ትንቢተ ኢሳይያስ 19
19
ስለ ግብፅ የተነገረ ትንቢት
1ስለ ግብፅ የተነገረ ራእይ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደ ግብፅ ይመጣል፤ የግብፅም የእጆቻቸው ሥራዎች#ዕብ. “ጣዖታት” ይላል። በፊቱ ይዋረዳሉ፤ የግብፃውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል። 2“ግብፃውያን በግብፃውያን ላይ ይነሣሉ፤ ወንድምም ወንድሙን፥ ሰውም ባልንጀራውን ይገድላል፤ ከተማም ከተማን፥ መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል። 3የግብፅም መንፈስ በውስጣቸው ትደነግጣለች፤ ምክራቸውን አጠፋለሁ፤ እነርሱም አማልክቶቻቸውንና ጣዖቶቻቸውን፥ ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎቻቸውንም ይጠይቃሉ። 4ግብፃውያንንም በጨካኝ ጌቶች እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ጨካኞች ነገሥታትም ይገዟቸዋል” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 5ግብፃውያን ከባሕር ውኃን ይጠጣሉ፤#ዕብ. “ውሆች ከባሕር ይደርቃሉ” ይላል። ወንዙም ያንሳል፤ ደረቅም ይሆናል። 6ወንዞችም ይነጥፋሉ። ቦዮችና መስኖች ያንሳሉ፤ ይደርቃሉም፤ ደንገልና ቄጤማ ይጠወልጋሉ። 7በዓባይ ወንዝ ዳር ያለው መስክ፥ በዓባይም ወንዝ አጠገብ የተዘራ እርሻ ሁሉ በነፋስ ይመታል፤ ይደርቃልም፤ 8ዓሣ አጥማጆቹ ያዝናሉ፤ በዓባይም ወንዝ መቃጥን የሚጥሉት ሁሉ ያለቅሳሉ፤ በውኆችም ላይ መረብ የሚዘረጉት ያለቅሳሉ። 9የተቈራረጠውንም መረብ የሚጠግኑ፥ ነጩንም ልብስ የሚሠሩ ሸማኔዎች ያፍራሉ። 10በእነርሱም የሚሠሩ ይሠቃያሉ፤ በሐር ኩብ የሚነግዱ ሁሉ ይቀልጣሉ፤ ልቡናቸውም ያዝናል።#ምዕ. 19 ቍ. 10 በዕብ. ልዩነት አለው።
11የጣኔዎስ አለቆች ሰነፎች ይሆናሉ፤ ነገሥታትን የሚመክሩ ጥበበኞችም ምክራቸው ስንፍና ትሆናለች። ንጉሥን፥ “እኛ የጥበበኞች ልጆች፥ የቀደሙ ነገሥታትም ልጆች ነን እንዴት ትሉታላችሁ?” 12አሁን ጥበበኞችህ የት አሉ? አሁን ያብስሩህ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በግብፅ ላይ ያሰበውን እስኪ ይንገሩህ። 13የጣኔዎስ አለቆች አለቁ፤ የሜምፎስም አለቆች ከፍ ከፍ አሉ፤ ግብፃውያን በየወገናቸው ተሳሳቱ።#ዕብ. “የነገዶችዋ የማዕዘን ድንጋዮች የሆኑ ግብፅን አሳቱ” ይላል። 14እግዚአብሔር የሚያስት መንፈስን ልኮባቸዋልና፤ ሰካርም፥ ደም ያዞረውም እንዲስት እንዲሁ ግብፃውያን በሥራቸው ሁሉ ሳቱ። 15ለግብፃውያን ራስ ወይም ጅራት፥ መጀመሪያ ወይም መጨረሻ#ዕብ. “የሰሌን ቅርንጫፍ ወይም እንግጫ” ይላል። ያለው ሥራ የላቸውም።
16በዚያም ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከሚያወርድባቸው ፍርሀትና መንቀጥቀጥ የተነሣ ግብፃውያን እንደ ሴቶች ይሆናሉ። 17የይሁዳም ምድር ግብፅን የምታስደነግጥ ትሆናለች፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከመከረባት ምክር የተነሣ ስምዋን የሚሰማ ሁሉ ይፈራል።
18በዚያ ቀን አምስት የግብፅ ከተሞች በከነዓን ቋንቋ ይናገራሉ፤ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔርም ስም ይጠሩ ዘንድ ከተሞች አንድ ይሆናሉ፤ ከእነዚህም አንዲቱ የጽድቅ ከተማ ተብላ ትጠራለች።#ዕብ. “አንዲቱም ከተማ የጥፋት ከተማ ትባላለች” ይላል።
19በዚያ ቀን በግብፅ ምድር መካከል አንዲቱ ከተማ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ትሆናለች፤ በዳርቻዋም ለእግዚአብሔርዐምድ#ግእዙ “ቤተ እግዚአብሔር” ይላል። ይሆናል። 20ይህም ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በግብፅ ምድር ለዘለዓለም ምልክት ይሆናል፤ ከሚያስጨንቋቸው የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉና፥ እርሱም የሚያድናቸውን ሰው ይልክላቸዋል፤ ይፈርዳል፤ ያድናቸዋልም። 21በዚያም ቀን እግዚአብሔር በግብፅ የታወቀ ይሆናል፤ በዚያም ጊዜ ግብፃውያን እግዚአብሔርን ያውቃሉ፤ መሥዋዕትም ያቀርቡለታል፤ ለእግዚአብሔርም ስእለት ይሳላሉ፤ መባኡንም ያገባሉ። 22እግዚአብሔርም ግብፅን በታላቅ መቅሠፍት ይመታታል፤ ይፈውሳታልም፤ ከዚያም በኋላ ወደ እግዚአብሔር ይመለሳሉ፤ እርሱም ይሰማቸዋል፤ ይፈውሳቸውማል።
23በዚያም ወራት ከግብፅ ወደ አሦር መንገድ ይሆናል፤ አሦራዊውም ወደ ግብፅ፥ ግብፃዊውም ወደ አሦር ይገባል፤ ግብፃውያንም ለአሦራውያን ይገዛሉ። 24በዚያም ወራት እስራኤል ለግብፅና ለአሦር ሦስተኛ ይሆናል፤ በምድርም መካከል በረከት ይሆናል። 25የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ “በግብፅ ውስጥ ያለ ሕዝቤ፥ በአሦር መካከልም ያለ ሕዝቤ፥ ርስቴም እስራኤል የተባረከ ይሁን” ብሎ ይባርካቸዋልና።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 19: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ