ትንቢተ ኢሳይያስ 30:12-18

ትንቢተ ኢሳይያስ 30:12-18 አማ05

ስለዚህ የእስራኤል ቅዱስ ቃል ይህ ነው፦ “እናንተ ማስጠንቀቂያን ንቃችሁ ይደግፈናል ብላችሁ በተማመናችሁበት በግፍና በማታለል ላይ እምነታችሁን ጥላችኋል። ስለዚህ ይህ በደላችሁ ተሰነጣጥቆ በማኰፍኰፍ ሊወድቅ እንደ ተቃረበና አወዳደቁም በፍጥነትና በቅጽበት እንደሚደርስበት እንደ ረጅም የቅጽር ግንብ ያደርጋችኋል። ከተሰባበረ በኋላ ለእሳት መጫሪያ ወይም ለውሃ መጥለቂያ የሚሆን ከፍ ያለ ገል እንኳ ከመካከሉ እንደማይገኝበት ተንኰታኲቶ እንደሚወድቅ የሸክላ ዕቃ ትሆናላችሁ።” የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በመመለስና በማረፍ ደኅንነትን ታገኛላችሁ፤ ጸጥ በማለትና በመታመን ኀይል ታገኛላችሁ፤ እናንተ ግን እምቢ አላችሁ። በዚህ ፈንታ በፈጣን ፈረሶች ላይ ተቀምጣችሁ ከጠላቶቻችሁ እጅ ለማምለጥ ታቅዳላችሁ፤ ስለዚህም ትሸሻላችሁ፤ ‘ፈረሶቻችን እጅግ ፈጣኖች ናቸው’ ትሉ ይሆናል፤ ነገር ግን አሳዳጆቻችሁ ከእናንተ የፈጠኑ ይሆናሉ። ከጠላት ወታደር የአንድ ሰው ዛቻ ከእናንተ ሺህ ሰዎችን እንዲሸሹ ያደርጋል፤ እናንተን በሙሉ አምስት የጠላት ወታደሮች በተራራ ላይ እንዳለ የሰንደቅ ዓላማ ምሰሶና በኰረብታ ላይ ያለን ምልክት ጥቂቶቻችሁ ብቻ እስክትቀሩ ድረስ ያባርሩአችኋል። ይህም ሁሉ ሆኖ እግዚአብሔር ምሕረት ሊያደርግላችሁ ተዘጋጅቶአል፤ እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ስለ ሆነ ሊራራላችሁ ወዶአል፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር የሚታመኑ ሁሉ የተባረኩ ናቸው።”