ትንቢተ ኢሳይያስ 46
46
የባቢሎን አማልክት
1ቤል ወደቀ፤ ዳጎን ተሰባበረ፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የተቀረጹ ጣዖቶቻቸው በእንስሳና በከብት ላይ ተጭነዋል እንደ ደካማ ሸክም አስራችሁ ውሰዱአቸው” ይላል። ምስሎቻቸውም እንደ ትቢያ ሆኑ፤ አራዊትና እንስሳም ይረግጡአቸዋል፤ እንደ ፋንድያም ሸክም የሚያጸይፉ ናቸውና አያነሡአቸውም። 2ደካሞች ናቸው፤ ኀይልም የላቸውም፤ ከጦርነትም ራሳቸውን ለማዳን አልቻሉም፤ ራሳቸው ግን ተማረኩ።
3እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ የእስራኤልም ቤት ቅሬታ ሁሉ፥ ከማኅፀንም ጀምሮ የተሸከምኋችሁ፥ ከሕፃንነትም ጀምሮ ያስተማርኋችሁ፥ ስሙኝ። 4እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፤ እስከ ሽበትም ድረስ እኔ ነኝ፤ እኔ እታገሣችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻለሁ፤ እኔም ይቅር እላለሁ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ፤ እኔም አድናችኋለሁ። 5እንግዲህ በማን ትመስሉኛላችሁ? የምትሳሳቱ እናንተ ሁላችሁ፥ እዩ፤ አስተውሉም። 6ወርቁንና ብሩን ከኮሮጆ የሚያወጡና በሚዛን የሚመዝኑ እነርሱ አንጥረኛውን ይቀጥራሉ፤ እርሱም ጣዖት አድርጎ ይሠራዋል፤ ለዚያም ይጐነበሱለታል፤ ይሰግዱለትማል። 7በጫንቃቸው ላይ ተሸክመውት ይሄዳሉ፤ በስፍራውም በአኖሩት ጊዜ በዚያ ይቆማል፤ ከስፍራውም ፈቀቅ አይልም፤ ሰውም ወደ እርሱ ቢጮህ አይሰማውም፤ ከክፉም አያድነውም።
8ይህን ዐስቡና አልቅሱ፤ የተሳሳታችሁ ሆይ፥ ንስሓ ግቡ፤ ልባችሁንም መልሱ። 9እኔ አምላክ ነኝና፤ ያለ እኔም ሌላ የለምና የቀድሞውንና የጥንቱን ነገር ዐስቡ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። 10በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እናገራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች፤ የመከርሁትንም ሁሉ አደርጋለሁ እላለሁ። 11ከምሥራቅና ከሩቅ ሀገር ስለ መከርሁት ምክር ዎፍን እጠራለሁ፤ ተናገርሁ፤ አመጣሁም፤ ፈጠርሁ፤ አደረግሁም፤ አመጣሁት፤ መንገዱንም አቀናሁለት።
12እናንተ ከጽድቅ የራቃችሁ ልበ ጥፉዎች፥ ስሙኝ፤ 13ጽድቄን አመጣኋት፤ ከእኔ ዘንድ የምትገኝ መድኀኒትንም አላዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኀኒትን ለእስራኤል ሰጥቻለሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 46: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ