ትንቢተ ኢሳይያስ 17
17
ሶርያና እስራኤል እንደሚቀጡ
1ስለ ደማስቆ የተነገረ ቃል። “እነሆ፥ ደማስቆ ከከተሞች መካከል ተለይታ ትጠፋለች፤ ትፈርሳለችም። 2ለዘለዓለም የተፈታች ትሆናለች፤ ለመንጋ ማሰማርያም ትሆናለች፤ የሚያሳድዳቸውም የለም። 3ኤፍሬም የሚጠጋበት ምሽግ አይኖርም፤ ከእንግዲህም ወዲያ ንጉሥ በደማስቆ አይነግሥም። የሶርያ ቅሬታ ሆይ፥ ከእስራኤል ልጆች ከክብራቸው የምትሻል አይደለህም” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
4“በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ የያዕቆብ ክብር ይደክማል፤ የሚበዛ#ዕብ. “የሥጋውም ውፍረት ይከሳል” ይላል። የክብሩ ብልጽግናም ይነዋወጣል። 5አጫጅ የቆመውን እህል ሰብስቦ ዛላውን እንደሚያጭድ ይሆናል፤ በሸለቆ እሸትን እንደሚሰበስብም እንዲሁ ይሆናል። 6ወይራ በተመታ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ፍሬ በራሱ ላይ እንደሚቀር፥ አራት ወይም አምስት በዛፊቱ ጫፍ እንደሚገኝ፥ በእርሱ ዘንድ ቃርሚያ ይቀራል” ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር።
7በዚያም ቀን ሰው በፈጣሪው ይታመናል፤ ዐይኖቹም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ። 8በጣዖታቸውና ጣቶቻቸው በሠሩአቸው የእጃቸው ሥራዎች አይተማመኑም፤ ለርኵሰታቸውም ዛፎችን አይቈርጡም። 9በዚያም ቀን በእስራኤል ልጆች ፊት የአሞራውያንና የኤዌዎያውያን ከተሞች እንደ ተፈቱ፥ እንዲሁ ከተሞችህ ይፈታሉ፤ ባድማም ይሆናሉ። 10አዳኝህ እግዚአብሔርን ትተኸዋልና፥ ረዳትህ እግዚአብሔርንም አላስብኸውም፤ ስለዚህ የሐሰትን#ዕብ. “ያማረ” ይላል። ተክል ተክለሃል፤ የሐሣርንም#ዕብ. “እንግዳንም” ይላል። ዘር ዘርተሃል። 11ተክልን በተከልህበት ቀን ትበድላለህ፤ የዘራኸውም በበነጋው በምታወርስበት ቀን ይበቅላል፤ አባትም ለልጁ እንደሚያወርስ አንተም ለልጆችህ ታወርሳለህ።#ምዕ. 17 ቍ. 11 አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ ልዩነት ያሳያል።
12እንደ ውኃ ለሞሉ፥ ከተራራ በመከታተል እንደሚወርድ የውኃ ፈሳሽ ለሆኑም ብዙዎች አሕዛብ ወዮላቸው! 13ብዙዎች አሕዛብ እንደ ብዙ ውኃ ናቸው፤ ከፏፏቴ ውስጥ በኀይል እንደሚወርድ እንደ ብዙ ውኃ ፈሳሽ ይጮኻሉ፤ ያጠፉታልም፤ እነርሱም ከሩቅ ይወርዳሉ፤ በተራራም ላይ እንዳለ እብቅ፥ በነፋስ ፊት ዐውሎ ነፋስ እንደሚያዞረው እንደ መንኰራኵር ትቢያም ይበተናሉ። 14በመሸም ጊዜ ሳይነጋ ያለቅሳሉ፤ ያንጊዜም የይሁዳ ወገኖች “ይህ የወራሾች ርስት ነው፤ የበዘበዙንም ዕድል ፋንታ ይህ ነው” ይላሉ።#ምዕ. 17 ከቍ. 12 እስከ 14 በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. ልዩ ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 17: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ