መጽሐፈ ዕዝራ 3
3
የሥርዐተ አምልኮት እንደ ገና መጀመር
1ሰባተኛውም ወር በደረሰ ጊዜ፥ የእስራኤልም ልጆች በከተሞቻቸው ሳሉ፥ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 2የኢዮሴዴቅም ልጅ ኢያሱ፥ ወንድሞቹም ካህናቱ፥ የሰላትያልም ልጅ ዘሩባቤል፥ ወንድሞቹም ተነሥተው በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ ሠሩ። 3በሀገሩም ካሉት አሕዛብ ፈርተው ነበርና መሠዊያውን በስፍራው ላይ አስቀመጡት፤ በጥዋትና በማታም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡበት። 4እንደ ተጻፈውም የዳስ በዓል አደረጉ፤ እንደ ሥርዐቱም ለየዕለቱ የተገባውን የየዕለቱን የሚቃጠል መሥዋዕት በቍጥር አቀረቡ። 5ከዚያም በኋላ ዘወትር የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የመባቻውንም መሥዋዕት፥ የተቀደሱትንም የእግዚአብሔር በዓላት ሁሉ መሥዋዕት፥ ሰውም ሁሉ ለእግዚአብሔር በፈቃድ የሰጠውን ቍርባን አቀረቡ። 6በሰባተኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ፤ የእግዚአብሔር መቅደስ ግን ገና አልተመሠረተም ነበር። 7ለጠራቢዎችና ለአናጢዎችም ብር#ዕብ. “ገንዘብ” ይላል። ሰጡ፤ የፋርስም ንጉሥ ቂሮስ እንደ ፈቀደላቸው የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ በባሕር ወደ ኢዮጴ ያመጡ ዘንድ ለሲዶናና ለጢሮስ ሰዎች መብልና መጠጥ፥ ዘይትም ሰጡ።
8በኢየሩሳሌምም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጡ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛውም ወር የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፥ የኢዮሴዴቅም ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ወንድሞቻቸው ካህናትና ሌዋውያን፥ ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌምም የተመለሱት ሁሉ ጀመሩ፤ ሌዋውያንንም ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ እንዲያሠሩት ሾሙአቸው። 9ኢያሱም፥ ልጆቹም ተሾሙ፤ ወንድሞቹም፥ የይሁዳም ልጆች ቀደምያልና ልጆቹ፥ የኢንሐዳድም ልጆች፥ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን ያሠሩ ዘንድ በአንድነት ቆሙ። 10አናጢዎቹም የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሠሩ ዘንድ መሠረት በጣሉ ጊዜ ካህናቱ ልብሳቸውን ለብሰው መለከቱን ይዘው፥ የአሳፍም ልጆች ሌዋውያን ጸናጽል ይዘው እንደ እስራኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት ሥርዐት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ። 11ደግሞ፥ “ቸር ነውና፥ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና” እያሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ እርስ በርሳቸው ያስተዛዝሉ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ቤት በተመሠረተ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩ በታላቅ ድምፅ ዘመሩ። 12የፊተኛውን ቤት ያዩ ሽማግሌዎች የሆኑ ብዙ ካህናትና ሌዋውያን፥ የአባቶችም ቤቶች አለቆች ግን ይህ መቅደስ በፊታቸው በተመሠረተ ጊዜ በታላቅ ድምፅ ያለቅሱ ነበር፤ ብዙ ሰዎችም እየዘመሩ በደስታ ይጮኹ ነበር፤ 13ደስ ብሎአቸው የሚጮኹትን ድምፅ ከሕዝቡ ልቅሶ ድምፅ መለየት የሚችል አልነበረም፥ ሕዝቡ በታላቅ ድምፅ ይጮኽ ነበርና ድምፁም ከሩቅ ይሰማ ነበርና።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ 3: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ