ኦሪት ዘፍጥረት 45
45
ዮሴፍ ራሱን ለወንድሞቹ መግለጡ
1ዮሴፍም በፊቱ ሰዎች ሁሉ ቆመው ሳሉ ሊታገሥ አልተቻለውም፥ “ሰዎቹንም ሁሉ ከፊቴ አስወጡልኝ” ብሎ ተናገረ፤ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን በገለጠ ጊዜ በእርሱ ዘንድ የቆመ ማንም አልነበረም። 2ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ የግብፅ ሰዎችም ሰሙ፤ በፈርዖን ቤትም ተሰማ። 3ዮሴፍም ለወንድሞቹ፥ “እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ፤ አባቴ እስከ አሁን በሕይወቱ ነውን?” አላቸው። ወንድሞቹም ይመልሱለት ዘንድ አልቻሉም፤ ደንግጠው ነበርና። 4ዮሴፍም ወንድሞቹን፥ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። ወደ እርሱም ቀረቡ። እንዲህም አላቸው፥ “ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። 5አሁንም ወደዚህ ስለሸጣችሁኝ አትፍሩ፤ አትቈርቈሩም፤ እግዚአብሔር ለሕይወት ከእናንተ በፊት ልኮኛልና። 6እነሆ፥ ይህ ሁለቱ ዓመት በምድር ላይ ራብ የሆነበት ነውና፤ የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ገና አለ። 7እግዚአብሔርም በምድር ላይ እንድትድኑና እንድትተርፉ እመግባችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ። 8አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፤ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፤ ለፈርዖንም እንደ አባት#ግእዙ “ልጅ” ይላል። አደረገኝ፤ በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብፅ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ። 9አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ሂዱ፤ እንዲህም በሉት፦ ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው፦ እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፤ ወደ እኔ ና፤ በዚያም አትዘግይ፤ 10በዐረብ በኩል በጌሤም ምድርም ትቀመጣለህ፤ ወደ እኔም ትቀርባለህ። አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች፥ በጎችህና ላሞችህ፥ የአንተ የሆነው ሁሉ፥ 11በዚያም አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ፤ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና፤ 12እነሆም፥ ለእናንተ እኔ ራሴ በአፌ እንደ ተናገርሁአችሁ እናንተ በዐይኖቻችሁ አይታችኋል፤ ወንድሜ ብንያም በዐዓይኖቹ አይቶአል። 13ለአባቴ በግብፅ ምድር ያለኝን ክብሬን ሁሉ፥ በዐይኖቻችሁ ያያችሁትንም ሁሉ ንገሩት፤ አባቴንም ወደዚህ ፈጥናችሁ አምጡት።” 14የወንድሙን የብንያምንም አንገት አቅፎ አለቀሰ፤ ብንያምም በአንገቱ ላይ አለቀሰ። 15ወንድሞቹን ሁሉ ሳማቸው፤ በእነርሱም ላይ አለቀሰ፤ ከዚያም በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር ተጨዋወቱ።
16በፈርዖንም ቤት፥ “የዮሴፍ ወንድሞች መጡ” ተብሎ ወሬ ተሰማ፤ ፈርዖንና ቤተ ሰቡም ሁሉ ደስ አላቸው። 17ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፥ “ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ይህን አድርጉ፤ ዕቃችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ሂዱ፤ 18አባታችሁንና ንብረታችሁን ሁሉ#ዕብ. “ቤተ ሰባችሁን” ይላል። ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም የግብፅን ምድር በረከት ሁሉ እሰጣችሁአለሁ፤ የምድሪቱንም ድልብ ትበላላችሁ። 19አንተም ወንድሞችህን፦ እንዲህ አድርጉ በላቸው፤ ከግብፅ ምድር ለሕፃኖቻችሁ፥ ለሴቶቻችሁም ሰረገሎችን ውሰዱ፤ አባታችሁንም ይዛችሁ ኑ፤ 20ለዕቃችሁም ዐይናችሁ ለአየውም ሁሉ አታስቡ፤ የግብፅ በረከት ሁሉ ለእናንተ ነውና።”
21የእስራኤል ልጆችም እንደ አዘዛቸው አደረጉ፤ ዮሴፍም የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን እንደ ነገረው ሰረገሎችንና ለመንገድ ስንቅን ሰጣቸው፤ 22ለሁሉም ሁለት ሁለት መለወጫ ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን ሦስት መቶ ብርና አምስት መለወጫ ልብስ ሰጠው። 23ለአባቱም እንደዚሁ ላከ፤ ከግብፅ በረከት ሁሉ የተጫኑ ዐሥር አህዮችን፥ ደግሞም በመንገድ ለአባቱ ስንቅ የተጫኑ ዐሥር በቅሎዎችን። 24ዮሴፍም ወንድሞቹን አሰናበታቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “በመንገድ እርስ በርሳችሁ አትጣሉ።” 25እነርሱም ከግብፅ ሀገር ወጥተው ሄዱ፤ ወደ ከነዓንም ምድር ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ደረሱ። 26እንዲህም ብለው ነገሩት፥ “ልጅህ ዮሴፍ በሕይወቱ ነው፤ እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ገዥ ሆኖአል።” ያዕቆብም ልቡ ደነገጠ፤ አላመናቸውምም፤ 27እነርሱም ዮሴፍ ያላቸውን፥ የተናገራቸውንም ነገር ሁሉ ነገሩት፤ ይወስዱት ዘንድ ዮሴፍ የላካቸውን ሰረገሎች በአየ ጊዜ የአባታቸው የያዕቆብ ልቡ፥ መንፈሱም ታደሰ። 28እስራኤልም፥ “ልጄ ዮሴፍ ገና በሕይወት ከሆነ ይህ ለእኔ ታላቅ ነገር ነው፤ ሳልሞት እንዳየው እሄዳለሁ” አለ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 45: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ