ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፥ ሰማይንም በስንዝሩ የለካ፥ ምድርንም ሁሉ ሰብስቦ በእጁ የያዘ፥ ተራሮችን በሚዛን፥ ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው? የእግዚአብሔርን ሕሊና ያወቀ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያማከረው ማን ነው? ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? ፍርድንስ ማን አስተማረው? የጥበብንስ መንገድ ማን አሳየው? እነሆ፥ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፤ እንደ ሚዛንም ውልብልቢት ተቈጥረዋል፤ እንደ ኢምንትም ናቸው። ሊባኖስ ለማንደጃ እንስሶችዋም ለሚቃጠል መሥዋዕት አይበቁም። አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንዳልነበሩ ናቸው፤ እንደ ከንቱ ነገርም ይመስላሉ። እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ? እንጨት ጠራቢ በሠራው ምስል፥ ወይስ አንጥረኛ መትቶ በሠራው ወርቅ፥ በወርቅም ለብጦ በሠራው ምስል ትመስሉታላችሁን? ጠራቢው የማይነቅዘውን እንጨት ይመርጣል፤ ምስሉም እንዳይናወጥ ያቆመው ዘንድ ብልህ ሠራተኛን ይፈልጋል። አላወቃችሁምን? ወይስ አልሰማችሁምን? ከጥንትስ አልተወራላችሁምን? ወይስ ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን? እርሱ የምድርን ክበብ ያጸናል፤ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፤ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው፥ እንደ ድንኳንም ለመኖሪያ የሚዘረጋቸው፤ አለቆችንም የሚገዛላቸው እንዳይኖር የሚያደርግ ምድርንም እንደ ኢምንት የሚያደርጋት እርሱ ነው። በእርሱም ላይ ዛፉንና ሣሩን፥ የማይቈጠር ሌላውንም ብዙ ፍጥረት የፈጠረ እርሱ ነው። ነፋስም በነፈሰባቸው ጊዜ ይደርቃሉ፤ ዐውሎ ነፋስም እንደ ገለባ ይጠርጋቸዋል። እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ እግዚአብሔር።
ትንቢተ ኢሳይያስ 40 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 40:12-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos