ኦሪት ዘፍጥረት 15:1-11

ኦሪት ዘፍጥረት 15:1-11 አማ05

ከዚህ በኋላ አብራም ራእይ አየ፤ እግዚአብሔርም “አብራም፥ አትፍራ፤ እንደ ጋሻ ሆኜ ከአደጋ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ታላቅ በረከትም እሰጥሃለሁ” ሲል ሰማው። አብራምም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ጌታ አምላክ ሆይ፥ ምንም ልጅ ስለሌለኝ የምትሰጠኝ በረከት ምን ያደርግልኛል? ሀብቴን የሚወርሰው የደማስቆ ሰው የሆነው ኤሊዔዘር ነው። ምንም ዘር ስላልሰጠኸኝ ሀብቴን የሚወርሰው በቤቴ የተወለደ አገልጋይ ነው።” ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል “ይህ ኤሊዔዘር የተባለው አገልጋይ የአንተን ሀብት አይወርስም፤ ከአንተ የሚወለደው ልጅ ወራሽህ ይሆናል” ብሎ ሲነግረው ሰማ። ቀጥሎም እግዚአብሔር አብራምን ወደ ውጪ አወጣውና “ወደ ሰማይ ተመልከት፤ ከዋክብትን መቊጠር ትችል እንደሆን ሞክር፤ እንግዲህ የአንተም ዘሮች እንደዚህ ይበዛሉ” አለው። አብራም በእግዚአብሔር አመነ፤ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት። ደግሞም እግዚአብሔር አብራምን “ይህችን አገር በውርስ ለአንተ እንድሰጥህ ዑር ከምትባለው ከከለዳውያን ምድር ያወጣሁህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ” አለው። አብራም ግን “ጌታ አምላክ ሆይ፥ ይህች ምድር የእኔ እንደምትሆን እንዴት ለማወቅ እችላለሁ?” ሲል ጠየቀ። እግዚአብሔርም “ሦስት፥ ሦስት ዓመት የሆናቸው አንድ ጊደር፥ አንድ ፍየልና፥ አንድ በግ፥ እንዲሁም ዋኖስና ርግብ አምጣልኝ” አለው። አብራምም እነዚህን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር አምጥቶ እያንዳንዱን እየቈረጠ በሁለት ከፈለው፤ የተከፈሉትንም ትይዩ አድርጎ በሁለት መስመር አስቀመጣቸው። ወፎቹን ግን ቈርጦ አልከፈላቸውም። አሞራዎች የተቈራረጠውን ሥጋ ለመብላት ሲመጡ አብራም አባረራቸው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}