ትንቢተ ኤርምያስ 20
20
ጳስኮር ነቢዩ ኤርምያስን እንደ ተጣላው
1በእግዚአብሔርም ቤት የተሾመው አለቃ የካህኑ የኢሜር ልጅ ጳስኮር ኤርምያስ በዚህ ነገር ትንቢት ሲናገር ሰማ። 2ጳስኮርም ነቢዩን ኤርምያስን ገረፈው፤ በእግዚአብሔርም ቤት በነበረው በላይኛው በብንያም በር ባለው አዘቅት ውስጥ ጣለው።
3በነጋውም ጳስኮር ኤርምያስን ከአዘቅት ውስጥ አወጣው። ኤርምያስም እንዲህ አለው፥ “እግዚአብሔር ስምህን፦ ዘዋሪ ስደተኛ እንጂ ጳስኮር ብሎ አይጠራህም። 4እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ አንተን ከወዳጆችህ ሁሉ ጋር አፈልስሃለሁ፤ እነርሱም በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ፤ ዐይኖችህም ያያሉ፤ አንተንና ይሁዳንም ሁሉ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም ወደ ባቢሎን ያፈልሳቸዋል፤ በሰይፍም ይገድላቸዋል። 5የዚችንም ከተማ ኀይል ሁሉ፥ ጥሪቷንም ሁሉ፥ ክብርዋንም ሁሉ፥ የይሁዳንም ነገሥታት መዝገብ ሁሉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱ ይበዘብዙአቸዋል፤ ይዘውም ወደ ባቢሎን ያስገቡአቸዋል። 6አንተም ጳስኮር ሆይ! በቤትህም የሚኖሩት ሁሉ ተማርካችሁ ትሄዳላችሁ፤ አንተም በሐሰት ትንቢት የተናገርህላቸው ወዳጆችህ ሁሉ ወደ ባቢሎን ትገባላችሁ፤ በዚያም ትሞታላችሁ፤ በዚያም ትቀበራላችሁ።”
ኤርምያስ ኀዘኑን እንደ ገለጠ
7አቤቱ! አታለልኸኝ፤ እኔም ተታለልሁ፤#ግእዝ “ቀሰፍከኒ ወተቀሰፍኩ” ይላል። ከእኔም በረታህ አሸነፍህም፤ ቀኑን ሁሉ መሳቂያ ሆኛለሁ፤ ሁሉም ያፌዙብኛል። 8በተናገርሁ ቍጥር እጮኻለሁ፤ ግፍና ጥፋት ብዬ እጠራለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ቀኑን ሁሉ ስድብና ዋዛ ሆኖብኛልና። 9እኔም እንዲህ አልሁ፥ “የእግዚአብሔርን ስም አላነሣም፤ ከእንግዲህ ወዲህ በስሙ አልናገርም፥” በአጥንቶች ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት ያለ በልቤ ሆነብኝ፤ ደከምሁ፤ መሸከምም አልቻልሁም። 10በእኔ ላይ የተሰበሰቡና የከበቡኝን የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁ፤ መውደቄን የሚጠብቁ የሰላሜ ሰዎች ሁሉ፥ “ምናልባት ይታለል እንደ ሆነ፥ እናሸንፈውም እንደ ሆነ፥ እርሱንም እንበቀል እንደ ሆነ፥ ተነሡ እኛም እንነሣለን” ይላሉ።
11እግዚአብሔር ግን እንደ ኀያል ተዋጊ ከእኔ ጋር ነው፤ ስለዚህ አሳዳጆች ይሰናከላሉ፤ አያሸንፉም፤ ለዘለዓለምም የማይረሳ ጕስቍልናቸውን አላወቁምና ፈጽመው አፈሩ። 12አቤቱ! ጽድቅን የምትፈትን ኵላሊትንና ልብን የምትመረምር የሠራዊት ጌታ ሆይ! ክርክሬን ገልጬልሃለሁና ፍረድልኝ። 13ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ አመስግኑትም፤ የችግረኛውን ነፍስ ከክፉ አድራጊዎች እጅ አድኖአልና።
14የተወለድሁባት ቀን፥ እናቴ እኔን የወለደችባት ቀን የተረገመች ትሁን፤ የተባረከችም አትሁን። 15ወንድ ልጅ ተወልዶልሃል ብሎ ለአባቴ የምሥራች ነግሮ ደስ ያሰኘው ሰው የተረገመ ይሁን። 16ያም ሰው እግዚአብሔር በቍጣው እንደ ገለበጣቸው፥ ይቅርም እንደ አላላቸው ከተሞች ይሁን፥ በማለዳም ልቅሶን፥ በቀትርም ጩኸትን ይስማ፤ 17እናቴ መቃብር ትሆነኝ ዘንድ፥ ማኅፀንዋም ዘወትር ይዞኝ ያቈይ ዘንድ በማኅፀን ውስጥ አልገደለኝምና። 18ድካምንና ጣርን አይ ዘንድ፥ ዘመኔም በእፍረት ታልቅ ዘንድ ስለ ምን ከማኅፀን ወጣሁ?
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 20: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ