክራቸዋለሁም፤ ከዚያም በኋላ አይነቁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 40እንደ ጠቦቶችና እንደ አውራ በጎች፥ እንደ አውራ ፍየሎችም ወደ መታረድ አወርዳቸዋለሁ።
41“የምድርም ሁሉ ክብር#ዕብ. “ሼሻክ” ይላል። እንዴት ተያዘች! እንዴትስ ተወሰደች! ባቢሎን በአሕዛብ መካከል እንዴት ለጥፋት ሆነች! 42ባሕር በባቢሎን ላይ ወጣ፤ በሞገዱም ብዛት ተከደነች። 43ከተሞችዋ ባድማና ደረቅ ምድር፥ ሰውም የማይቀመጥበት፥ የሰውም ልጅ የማያልፍበት ምድር ሆኑ። 44በባቢሎንም ላይ እበቀላለሁ፤#ዕብ “በባቢሎን ውስጥ ቤልን እቀጣለሁ” ይላል። የዋጠችውንም ከአፍዋ አስተፋታለሁ፤ አሕዛብም ከዚያ ወዲያ ወደ እርስዋ አይሰበሰቡም፤ የባቢሎንም ቅጥሮች ይወድቃሉ።
45“ሕዝቤ ሆይ! ከመካከልዋ ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ራሳችሁን አድኑ። 46በምድርም ከሚሰማ ወሬ የተነሣ አትፍሩ፤ ልባችሁም የዛለ አይሁን፤ በአንድ ዓመት ወሬ ይመጣል፤ ከዚያም በኋላ በሌላው ዓመት ወሬ ይመጣል፤ በምድርም ላይ ግፍ ይነግሣል፤ አለቃም በአለቃ ላይ ይነሣል። 47ስለዚህ እነሆ የተቀረጹትን የባቢሎንን ምስሎች የምበቀልበት ዘመን ይመጣል፤ ምድርዋም ሁሉ ትደርቃለች፤ ተዋግተውም የሞቱት ሁሉ በመካከልዋ ይወድቃሉ። 48አጥፊዎች ከሰሜን ይመጡባታልና ሰማይና ምድር፥ በእነርሱም ያለው ሁሉ ስለ ባቢሎን ደስ ይላቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር።#ምዕ. 51 ከቁ. 45 እስከ 48 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 49ባቢሎንም በእስራኤል ስለ ተገደሉት ትወድቃለች፤ ስለ ባቢሎንም በምድር ሁሉ የተገደሉት ይወድቃሉ።
50“ከሰይፍ ያመለጣችሁ ሆይ! ሂዱ፤ አትቁሙ፤ በሩቅ ያላችሁም እግዚአብሔርን አስቡ፤ ኢየሩሳሌምንም በልባችሁ አስቡ። 51ስድባችንን ስለ ሰማን አፍረናል፤ ባዕዳን ሰዎችም ወደ ቤተ መቅደሳችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብተዋልና ውርደት ፊታችንን ከድኖታል። 52ስለዚህ እነሆ የተቀረጹትን ምስሎችዋን የምበቀልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በምድርዋም ሁሉ የተገደሉት ይወድቃሉ። 53ባቢሎንም ወደ ሰማይ ብትወጣ፥ ቅፅሮችዋንም በኀይልዋ ብታጸና፥ ከእኔ ዘንድ አጥፊዎች ይመጡባታል፥ ይላል እግዚአብሔር።
54“ከባቢሎን የጩኸት ድምፅ፥ ከከለዳውያንም ምድር የታላቅ ጥፋት ድምፅ ተሰምቶአል። 55እግዚአብሔር ባቢሎንን አጥፍቶአታልና፥ ከእርስዋም ሞገዱ እንደ ብዙ ውኃዎች የሚተመውን ታላቁን ድምፅ ዝም አሰኝቶአልና፤ የድምፃቸው ጩኸት ተሰምቶአል። 56ጥፋት#ዕብ. “አጥፊው” ይላል። በባቢሎን ላይ መጥቶባታልና፥ ተዋጊዎችዋ ተያዙ፤ ቀስታቸውም ተሰባበረ፤ እግዚአብሔር ተበቅሎአቸዋልና፥ እግዚአብሔርም ፍዳን ከፍሎአቸዋልና። 57መሳፍንቶችዋንና ጥበበኞችዋንም፥ አለቆችዋንና ሹሞችዋን፥ ኀያላኖችዋንም አሰክራለሁ፤ ለዘለዓለምም አንቀላፍተው አይነቁም#“ለዘለዓለምም አንቀላፍተው አይነቁም” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ይላል ስሙ ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር የተባለው ንጉሥ። 58የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰፊው የባቢሎን ቅጥር ፈጽሞ ይፈርሳል፤ ረጃጅሞች በሮችዋም በእሳት ይቃጠላሉ፤ ሕዝቡ ለከንቱ ይደክማሉ፤ አሕዛብም በመጀመሪያ በእሳት ያልቃሉ።”
ነቢዩ ኤርምያስ ወደ ባቢሎን መልእክት እንደ ላከ
59የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ከእርሱ ዘንድ ወደ ባቢሎን በሄደ ጊዜ ለማሴው ልጅ ለኔርዩ ልጅ ለሠራያ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘው ቃል ይህ ነው። 60ሠራያም የቤቱ አዛዥ ነበረ፤ በባቢሎንም ላይ የሚመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ፥ ስለ ባቢሎን የተጻፈውን ይህን ቃል ሁሉ ኤርምያስ በአንድ መጽሐፍ ላይ ጻፈው። 61ኤርምያስም ሠራያን እንዲህ አለው፥ “ወደ ባቢሎን በገባህ ጊዜ እይ፤ ይህንም ቃል ሁሉ አንብብና፦ 62አቤቱ! ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ማንም እንዳይቀመጥባት፥ ለዘለዓለምም ባድማ እንድትሆን ታጠፋት ዘንድ በዚች ስፍራ ላይ ተናግረሃል በል። 63ይህንም መጽሐፍ ማንበብ ከፈጸምህ በኋላ፥ ድንጋይን እሰርበት፤ በኤፍራጥስም ወንዝ ውስጥ ጣለው። 64አንተም፦ እኔ ከማመጣባት ክፉ ነገር የተነሣ እንዲሁ ባቢሎን ትሰጥማለች፤ አትነሣምም በል።”
የኤርምያስ ቃል እስከዚህ ድረስ ነው።#ምዕ. 51 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 28 ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 51: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ