ትንቢተ ኤርምያስ 2
2
የእስራኤል አባቶች በደል
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“ሂድ፤ እንዲህ ብለህ በኢየሩሳሌም ጆሮ ተናገር፤#“ሂድ በኢየሩሳሌም ጆሮ ተናገር” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የብላቴንነትሽን ምሕረት፥ የታጨሽበትንም ፍቅር፥ በምድረ በዳ ዘር ባልተዘራበት ምድር#“በምድረ በዳ ዘር ባልተዘራበት ምድር” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። እንደ ተከተልሽኝ አስቤአለሁ። 3እስራኤል ለእግዚአብሔር ቅዱስ ነበረ፤ የቡቃያው በኵራትም ነበረ፤ የበሉት እንደ በደለኞች ይቈጠራሉ፤ ክፉም ነገር ያገኛቸዋል፤ ይላል እግዚአብሔር።”
4የያዕቆብ ቤት የእስራኤልም ቤት ወገኖች ሁሉ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “አባቶቻችሁ ከእኔ ዘንድ የራቁ፥ ከንቱነትንም የተከተሉ፥ ከንቱም የሆኑ ምን ክፋት አግኝተውብኝ ነው? 6እነርሱም፥ “ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በምድረ በዳና በባድማ፥ ዕንጨትና ውኃ፥ የእንጨት ፍሬም በሌለበት ምድር፥ ሰው በማያልፍበትና የሰው ልጅም በማይቀመጥበት ምድር የመራን እግዚአብሔር ወዴት አለ? አላሉም። 7ፍሬዋንና በረከቷንም ትበሉ ዘንድ ወደ ቀርሜሎስ አገባኋችሁ፤ ነገር ግን በገባችሁ ጊዜ ምድሬን አረከሳችሁ፤ ርስቴንም አጐሳቈላችሁ። 8ካህናቱም፦ እግዚአብሔር ወዴት አለ? አላሉም፤ ሕጌን የተማሩትም አላወቁኝም፤ ጠባቂዎችም ዐመፁብኝ፤ ነቢያትም በበዐል ትንቢት ተናገሩ፤ የማይጠቅማቸውንም ነገር ተከተሉ።
እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ ወቀሰ
9“ስለዚህ እንደ ገና ከእናንተ ጋር እከራከራለሁ፤ ከልጆቻችሁም ልጆች ጋር እከራከራለሁ። 10ወደ ኬቲም ደሴቶች እለፉና ተመልከቱ፤ ወደ ቄዳርም ላኩና እጅግ መርምሩ፤ እንደዚህም ያለ ነገር ሆኖ እንደ ሆነ እዩ። 11አሕዛብ አማልክት ያልሆኑ አማልክቶቻቸውን ይለውጡ አንደ ሆነ እዩ፤ ነገር ግን ሕዝቤ ክብራቸውን ለማይረባ ነገር ለወጡ። 12ሰማይ በዚህ ደነገጠ፤ እጅግም ተንቀጠቀጠ” ይላል እግዚአብሔር። 13ሕዝቤ ሁለት ክፉ ነገሮችን አድርገዋልና፤ የሕይወት ውኃ ምንጭ እኔን ትተውኛል፥ የተነደሉትን ውኃውንም ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጕድጓዶች ለራሳቸው ቈፍረዋል።
14“በውኑ እስራኤል ባሪያ ነውን? ወይስ የቤት ውላጅ ነውን? ስለ ምን ምርኮ ሆነ? 15የአንበሳ ደቦሎች በእርሱ ላይ አገሡ፤ በእርሱም ላይ ደነፉ፤ ምድሩንም ባድማ አደረጉ፤ ከተሞቹንም አፈረሱ፤ የሚቀመጥባቸውም የለም። 16የሜምፎስና የጣፍናስ ልጆች አስነወሩሽ፤ አላገጡብሽም። 17ይህን ሁሉ ያመጣብሽ እኔን መርሳትሽ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር አምላክሽ። 18አሁንስ የግዮንን ውኃ ትጠጪ ዘንድ በግብፅ መንገድ ምን ጉዳይ አለሽ? የወንዞችንም ውኃ ትጠጪ ዘንድ በአሦር መንገድ ምን ጉዳይ አለሽ? 19ክፋትሽ ይገሥጽሻል፤ ክዳትሽም ይዘልፍሻል፤ እኔን መተውሽም ክፉና መራራ ነገር መሆኑን ታውቂያለሽ፤ ትረጂማለሽ” ይላል አምላክሽ እግዚአብሔር፤ “መፈራቴም በአንቺ ዘንድ የለም፤ ይህም ደስ አላሰኘኝም” ይላል አምላክሽ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
እግዚአብሔርን ለማምለክ የእስራኤል እንቢታ
20ከጥንት ጀምሬ ቀንበርሽን ሰብሬአለሁ፤ እስራትሽንም ቈርጫለሁ፤ አንቺም፦ አላገለግልም አልሽ፤ ነገር ግን ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ፤ ከለምለምም ዛፍ ሁሉ በታች ለማመንዘር ተጋደምሽ። 21እኔ የተመረጠች ወይን፥ ፍጹምም እውነተኛ ዘር አድርጌ ተክዬሽ ነበር፤ አንቺ ግን ተለውጠሽ እንዴት መራራ የእንግዳ ወይን ግንድ ሆንሽ? 22በእንዶድ ብትታጠቢም፥ ለራስሽም ሳሙና ብታበዢ፥ በእኔ ፊት በኀጢአትሽ ረክሰሻል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 23አንቺስ፦ አልረከስሁም፤ በዓሊምንም አልተከተልሁም፤ እንዴት ትያለሽ? በሸለቆ ያለውን መንገድሽን ተመልከቺ፤ ያደረግሽውንም ዕወቂ። ማታ ማታ በመንገዶች ትጮኻለች፤ 24በምድረ በዳ ባሉ ውኃዎች ተዘረጋች፤ በሰውነቷም ምኞት ትወሰዳለች፤ ይይዟታል፤ የሚመልሳት ግን የለም፤#ዕብ. “በምኞቷ ነፋስን እንደምታሸትት በምድረ በዳ እንደ ለመደች እንደ ሜዳ አህያ ነሽ ፤ ከምኞቷ የሚመልሳት ማን ነው” ይላል። የሚሹአትም አይደክሙም፤ በተዋረደችበትም ጊዜ ያገኙአታል። 25እግርሽን ከሰንከልካላ መንገድ፥ ጕሮሮሽንም ከውኃ ጥም ከልክዪ፤ እርስዋ ግን፥ “እጨክናለሁ፤ እንግዶችንም ወድጄአለሁ” ብላ ተከተለቻቸው።
የእስራኤል ቅጣት
26ሌባ በተያዘ ጊዜ እንደሚያፍር፤ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች፥ እነርሱና ንጉሦቻቸውም፥ አለቆቻቸውም፥ ካህናቶቻቸውም፥ ነቢያቶቻቸውም ያፍራሉ። 27ግንዱን፥ “አንተ አባቴ ነህ፤ ድንጋዩንም፦ አንተ ወለድኸኝ” ይላሉ፤ ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡኝ፤ በመከራቸው ጊዜ ግን፥ “ተነሥተህ አድነን ይላሉ። 28ለአንተ የሠራሃቸው አማልክትህ ግን ወዴት ናቸው? ይሁዳ ሆይ፥ አማልክትህ እንደ ከተሞችህ ቍጥር እንዲሁ ናቸውና ይነሡ፤ በመከራህም ጊዜ ያድኑህ። በኢየሩሳሌምም በመንገዶችዋ ቍጥር ለጣዖት ሠዉ።
29“ከእኔ ጋር ለምን ትከራከራላችሁ? ሁላችሁ ክዳችሁኛል፤ ሁላችሁም ዐምፃችሁብኛል” ይላል እግዚአብሔር። 30ልጆቻችሁን በከንቱ ቀሥፌአቸዋለሁ፤ ተግሣጼን አልተቀበላችሁም፤ ሰይፋችሁ እንደሚሰብር አንበሳ ነቢያቶቻችሁን በልቶአል፤ በዚህም አልፈራችሁኝም። 31የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። በውኑ ለእስራኤል ምድረ በዳ ወይስ የጨለመች ምድር ሆንሁበትን? ሕዝቤስ ስለ ምን፦ እኛ አንገዛልህም፤ ከእንግዲህም ወዲህ ወደ አንተ አንመለስም ይላል? 32በውኑ ሙሽራ ጌጥዋን ወይስ ድንግል ዝርግፍ ጌጥዋን ትረሳለችን? ሕዝቤ ግን ለማይቈጠር ወራት ረስቶኛል። 33ፍቅርን ለመሻት እንግዲህ በመንገድሽ የምትፈልጊው መልካም ምንድን ነው? እንዲህ አይደለም፤ መንገድሽን ታረክሺ ዘንድ ዳግመኛ በደልሽ። 34በእጆችሽም የንጹሓን ድሆች ደም ተገኝቶአል፤ በዛፍ ሁሉ ላይ በግልጥ አገኘሁት እንጂ በጕድጓድ ፈልጌ አላገኘሁትም። 35አንቺ ግን፦ ንጹሕ ነኝ፤ በእውነት ቍጣው ከእኔ ይመለስ አልሽ። እነሆ ኀጢአት አልሠራሁም ብለሻልና እፋረድሻለሁ። 36መንገድሽን እጥፍ ታደርጊ ዘንድ ለምን እጅግ ትሮጫለሽ? በአሦር እንዳፈርሽ በግብፅም ታፍሪያለሽ። 37እግዚአብሔርም ተስፋሽን አስቈርጦሻልና፥ በእርሱም አይከናወንልሽምና እጅሽን በራስሽ ላይ አድርገሽ ከዚያ ደግሞ ትወጫለሽ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 2: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ