ከዚህም ነገር በኋላ የእግዚአብሔር ቃል በራእይ ወደ አብራም መጣ፤ እንዲህ ሲል፥ “አብራም ሆይ፥ አትፍራ፤ እኔ ጋሻ እሆንሃለሁ፤ ዋጋህም በእኔ ዘንድ እጅግ ብዙ ነው።” አብራምም፥ “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ ምን ትሰጠኛለህ? እነሆ፥ ልጅ ሳልወልድ እሞታለሁ፤ የቤቴም ወራሽ ከዘመዴ ወገን የሚሆን የደማስቆ ሰው የማሴቅ ልጅ ይህ ኢያውብር ነው” አለ። አብራምም፥ “ለእኔ ዘር አልሰጠኸኝም፤ የዘመዴ ልጅ እርሱ ይወርሰኛል” አለ። ያን ጊዜም የአግዚአብሔር ቃል ወደ አብራም እንዲህ ሲል መጣ፤ “እርሱ አይወርስህም፤ ነገር ግን ከአብራክህ የሚወጣው እርሱ ይወርስሃል።” ወደ ሜዳም አወጣውና “ወደ ላይ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ ልትቈጥራቸው ትችል እንደሆነ ከዋክብትን ቍጠራቸው። ዘርህም እንደዚሁ ነው” አለው። አብራምም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት። “ይህችን ምድር ትወርሳት ዘንድ እንድሰጥህ ከከለዳውያን ምድር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ” አለው። “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደምወርሳት በምን አውቃለሁ?” አለው። እርሱም አለው፥ “የሦስት ዓመት ላም፥ የሦስት ዓመት ፍየልም፥ የሦስት ዓመት በግም፥ ዋኖስም፥ ርግብም አምጣ፤ እኒህንም ሁሉ አምጥተህ ከሁለት ከሁለት ቍረጣቸው፤ ወፎችን ግን አትቍረጣቸው።” እንዲሁም እነዚህን ሁሉ ወሰደለት፤ በየሁለትም ከፈላቸው፤ የተከፈሉትንም በየወገኑ ትይዩ አደረጋቸው፤ ወፎችን ግን አልቈረጣቸውም። አሞራዎችም በተቈረጠው ሥጋቸው ላይ ወረዱ፤ አብራምም በእነርሱ ዘንድ ተቀምጦ አባረራቸው።
ኦሪት ዘፍጥረት 15 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 15:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች