ትንቢተ ሐጌ 1
1
1በንጉሡ በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት በስድስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ ወደ ይሁዳ አለቃ ወደ ሰላትያል ልጅ ወደ ዘሩባቤል፥ ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኢዮሴዴቅ ልጅ ወደ ኢያሱ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፦ ይህ ሕዝብ፦ ዘመኑ አልደረሰም፥ የእግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ዘመን አልደረሰም ይላል ብሎ ተናገረ። 3የእግዚአብሔርም ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፦ 4በውኑ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? 5አሁንም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። 6ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፣ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፣ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፣ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፣ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ።
7የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። 8ወደ ተራራው ውጡ፥ እንጨትንም አምጡ፥ ቤቱንም ሥሩ፣ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፥ እኔም እመሰገናለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 9እናንተ ብዙ ነገርን ተስፋ አደረጋችሁ፥ እነሆም፥ ጥቂት ሆነ፣ ወደ ቤትም ባገባችሁት ጊዜ እፍ አልሁበት። ይህ ስለ ምንድር ነው? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ሁሉ ወደ እየቤታችሁ እየሮጣችሁ የእኔ ቤት ፈርሶ ስለ ተቀመጠ ነው። 10ስለዚህ ሰማያት በላያችሁ ጠልን ከልክለዋል፥ ምድሪቱም ፍሬዋን ከልክላለች። 11እኔም በምድርና በተራሮች፥ በእህልና በወይንም፥ በዘይትና ምድርም በምታበቅለው ላይ፥ በሰዎችና በእንስሶችም ላይ፥ እጅም በሚደክምበት ሁሉ ላይ ድርቅን ጠርቻለሁ።
12የሰላትያልም ልጅ ዘሩባቤል፥ ታላቁም ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ሕዝብ ሁሉ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ድምፅ የነቢዩንም የሐጌን ቃል፥ አምላካቸው እግዚአብሔር እንደ ላከው ሁሉ ሰሙ፣ ሕዝቡም በእግዚአብሔር ፊት ፈሩ። 13የእግዚአብሔርም መልእክተኛ ሐጌ በእግዚአብሔር መልእክት ሕዝቡን፦ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር ብሎ ተናገረ። 14-15እግዚአብሔርም የይሁዳን አለቃ የሰላትያልን ልጅ የዘሩባቤልን መንፈስ፥ የታላቁንም ካህን የኢዮሴዴቅን ልጅ የኢያሱን መንፈስ፥ የቀሩትንም ሕዝብ ሁሉ መንፈስ አስነሣ፣ በንጉሡም በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት በስድስተኛው ወር ከወሩም በሀያ አራተኛው ቀን መጡ፥ የአምላካቸውንም የሠራዊትን ጌታ የእግዚአብሔርን ቤት ሠሩ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሐጌ 1: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ