ኦሪት ዘፍጥረት 38
38
ይሁዳና ትዕማር
1በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ ወረደ፤ ስሙ ኤራስ በሚባል በዓዶሎማዊውም ሰው ዘንድ አደረ። 2ከዚያም ይሁዳ ያንድ ከነዓናዊ ሰው ሴት ልጅን አየ፤ ስምዋም ሴዋ#ዕብ. “ሴዋን” የይሁዳ የሚስቱ አባት ነው ይላል። ይባላል። ወሰዳትም፤ ወደ እርስዋም ገባ። 3ፀነሰችም፤ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም ዔር ብላ ጠራችው። 4ደግሞም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም አውናን ብላ ጠራችው። 5እንደገና ደግሞ ወንድ ልጅን ወለደች፤ ስሙንም ሴሎም ብላ ጠራችው፤ እነርሱንም በወለደች ጊዜ ኬሴቢ በሚባል ሀገር ነበረች። 6ይሁዳም ለበኵር ልጁ ለዔር ትዕማር የምትባል ሚስት አጋባው። 7የይሁዳም የበኵር ልጅ ዔር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው። 8ይሁዳም አውናንን፥ “ወደ ወንድምህ ሚስት ግባ፤ አግባትም፤ ለወንድምህም ዘርን አቁምለት” አለው። 9አውናንም ዘሩ ለእርሱ እንዳይሆን ዐወቀ፤ ወደ ወንድሙ ሚስትም በገባ ጊዜ ለወንድሙ ዘር እንዳይተካ ዘሩን በምድር ያፈስሰው ነበር። 10ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ ሆነበት፤ እንዲህ አድርጎአልና እርሱንም ደግሞ ቀሠፈው። 11ይሁዳም ምራቱን ትዕማርን፥ “ልጄ ሴሎም እስኪያድግ ድረስ በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ተቀመጪ” አላት፤ እርሱ ደግሞ እንደ ወንድሞቹ እንዳይሞትብኝ ብሎአልና። ትዕማርም ሄዳ በአባቷ ቤት ተቀመጠች።
12ዘመንዋም በተፈጸመ ጊዜ የይሁዳ ሚስት ሴዋ ሞተች፤ ይሁዳም ተጽናና፤ የበጎቹን ጠጕር ወደሚሸልቱት ሰዎችም ወደ ተምና ወጣ፤ እርሱም ዓዶሎማዊው በግ ጠባቂው ኤራስም። 13ለምራቱ ትዕማርም፥ “እነሆ፥ አማትሽ ይሁዳ የበጎቹን ጠጕር ይሸልት ዘንድ ወደ ተምና ይወጣል” ብለው ነገሩአት። 14እርስዋም የመበለትነቷን ልብስ አወለቀች፤ መጐናጸፊያዋንም ለበሰች፤ ተሸፈነችም፤ ወደ ተምናም በሚወስደው መንገድ ዳር በኤናይም ደጅ ተቀመጠች፤ ሴሎም እንደ አደገ፥ ሚስትም ትሆነው ዘንድ እርስዋን ሊሰጠው እንዳልፈለገ አይታለችና። 15ይሁዳም በአያት ጊዜ ዘማ መሰለችው፤ ፊቷን ተሸፍና ነበርና አላወቃትም። 16ወደ እርስዋም አዘነበለ፥ “እባክሽ ወደ አንቺ ልግባ አላት፤” እርስዋ ምራቱ እንደ ሆነች አላወቀም ነበርና። እርስዋም፥ “ወደ እኔ ብትገባ ምን ትሰጠኛለህ?” አለችው። 17“የፍየል ጠቦት ከመንጋዬ እልክልሻለሁ” አላት። እርስዋም፥ “እስክትልክልኝ ድረስ መያዣ ስጠኝ” አለችው። 18እርሱም፥ “ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እርስዋም፥ “ቀለበትህን፥ ኩፌትህን፥ በእጅህ ያለውን በትር” አለች። እርሱም ሰጣትና ከእርስዋ ደረሰ፤ እርስዋም ፀነሰችለት። 19እርስዋም ተነሥታ ሄደች፤ መጐናጸፊያዋንም አውልቃ የመበለትነቷን ልብስ ለበሰች። 20ይሁዳም መያዣውን ከሴቲቱ እጅ ይቀበል ዘንድ በበግ ጠባቂው በዓዶሎማዊው እጅ የፍየሉን ጠቦት ላከላት፤ እርስዋንም አላገኛትም። 21እርሱም የሀገሩን ሰዎች፥ “በኤናይም በመንገድ ዳር ተቀምጣ የነበረች ዘማ ወዴት ናት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “በዚህ ዘማ አልነበረችም” አሉት። 22ወደ ይሁዳም ተመልሶ እንዲህ አለው፥ “አላገኘኋትም፤ የሀገሩ ሰዎች ደግሞ፦ ከዚህ ዘማ የለችም” አሉኝ። 23ይሁዳም፥ “እኛ መዘበቻ እንዳንሆን ትውሰደው፤ እነሆ፥ የፍየሉን ጠቦት ላክሁላት፤ አንተም አላገኘሃትም” አለ።
24እንዲህም ሆነ፤ ከሦስት ወር በኋላ ለይሁዳ፥ “ምራትህ ትዕማር ሴሰነች፤ እነሆ፥ በዝሙት ፀነሰች” ብለው ነገሩት። ይሁዳም፥ “አውጡአትና በእሳት ትቃጠል” አለ። 25እርስዋም ሲወስዱአት ወደ አማቷ እንዲህ ብላ ላከች፤ “ተመልከት፦ ይህ ቀለበት፥ ይህ ኩፌት፥ ይህ በትር የማን ነው? ይህስ ፅንስ የማን ነው?” 26ይሁዳም አይቶ “ከእኔ ይልቅ ትዕማር እውነተኛ ሆነች፤ ልጄን ሴሎምን አልሰጠኋትምና” አለ። ትገደል ማለትንም ተወ፤#“ትገደል ማለትንም ተወ” በግእዝ ብቻ ነው። ደግሞም አላወቃትም። 27መውለጃዋም በደረሰ ጊዜ እነሆ፥ መንታ ልጆች በሆድዋ ነበሩ። 28ስትወልድም አንዱ እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም ቀይ ፈትል ወስዳ በእጁ አሰረች፥ “ይህ መጀመሪያ ይወጣል” አለች። 29እንዲህም ሆነ፤ እጁን በመለሰ ጊዜ እነሆ፥ ወንድሙ ወጣ፤ እርስዋም፥ “ለምን ጥሰህ ወጣህ? ስትል ስሙን ፋሬስ” ብላ ጠራችው። 30ከእርሱም በኋላ ቀይ ፈትል በእጁ ያለበት ወንድሙ ወጣ፤ ስሙም ዛራ ተባለ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 38: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ