እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደ ሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ፥ ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ፤ ሕዝቡም ወጥተው ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይሰብስቡ። እንዲህም ይሆናል፤ በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፤ ዕለት ዕለትም ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን” አለው። ሙሴና አሮንም ለእስራኤል ልጆች ሁሉ፥ “እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር እንደ አወጣችሁ ማታ ታውቃላችሁ፤ የእግዚአብሔርንም ክብር ጥዋት ታያላችሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ያንጐራጐራችሁትን ሰምቶአልና፤ በእኛም ላይ የምታንጐራጕሩ እኛ ምንድን ነን?” አሉ። ሙሴም፥ “እግዚአብሔር ያንጐራጐራችሁበትን ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና በመሸ ጊዜ ትበሉ ዘንድ ሥጋን፥ በማለዳም ትጠግቡ ዘንድ እንጀራን እግዚአብሔር ይሰጣችኋል፤ እኛም ምንድን ነን? ማንጐራጐራችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ በእኛ ላይ አይደለም” አለ። ሙሴም አሮንን፥ “ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ፦ ‘ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ’ በል” አለው። አሮንም ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አቀኑ፤ እነሆም፥ የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ታየ። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “የእስራኤልን ልጆች ማንጐራጐር ሰማሁ፦ ማታ ሥጋን ትበላላችሁ፤ ማለዳም እንጀራን ትጠግባላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው።” እንዲህም ሆነ፤ በመሸ ጊዜ ድርጭቶች መጡ፤ ሰፈሩንም ሸፈኑት፤ በማለዳም በሰፈሩ ዙሪያ ጠል ወድቆ ነበር። የወደቀው ጠል በአለፈ ጊዜ፥ እነሆ፥ በመሬት ላይ እንደ ውርጭ ነጭ ሆኖ ድንብላል የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ ታየ። የእስራኤልም ልጆች በአዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው፥ “ይህ ምንድን ነው?” ተባባሉ። ያ ምን እንደሆነ አላወቁምና። ሙሴም አላቸው፥ “ትበሉ ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ይህ ነው። ታደርጉት ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ እያንዳንዱ ሰው ለቤተ ሰቡ ለእያንዳንዱ አንድ ጎሞር ይሰብስብ፤ እንደ ቤተ ሰቡ ቍጥር ለእያንዳንዱ በድንኳኑ አብረውት ከሚኖሩት ጋር ይሰብስብ።” የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ አንዱ አብዝቶ፥ አንዱም አሳንሶ ሰበሰበ። በጎሞርም በሰፈሩት ጊዜ እጅግ ለሰበሰበ አልተረፈውም፤ ጥቂትም ለሰበሰበ አልጐደለበትም፤ ሁሉም እያንዳንዱ ሰው ለየቤቱ ሰበሰበ። ሙሴም፥ “የእስራኤልን ልጆች ማንም ከእርሱ አንዳች ለነገ አያስቀር” አላቸው። ነገር ግን ሙሴን አልሰሙትም፤ አንዳንድ ሰዎችም ከእርሱ ለነገ አስቀሩ፤ እርሱም ተላ፤ ሸተተም፤ ሙሴም ተቈጣቸው።
ኦሪት ዘፀአት 16 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 16:4-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች