ፈርዖንም ልኮ ዮሴፍን አስጠራው፤ ከግዞት ቤትም አወጡት፤ ራሱንም ላጩት፤ ልብሱንም ለወጡ፤ ወደ ፈርዖንም ገባ። ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፥ “ሕልምን አየሁ፤ የሚተረጕምልኝም አጣሁ፤ ሕልምን እንደ ሰማህ፥ እንደ ተረጐምህም ስለ አንተ ሰማሁ።” ዮሴፍም፥ “እግዚአብሔር ከገለጸለት ሰው በቀር መተርጐም የሚችል የለም” ብሎ ለፈርዖን መለሰለት። ፈርዖንም ለዮሴፍ እንዲህ አለው፥ “እነሆ፥ በሕልሜ በወንዝ ዳር ቆሜ ነበር፤ እነሆም፥ ሥጋቸው የወፈረ፥ መልካቸውም ያማረ ሰባት ላሞች ወጡ፤ በወንዙ ዳር በመስኩም ይሰማሩ ነበር፤ ከእነርሱም በኋላ እነሆ፥ የደከሙ፥ መልካቸውም እጅግ የከፋ፥ ሥጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጡ፤ በግብፅም ምድር ሁሉ እንደ እነርሱ መልከ ክፉ ከቶ አላየሁም፤ እነዚያ የከሱትና መልከ ክፉዎቹ ላሞች እነዚያን የመጀመሪያዎቹን ያማሩና የወፈሩ ሰባት ላሞች ዋጡአቸው፤ በሆዳቸውም ተዋጡ፤ በሆዳቸውም ውስጥ የገባ እንደሌለ ሆኑ፤ መልካቸውም በመጀመሪያ እንደ ነበረው የከፋ ነበረ፤ ነቃሁም። ዳግመኛም ተኛሁ፤ በሕልሜም እነሆ፥ የጐመሩና መልካም የሆኑ ሰባት እሸቶች ከአንድ አገዳ ሲወጡ አየሁ፤ ከእነርሱም በኋላ እነሆ የሰለቱና በነፋስ የተመቱ ሌሎች ሰባት እሸቶች ወጡ፤ እነዚያ የሰለቱትና በነፋስ የተመቱት እሸቶች እነዚያን ያማሩትንና የጐመሩትን ሰባቱን እሸቶች ዋጡአቸው። ለሕልም ተርጓሚዎችም ሕልሜን ነገርሁ፤ የተረጐመልኝም የለም።” ዮሴፍም ፈርዖንን አለው፥ “የፈርዖን ሕልሙ አንድ ነው፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን አሳይቶታል። እነዚያ ሰባቱ መልካካሞች ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እነዚያም ሰባቱ መልካካሞች እሸቶች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ የፈርዖን ሕልሙ አንድ ነው። ከእነርሱም በኋላ የወጡት እነዚያ የከሱና መልከ ክፉዎቹ ሰባት ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እነዚያም የሰለቱትና ነፋስ የመታቸው ሰባቱ እሸቶች እነርሱ ራብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ናቸው። ለፈርዖን የነገርሁት ነገር ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን አሳየው። እነሆ፥ በግብፅ ምድር ሁሉ እጅግ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ፤ ደግሞም ከዚህ በኋላ ሰባት የራብ ዓመት ይመጣል፤ በግብፅ ሀገር ሁሉ የነበረውንም ጥጋብ ሁሉ ይረሱታል፤ ራብም ምድርን ሁሉ ያጠፋል፤ በኋላም ከሚሆነው ከዚያ ራብ የተነሣ በምድር የሆነው ጥጋብ አይታወቅም፤ እጅግ ጽኑ ይሆናልና። ሕልሙም ለፈርዖን ደጋግሞ መታየቱ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ስለሆነ ነው፤ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ያደርገዋል። አሁንም ብልህና ዐዋቂ ሰውን ለአንተ ፈልግ፤ በግብፅ ምድር ላይም ሹመው። ፈርዖን በግብፅ ምድር ላይ ሹሞችን ይሹም፤ በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ፍሬ በግብፅ ምድር ሁሉ ከአምስት እጅ አንደኛውን ይውሰድ። የሚመጡትን የመልካሞቹን ሰባት ዓመታት እህላቸውን ያከማቹ፤ ስንዴውንም ከፈርዖን እጅ በታች ያኑሩ፤ እህሎችም በከተሞች ይጠበቁ። በግብፅ ምድር ስለሚሆነው ስለ ሰባቱ ዓመታት ራብ እህሉ ለሀገሩ ሁሉ ተጠብቆ ይኑር፥ ምድሪቱም በራብ አትጠፋም።”
ኦሪት ዘፍጥረት 41 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 41:14-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች