እግዚአብሔርም፥ “በውኃው መካከል ጠፈር ይሁን፤ በውኃና በውኃ መካከልም ይለይ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፤ ከጠፈር በላይና ከጠፈር በታች ያሉትንም ውኆች ለየ። እግዚአብሔር ያን ጠፈር “ሰማይ” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። ማታም ሆነ፤ ጥዋትም ሆነ፤ ሁለተኛም ቀን ሆነ። እግዚአብሔርም ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ፤ እንዲሁም ሆነ። ከሰማይ በታች ያለው ውኃም በመጠራቀሚያው ተሰበሰበ፤ የብሱም ተገለጠ። እግዚአብሔርም የብሱን “ምድር” ብሎ ጠራው፤ የውኃ መጠራቀሚያውንም “ባሕር” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም “ምድር በየዘሩ፥ በየወገኑና በየመልኩ ዘር የሚሰጥ ቡቃያን፥ በምድርም ላይ በየወገኑ ዘሩ በውስጡ የሚገኘውንና ፍሬ የሚያፈራውን ዛፍ ታብቅል” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። ምድርም በየዘሩ፥ በየወገኑና በየመልኩ የሚዘራ ቡቃያን፥ በምድር ላይ በየወገኑ ዘሩ በውስጡ የሚገኘውንና ፍሬ የሚያፈራውን ዛፍ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። ማታም ሆነ፤ ጥዋትም ሆነ። ሦስተኛም ቀን ሆነ። እግዚአብሔርም አለ፥ “በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ፥ በቀንና በሌሊትም ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች፥ ለዘመናት፥ ለዕለታት፥ ለዓመታትም ይሁኑ። በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ፥ በሰማይ ጠፈር ለማብራት ይሁኑ፤” እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቅ ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን ቀንን እንዲመግብ፥ ትንሹ ብርሃንም ከከዋክብት ጋር ሌሊትን እንዲመግብ አደረገ። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፤ መዓልትንና ሌሊትንም እንዲመግቡ፥ በመዓልትና በሌሊትም መካከል እንዲለዩ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። ማታም ሆነ፤ ጥዋትም ሆነ፤ አራተኛም ቀን ሆነ። እግዚአብሔርም አለ፥ “ውኃ የሕይወት እስትንፋስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾችና በምድር ላይ ከሰማይ በታች የሚበርሩ አዕዋፍን ታስገኝ፥” እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም ታላላቅ አንበሪዎችን፥ ውኃ ያስገኘውን ተንቀሳቃሽ ሕያው ፍጥረትን ሁሉ በየወገኑ፥ የሚበርሩ አዕዋፍንም ሁሉ በየወገናቸው ፈጠረ። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ባረካቸው፥ “ብዙ፤ ተባዙም፤ የባሕርንም ውኃ ሙሉአት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ።” ማታም ሆነ፤ ጥዋትም ሆነ፤ አምስተኛም ቀን ሆነ። እግዚአብሔርም አለ፥ “ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፥ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን፥ የምድር አራዊትንም እንደየወገኑ ታውጣ፥” እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም የምድር አራዊትን እንደየወገኑ፥ እንስሳትንም እንደየወገኑ፥ በምድር የሚንቀሳቀሰውንም ሁሉ እንደየወገኑ አደረገ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደሆነ አየ።
ኦሪት ዘፍጥረት 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 1:6-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች