ጻድቅ ሰው እንደጠፋ አያችሁ፤ ይህንም በልባችሁ አላሰባችሁም፤ ጻድቃን ሰዎች ይወገዳሉ፤ ጻድቅም ከክፋት ፊት እንደ ተወገደ ማንም አያስተውልም። መቃብሩ በሰላም ይሆናል፤ ከመካከልም ይወሰዳል። እናንተ የኃጥኣን ልጆች፥ የዘማውያንና የጋለሞታዪቱ ዘር፥ ወደዚህ ቅረቡ። በማን ታላግጣላችሁ? በማንስ ላይ አፋችሁን ታላቅቃላችሁ? ምላሳችሁንስ በማን ላይ ታስረዝማላችሁ? እናንተ በለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች በጣዖት ደስ የምትሰኙ፥ እናንተም በሸለቆች ውስጥ በዓለትም ስንጣቂዎች በታች ልጆቻችሁን የምትሠዉ፥ እናንተ የጥፋት ልጆችና የዐመፀኞች ዘሮች አይደላችሁምን? በሸለቆ ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች ዕድል ፋንታሽ ናቸው፤ እነርሱም ዕጣሽ ናቸው፤ ለእነርሱም የመጠጥ ቍርባን አፍስሰሻል፤ የእህልንም ቍርባን አቅርበሻል። እንግዲህ በዚህ ነገር አልቈጣምን? ከፍ ባለውና በረዘመውም ተራራ ላይ መኝታሽን አደረግሽ፤ በዚያም መሥዋዕትሽን ሠዋሽ። ከመዝጊያው በኋላ መታሰቢያሽን አደረግሽ፤ እኔን ብትተዪ የሚጠቅምሽ መሰለሽን? ከእኔም ይልቅ ከአንቺ ጋራ የሚተኙትን መረጥሽ። ዝሙትሽን ከእነርሱ ጋር አበዛሽ፤ ከአንቺ የራቁ ብዙዎችንም ተጐዳኘሽ። መልእክተኞችሽንም ወደ ሩቅ ላክሽ፤ ከእነርሱም ጋር ተወገድሽ፤ እስከ ሲኦልም ድረስ ተዋረድሽ። በመንገድሽም ብዛት ደከምሽ፤ ዳግመኛም ጕልበት እያለኝ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን መንገድ አልተውም አላልሽም፤ ይህንም ስላደረግሽ አላፈርሽም። ሐሰት የተናገርሽው፥ እኔንም ያላሰብሽው፥ በልብሽም ነገሩን ያላኖርሽው ማንን ሰግተሽ ነው? ማንንስ ፈርተሽ ነው? እኔም ዝም አልሁሽ፤ አንቺም አልፈራሽኝም። እንግዲህ እኔ ጽድቄንና የማይረባሽን የአንቺን በደል እናገራለሁ። በችግርሽ ቀን በጮኽሽ ጊዜ እስኪ ይታደጉሽ፤ እነሆ፥ ዐውሎ ይወስዳቸዋል፤ ነፋስም ሁሉን ያስወግዳቸዋል። ወደ እኔ የሚጠጉ ግን ምድሪቱን ይገዛሉ፤ የተቀደሰውን ተራራዬንም ይወርሳሉ። እርሱም፥ “በፊቱ፥ መንገድን ጥረጉ፤ ከሕዝቤም መንገድ ዕንቅፋትን አስወግዱ” ይላል። ለዘለዓለም በአርያም የሚኖር ስሙም ቅዱሰ ቅዱሳን የሆነ፥ በቅዱሳን አድሮ የሚኖር፥ ለተዋረዱት ትዕግሥትን የሚሰጥ፥ ልባቸውም ለተቀጠቀጠ ሕይወትን የሚሰጥ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “መንፈስ ከእኔ ይወጣልና፥ የሁሉንም ነፍስ ፈጥሬአለሁና ለዘለዓለም አልቀስፋችሁም፤ ሁልጊዜም አልቈጣችሁም። ስለ ኀጢአቱ ጥቂት ጊዜ መከራ አመጣሁበት፤ ቀሠፍሁትም፤ ፊቴንም ከእርሱ መለስሁ፤ እርሱም አዘነ። እያዘነም ሄደ። ከዚህም በኋላ መንገዱን አይቻለሁ፤ ፈወስሁትም፤ አጽናናሁት፤ እውነተኛ ደስታንም ሰጠሁት። በሩቅም በቅርብም ላሉ በሰላም ላይ ሰላም ይሁን፤ እፈውሳቸውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። “ኃጥኣን ግን እንዲህ ይገለበጣሉ፤ ዕረፍትንም አያገኙም። ለኃጥአን ደስታ የላቸውም” ይላል እግዚአብሔር።
ትንቢተ ኢሳይያስ 57 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 57:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች