ትን​ቢተ ኢሳ​ይ​ያስ 30:12-18

ትን​ቢተ ኢሳ​ይ​ያስ 30:12-18 አማ2000

ስለ​ዚህ የእ​ስ​ራ​ኤል ቅዱስ እን​ዲህ ይላል፥ “ይህ​ችን ቃል አቃ​ል​ላ​ች​ኋ​ልና፥ በሐ​ሰ​ትና በጠ​ማ​ማ​ነት ተስፋ አድ​ር​ጋ​ች​ኋ​ልና፥ አጕ​ረ​ም​ር​ማ​ች​ኋ​ል​ምና፥ በዚ​ህም ቃል ታም​ና​ች​ኋ​ልና፤ ስለ​ዚህ ይህ በደል አዘ​ብ​ዝቦ ለመ​ፍ​ረስ እንደ ቀረበ፥ አፈ​ራ​ረ​ሱም ፈጥኖ ድን​ገት እን​ደ​ሚ​መጣ እንደ ከተማ ቅጥር ይሆ​ን​ባ​ች​ኋል። አወ​ዳ​ደ​ቁም እንደ ሸክላ ሠሪ ገንቦ የደ​ቀቀ ይሆ​ናል፤ ሳይ​ራ​ራም ያደ​ቅ​ቀ​ዋል፤ ከስ​ባ​ሪ​ውም እሳት ከማ​ን​ደጃ የሚ​ወ​ስ​ዱ​በት፥ ወይም ውኃ ከጕ​ድ​ጓድ የሚ​ቀ​ዱ​በት ገል አይ​ገ​ኝም።” የእ​ስ​ራ​ኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላ​ልና፥ “ብት​ጸ​ጸ​ትና ብታ​ለ​ቅስ ትድ​ና​ለህ፤ የት እን​ዳ​ለ​ህም ታው​ቃ​ለህ፤ በከ​ንቱ ታም​ነ​ሃ​ልና፤ ኀይ​ላ​ች​ሁም ከንቱ ይሆ​ናል፤ እና​ንተ ግን መስ​ማ​ትን እንቢ አላ​ችሁ፤ ነገር ግን፥ በፈ​ረስ ላይ ተቀ​ም​ጠን እን​ሸ​ሻ​ለን እንጂ እን​ዲህ አይ​ሆ​ንም አላ​ችሁ፤ ስለ​ዚ​ህም ትሸ​ሻ​ላ​ችሁ፤ ደግ​ሞም በፈ​ጣን ፈረስ ላይ እን​ቀ​መ​ጣ​ለን አላ​ችሁ፤ ስለ​ዚ​ህም የሚ​ያ​ሳ​ድ​ዱ​አ​ችሁ ፈጣ​ኖች ይሆ​ናሉ። ከአ​ንድ ሰው ዛቻ የተ​ነሣ ሺህ ሰዎች ይሸ​ሻሉ፤ እና​ን​ተም በተ​ራራ ራስ ላይ እን​ዳለ ምሰሶ፥ በኮ​ረ​ብ​ታም ላይ እን​ዳለ ምል​ክት ሆና​ችሁ እስ​ክ​ት​ቀሩ ድረስ፥ ከአ​ም​ስት ሰዎች ዛቻ የተ​ነሣ ብዙ​ዎች ይሸ​ሻሉ።” አም​ላ​ካ​ችን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፈራጅ ነውና ስለ​ዚህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይራ​ራ​ላ​ችሁ ዘንድ ይታ​ገ​ሣል፤ ይም​ራ​ች​ሁም ዘንድ ከፍ ከፍ ይላል፤ እር​ሱን በመ​ተ​ማ​መን የሚ​ጠ​ባ​በቁ ሁሉ ብፁ​ዓን ናቸው።