ላባም ያዕቆብን፥ “በእውነት አንተ አጥንቴ ሥጋዬም ነህ፤ ከእኔ ጋር ተቀመጥ” አለው። አንድ ወር የሚያህልም ከእርሱ ጋር ተቀመጠ። ላባም ያዕቆብን፥ “ወንድሜ ስለሆንህ በከንቱ አታገለግለኝም ደመወዝህ ምንድን ነው? ንገረኝ” አለው ለላባም ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱም ስም ራሔል ነበረ። ልያም ዓይነ ልም ነበረች፤ ራሔል ግን መልከ መልካም ነበረች፥ ፊቷም ውብ ነበረ። ያዕቆብም ራሔልን ወደዳት፤ ያዕቆብም ላባን እንዲህ አለው፥ “ስለ ታናሺቱ ልጅህ ስለ ራሔል ሰባት ዓመት እገዛልሃለሁ። ሚስት ትሆነኝ ዘንድ እርስዋን ስጠኝ” አለው። ላባም፥ “ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለማውቅህ ለዘመዴ ለአንተ ብሰጣት ይሻላል፤ ከእኔ ጋር ተቀመጥ” አለው። ያዕቆብም ስለ ራሔል ሰባት ዓመት ተገዛ፤ እርስዋንም ይወድዳት ስለነበረ በእርሱ ዘንድ ጥቂት ቀን ሆነለት። ያዕቆብም ላባን፥ “እንግዲህ ወደ እርስዋ እገባ ዘንድ ሚስቴን ስጠኝ፥ ቀኔ ተፈጽሞአልና አለው።” ላባም የዚያን ስፍራ ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፥ ሰርግም አደረገ። በመሸም ጊዜ ልጁን ልያን ወስዶ ወደ ያዕቆብ አስገባት፤ ያዕቆብም ወደ እርስዋ ገባ። ላባም ለልጁ ልያ አገልጋዪቱን ዘለፋን አገልጋይ ትሆናት ዘንድ ሰጣት። በነጋም ጊዜ እነሆ ልያ ነበረች፤ ያዕቆብም ላባን፥ “ምነው እንደዚህ አደረግህብኝ? ያገለገልሁህ ስለ ራሔል አልነበረምን? ለምን አታለልኸኝ?” አለው። ላባም እንዲህ አለ፥ “በሀገራችን ታላቂቱ ሳለች፥ ታናሺቱን እንሰጥ ዘንድ ወግ አይደለም፤ ለዚችም ሰባት ዓመት ፈጽም፤ ሌላ ሰባት ዓመት ደግሞ እኔን ስለምታገለግለኝ አገልግሎት እርስዋን ደግሞ እሰጥሃለሁ።” ያዕቆብም እንዲህ አደረገ፤ ለዚችም ሰባት ዓመት ፈጸመ፤ ልጁን ራሔልንም ለእርሱ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው። ላባም ለልጁ ለራሔል አገልጋዪቱን ባላን አገልጋይ ትሆናት ዘንድ ሰጣት። ያዕቆብም ወደ ራሔል ደግሞ ገባ። ራሔልንም ከልያ ይልቅ ወደዳት፤ ሌላ ሰባት ዓመትም ተገዛለት። እግዚአብሔርም ልያ የተጠላች መሆንዋን በአየ ጊዜ ማኅፀንዋን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች። ልያም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅንም ወለደች፥ ስሙንም ሮቤል ብላ ጠራችው፥ “እግዚአብሔር መዋረዴን አይቶአልና፥ እንግዲህስ ወዲህ ባሌ ይወድደኛል” ስትል። ልያም ዳግመኛ ፀነሰች፤ ሁለተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደችለት፤ “እኔ እንደ ተጠላሁ እግዚአብሔር ስለ ሰማ ይህን ጨመረልኝ” አለች፤ ስሙንም ስምዖን ብላ ጠራችው ። ደግሞም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ “ከእንግዲህ ወዲህስ ባሌ ወደ እኔ ይጠጋል፤ ሦስት ወንዶች ልጆችን ወልጄለታለሁና” አለች፤ ስለዚህም ስሙን ሌዊ ብላ ጠራችው። ደግሞም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ በዚህም ጊዜ “እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” አለች፤ ስለዚህም ስሙን ይሁዳ ብላ ጠራችው። መውለድንም አቆመች።
ኦሪት ዘፍጥረት 29 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 29:14-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos