ጻድቅ ይሞታል፤ ይህን ግን ማንም ልብ አይልም፤ ለእግዚአብሔር ያደሩ ሰዎች ይወሰዳሉ፤ ጻድቃን ከክፉ ይድኑ ዘንድ፣ መወሰዳቸውን፣ ማንም አያስተውልም። በቅንነት የሚሄዱ፣ ሰላም ይሆንላቸዋል፤ መኝታቸው ላይ ያርፋሉ። “እናንተ የአስማተኛዪቱ ልጆች ግን፣ እናንተ የአመንዝራውና የጋለሞታዪቱ ዘር፤ እናንተ፣ ወዲህ ኑ! የምትሣለቁት በማን ላይ ነው? የምታሽሟጥጡት ማንን ነው? ምላሳችሁንስ አውጥታችሁ የምታሾፉት በማን ላይ ነው? እናንተ የዐመፀኞች ልጆች፣ የሐሰተኞች ዘር አይደላችሁምን? በባሉጥ ዛፎች መካከል፣ ቅጠሉ በተንዠረገገ ዛፍ ሥር በዝሙት የምትቃጠሉ፣ በሸለቆዎች፣ በዐለት ስንጣቂዎችም ውስጥ ልጆቻችሁን የምትሠዉ አይደላችሁምን? በሸለቆው በሚገኙት ለስላሳ ድንጋዮች ውስጥ ያሉት ጣዖቶች የአንቺ ናቸው፤ እነርሱም ዕጣ ፈንታዎችሽ ናቸው፤ ርግጥ ነው፣ በእነርሱ ላይ የመጠጥ ቍርባን አፍስሰሻል፤ የእህል ቍርባንም አቅርበሻል፤ ታዲያ፣ ስለ እነዚህ ነገሮች ዝም እላለሁን? ዐልጋሽን ከፍ ባለውና በረጅሙ ኰረብታ ላይ አነጠፍሽ፤ በዚያም መሥዋዕትሽን ልታቀርቢ ወጣሽ። ከመዝጊያሽና ከመቃንሽ ጀርባ፣ የጣዖት ምስሎችሽን ሰቀልሽ፤ እኔን ትተሽ መኝታሽን ገላለጥሽ፤ በላይም ወጥተሽ በጣም ገለጥሽው፤ መኝታቸውን ከወደድሽላቸው ጋራ ስምምነት አደረግሽ፤ ዕርቃናቸውንም አየሽ። የወይራ ዘይት ይዘሽ፣ ሽቱ በላዩ ጨምረሽ ወደ ሞሎክ ሄድሽ፤ መልእክተኞችሽን ወደ ሩቅ አገር ላክሽ፤ እስከ ራሱ እስከ ሲኦልም ዘለቅሽ! በመንገድ ብዛት ደከምሽ፤ ነገር ግን ‘ተስፋ የለውም’ አላልሽም፤ የጕልበት መታደስ አገኘሽ፤ ስለዚህም አልዛልሽም። “እኔን የዋሸሽኝ፤ ማንን ፈርተሽ፣ ማንንስ ሠግተሽ ነው? እኔን ያላስታወስሽው፣ ይህንም በልብሽ ያላኖርሽው፣ እኔን ያልፈራሽው፣ ዝም ስላልሁ አይደለምን? ጽድቅሽንና ሥራሽን አጋልጣለሁ፤ እነርሱም አይጠቅሙሽም። ለርዳታ በምትጮኺበት ጊዜ፣ የሰበሰብሻቸው ጣዖቶች እስኪ ያድኑሽ! ነፋስ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ ሽውሽውታም ይበትናቸዋል። እኔን መጠጊያው ያደረገ ሰው ግን፣ ምድሪቱን ይወርሳል፤ የተቀደሰ ተራራዬንም ገንዘቡ ያደርገዋል።” እንዲህ ይባላል፤ “አብጁ፤ አብጁ፤ መንገድ አዘጋጁ! ከሕዝቤ መንገድ ዕንቅፋት አስወግዱ።” ከፍ ከፍ ያለውና ልዕልና ያለው እርሱ፣ ስሙም ቅዱስ የሆነው፣ ለዘላለም የሚኖረው እንዲህ ይላል፤ “የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት፣ ከፍ ባለውና በቅዱሱ ስፍራ እኖራለሁ፤ የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋራ እሆናለሁ። የሰው መንፈስ በፊቴ እንዳይዝል፣ የፈጠርሁትም ሰው እስትንፋስ እንዳይቆም፣ ለዘላለም አልወቅሥም፤ ሁልጊዜም አልቈጣም። ኀጢአት ስለ ሞላበት ስግብግብነቱ ተቈጣሁት፤ ቀጣሁት፤ ፊቴንም በቍጣ ከርሱ ሸሸግሁ፤ ያም ሆኖ በገዛ መንገዱ ገፋበት። መንገዶቹን አይቻለሁ፤ ቢሆንም እፈውሰዋለሁ፤ እመራዋለሁ፤ ለርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱትም መጽናናትን እመልሳለሁ፤ በእስራኤል አልቃሾች ከንፈር ላይ ምስጋና እፈጥራለሁ። በቅርብና በሩቅ ላሉት ሰላም፣ ሰላም ይሁን፤ እኔ እፈውሳቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር። ክፉዎች ግን ማዕበሉ ጭቃና ጕድፍ እንደሚያወጣ፣ ጸጥ ማለት እንደማይችል፣ እንደሚናወጥ ባሕር ናቸው። አምላኬ፣ “ለክፉዎች ሰላም የላቸውም” ይላል።
ኢሳይያስ 57 ያንብቡ
ያዳምጡ ኢሳይያስ 57
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኢሳይያስ 57:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች