ትንቢተ ኢሳይያስ 34
34
በአሕዛብ ላይ ስለሚመጣው ፍርድ
1እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ቅረቡ፤ እናንተም አለቆች ሆይ፥ አድምጡ፤ ምድርና በውስጥዋም ያሉ፥ ዓለምና በውስጥዋም ያሉ ሕዝብ ሁሉ ይስሙ። 2የእግዚአብሔር ቍጣ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ነውና፤ መቅሠፍቱም ያጠፋቸውና ለጦር ይሰጣቸው ዘንድ በቍጥራቸው ልክ ነው። 3ከእነርሱም የተገደሉት በድናቸው ይጣላል፤ የሬሳቸውም ግማት ይሸታል፤ ተራሮቹም ከደማቸው የተነሣ ይርሳሉ። 4ሰማያት እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ፤ ከወይንና ከበለስም ቅጠል እንደሚረግፍ ከዋክብት ሁሉ ይረግፋሉ።
5ሰይፌ በሰማይ ሆና ሰከረች፤ እነሆ፥ በኤዶምያስና በሚጠፉት ሕዝብ ላይ ለፍርድ ትወርዳለች። 6እግዚአብሔር መሥዋዕት በባሶራ፥ ታላቅም እርድ በኤዶምያስ ምድር አለውና የእግዚአብሔር ሰይፍ በደም ተሞልታለች፤ በበግ ስብ፥ በፍየል ደምም፥ በአውራም በግ ስብ ወፍራለች። 7ኀያላን ከእነርሱ ጋር፥ ወይፈኖችም ከኮርማዎች ጋር ይወድቃሉ፤ ምድራቸውም በደም ትሰክራለች፤ በስባቸውም ትወፍራለች።
8የእግዚአብሔር የፍርዱ ቀን፥ ስለ ጽዮንም ፍርድ የብድራት ዓመት ነውና። 9ሸለቆዎችዋ ዝፍት ሆነው ይወጣሉ፤ አፈርዋም ዲን ይሆናል፤ መሬቷም በቀንና በሌሊት እንደ ዝፍት ይቃጠላል፤ ለዘለዓለምም አይጠፋም፤ 10ጢሱም ወደላይ ይወጣል፤ ከትውልድ እስከ ትውልድም ድረስ ባድማ ሆና ትኖራለች፤ ለብዙ ዘመናትም ትጠፋለች። 11ጭልፊቶችና ጃርት፥ ጕጕትና ቍራም ይኖሩባታል፤ መሠረቷንም በመፍረስ ገመድ ይለካሉ። አጋንንትም ያድሩባታል፤ 12አለቆችዋ ያልቃሉ፤ ነገሥታቷና መሳፍንቷ ይጠፋሉ። 13በከተማዎችዋም እሾህ፥ በቅጥሮችዋም አሜከላ ይበቅሉባታል፤ የአጋንንት ማደሪያና የሰጎን ስፍራ ትሆናለች። 14በዚያም አጋንንትና ጂኖች ይገናኛሉ፤ እነርሱም እርስ በርሳቸው ይጠራራሉ፤ ጂኖችም በዚያ ይኖራሉ፤ ለራሳቸውም ማረፊያን ያገኛሉ። 15በዚያ ጃርቶች ይዋለዳሉ፤ ምድርም ልጆችዋን በኀይል ታድናለች፤ ዋሊያዎች በዚያ ይገናኛሉ፤ ፊት ለፊትም ይተያያሉ።#ዕብ. “በዚያም ዋሊያ ቤቷን ትሠራለች ፤ ዕንቁላልም ትጥላለች ፤ ትቀፈቅፈውማለች ፤ እያንዳንዳቸው ከባልንጀሮቻቸው ጋር ይሰበሰባሉ” ይላል።
16በየቍጥራቸው ያልፋሉ፤ ከእነርሱም አንዱ አይጠፋም፤ እርስ በርሳቸው አይተጣጡም፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አዝዞአቸዋልና መንፈሱም ሰብስቦአቸዋልና። 17እርሱም ዕጣ ጣለባቸው፤ እጁም ከፈለችላቸው፤ ለዘለዓለም ይሰማሩባታል፤ ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ይወርሱአታል፤ በውስጥዋም ያርፉባታል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 34: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ