የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ “በእናትህ ሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፤ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ።” እኔም፥ “ወዮልኝ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ ሕፃን ነኝና እናገር ዘንድ አልችልም” አልሁ። እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፥ “ወደምልክህ ሁሉ ዘንድ ትሄዳለህና፥ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና፦ ሕፃን ነኝ አትበል። እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋራ ነኝና ከፊታቸው የተነሣ አትፍራ” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፥ እግዚአብሔርም አለኝ፥ “እነሆ፥ ቃሌን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ፤ እነሆ ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል ዘንድ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ ሾሜሃለሁ።” ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል፥ “ኤርምያስ ሆይ! ምን ታያለህ?” እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም፥ “የሎሚ በትር አያለሁ” አልሁ። እግዚአብሔርም፥ “የተናገርሁትን እፈጽመው ዘንድ እተጋለሁና መልካም አይተሃል” አለኝ። ሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ምን ታያለህ?” እኔም፥ “የሚፈላ አፍላል አያለሁ፤ ፊቱም ወደ ሰሜን ወገን ነው” አልሁ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ከሰሜን ወገን ክፉ ነገር በምድሪቱ በተቀመጡ ሁሉ ላይ ይፈስሳል። እነሆ እኔ በሰሜን ያሉትን የመንግሥታቱን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እነርሱም ይመጣሉ እያንዳንዳቸውም በኢየሩሳሌም በር መግቢያ በዙሪያዋና በቅጥርዋ ሁሉ ላይ፥ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ላይ ዙፋናቸውን ያስቀምጣሉ። ስለ ክፋታቸውም ሁሉ፥ እኔን ስለ ተዉ፥ ለሌሎችም አማልክት ስለ ሠዉ፥ ለእጃቸውም ሥራ ስለ ሰገዱ፥ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፤ ተነሥም፤ ያዘዝሁህንም ሁሉ ንገራቸው፤ ከፊታቸውም የተነሣ አትፍራ። በፊታቸውም አትደንግጥ አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ይላል እግዚአብሔር። እነሆ በምድሪቱ ሁሉ ላይ፥ በይሁዳም ነገሥታት በአለቆችዋና በካህናቷ ላይ፥ በምድሪቱም ሕዝብ ላይ እንደ ተመሸገች ከተማ፥ እንደ ብረትም ዓምድ፥ እንደ ናስም ቅጥር ዛሬ አድርጌሃለሁ። ከአንተ ጋር ይዋጋሉ፤ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ድል አይነሡህም፥” ይላል እግዚአብሔር።
ትንቢተ ኤርምያስ 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 1:4-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች