ኦሪት ዘፀአት 39
39
የልብሰ ተክህኖ አሠራር
(ዘፀ. 28፥1-14)
1የቀረውም የመባ ወርቅ በእግዚአብሔር ፊት ይሠሩበት ዘንድ ንዋየ ቅድሳት ሆኖ ተሠራ። ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም ለመቅደሱ አገልግሎት ልብሶችን ሠሩ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለአሮን የተቀደሰውን ልብስ ሠሩ። 2ልብሰ እንግድዓውንም ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይ ግምጃም፥ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም ሠሩ። 3ወርቁንም ቀጥቅጠው እንደ ቅጠል ስስ አደረጉት፤ እንደ ፈትልም ቈረጡት። ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ ሰማያዊ፥ ሐምራዊም፥ ቀይ ግምጃም፥ የተፈተለም ጥሩ በፍታ፥ ከእርሱ ጠለፉ። 4ሁለቱ ወገን እንዲጋጠሙ፥ በሁለት ጫንቃዎች ላይ የሚጋጠም ልብሰ መትከፍ ሠሩ። 5እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው እርስዋን ከወርቅ፥ ከሰማያዊና ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃም፥ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም እንደ ሠሩ የልብሰ መትከፉን ቋድ ሠሩ።
6በወርቅ ፈርጥ የተያዙ የመረግድ ድንጋዮች ሠርተው እንደ ማኅተም ቅርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም ቀረጹባቸው። 7ለእስራኤልም ልጆች የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው፥ በልብሰ መትከፉ ጫንቃዎች ላይ አደረጓቸው።
የልብሰ እንግድዓ አሠራር
(ዘፀ. 28፥15-30)
8ልብሰ እንግድዓውን ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ፥ እንደ ልብሰ መትከፉ አሠራር ከወርቅና ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈትለም ከጥሩ በፍታ አደረጉ። 9አራት ማዕዘንም ነበረ፤ ልብሰ እንግድዓውም ድርብ ነበር፤ ርዝመቱ ስንዝር፥ ወርዱም ስንዝር፥ ድርብም ነበረ። 10ዕንቍዎቹንም በአራት ተራ አደረጉበት፤ በፊተኛውም ተራ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ መረግድ፤ 11በሁለተኛውም ተራ በሉር፥ ሰንፔር፥ ኢያሰጲድ፤ 12በሦስተኛውም ተራ ለግርዮን፥አካጥስ፥#ዕብ. “ያክንት ኬልቄዶን” ይላል። አሜቴስጢኖስ፤ 13በአራተኛውም ተራ ወርቃማ ድንጋይ፥ ቢረሌ፥ ሶም፤ ዙሪያውም በወርቅ ፈርጥ ተደረገ። 14የዕንቍዎችም ድንጋዮች እንደ ዐሥራ ሁለቱ እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ነበሩ፤ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ተቀረጹ፤ ስለ ዐሥራ ሁለቱም ነገዶች ነበሩ። 15ለልብሰ እንግድዓውም የተጐነጐኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገው ከጥሩ ወርቅ ሠሩ። 16ሁለትም የወርቅ ፈርጦች፥ ሁለትም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ ሁለቱንም የወርቅ ቀለበቶች በልብሰ እንግድዓው በሁለቱ ወገን አደረጉ። 17ሁለቱንም የተጐነጐኑትን የወርቅ ድሪዎች በልብሰ እንግድዓው በሁለቱ ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች አገቡ። 18የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተው በልብሰ መትከፉ ጫንቃዎች ላይ ፊት ለፊት አደረጓቸው። 19ሁለቱንም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ እነርሱንም ከልብሰ መትከፉ ፊት ለፊት ባለው በልብሰ እንግድዓው በሁለቱ ጫፎች ላይ አደረጓቸው። 20ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ በመደረቢያው ፊት፥ ከጫንቃዎች በታች፥ በብልሃት ከተጠለፈ ከመደረቢያው ቋድ በላይ፥ በመያዣው አጠገብ አደረጓቸው።#ምዕ. 39 ቍ. 20 በግእዙ የለም። 21ልብሰ እንግድዓው በብልሃት ከተጠለፈው ከመደረቢያው ቋድ በላይ እንዲሆን፥ ከመደረቢያው እንዳይለይ ልብሰ እንግድዓውን ከቀለበቶቹ ጋር ወደ መደረቢያው ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል አሰሩት።
የልዩ ልዩ አልባሳተ ክህነት አሠራር
(ዘፀ. 28፥31-43)
22እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ የመደረቢያውን ቀሚስ ሞላውን በሸማኔ ሥራ ሰማያዊ አድርጎ ሠራው። 23በቀሚሱም መካከል አንገትጌ ነበረ፤ እንዳይቀደድም በአንገትጌው ዙሪያ በአንድነት የተያያዘ ጥልፍ ነበረ። 24በቀሚሱም ታችኛ ዘርፍ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይ ግምጃም፥ ከተፈተለ በፍታም የአበቡ ሮማኖችን አደረጉ። 25ከጥሩ ወርቅም ሻኵራዎችን ሠሩ፤ ሻኵራዎቹንም ከሮማኖች መካከል በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ አደረጉ። 26በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ ሻኵራንና ሮማንን፥ ሻኩራንና ሮማንን እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለማገልገል አደረጉ።
27እንደ ሸማኔ ሥራ ከጥሩ በፍታ ለአሮንና ለልጆቹ እጀ ጠባቦችን፥ ከጥሩ በፍታም አክሊልን፥ 28ከጥሩ በፍታም መልካሞቹን ቆቦች፥ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም የእግር ሱሪዎችን፥ 29ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊም፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይም ግምጃ በጥልፍ አሠራር የተሠራ መታጠቂያውን እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።
30ከጥሩ ወርቅ የተለየ የወርቅ ቅጠል ሠሩ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገው፥ “ቅድስና ለእግዚአብሔር” የሚል ጻፉበት። 31እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው፥ በአክሊሉ ላይ ያንጠለጥሉት ዘንድ ሰማያዊውን ፈትል አሰሩበት።
የድንኳኑ ሥራ ፍጻሜ
(ዘፀ. 35፥10-19)
32እንዲሁም የምስክሩ ድንኳን ሥራ ሁሉ ተፈጸመ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ የእስራኤል ልጆች አደረጉ፤ እንዲሁ አደረጉ። 33ድንኳኑንም፥ መደረቢያውንም፥ ዕቃውንም ሁሉ ወደ ሙሴ አመጡ፤ መያዣዎቹን፥ ሳንቆቹን፥ መወርወሪያዎቹን፥ ምሰሶዎቹን፥ እግሮቹንም፤ 34ከቀይ አውራ በግ ቍርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ ከአቆስጣ ቁርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ የሚሸፍነውንም መጋረጃ፥ 35የምስክሩንም ታቦት፥ መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም፤ 36ገበታውንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ ኅብስተ ገጹንም፤ 37ጥሩውንም መቅረዝ፥ መብራቶቹንም፥ በተራ የሚሆኑትንም ቀንዲሎች፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመብራቱንም ዘይት፤ 38የወርቁንም መሠዊያ፥ የቅብዐቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ የድንኳኑንም ደጃፍ መጋረጃ፤ 39የናሱንም መሠዊያ፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንም፥ መቀመጫውንም፤ 40የአደባባዩንም መጋረጆች፥ ምሰሶዎቹንም፥ እግሮቹንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቹንም፥ ካስማዎቹንም፥ ለምስክሩ ድንኳን ማገልገያ የሚሆኑትን ዕቃዎች ሁሉ፤ 41በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነትም ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮንን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች አመጡ። 42እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ ሁሉ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ሥራውን ሁሉ ሠሩ። 43ሙሴም ሥራውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፥ አድርገውት ነበር፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንዲሁ አድርገውት ነበር፤ ሙሴም ባረካቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 39: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ