በዚያ ጊዜም ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤ እንዲህም ብለው ተናገሩ፦ “ለእግዚአብሔር እንዘምራለን፤ በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ብሎአልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። እኔን ለማዳን ረዳትና ሰዋሪ ሆነኝ፤ ይህ አምላኬ ነው፤ አመሰግነውማለሁ፤ የአባቴ አምላክ ነው፤ ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ። እግዚአብሔር ጦርነትን ያጠፋል፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው፤ የፈርዖንን ሰረገሎች፥ ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው። በሦስት የተከፈሉ ፈረሰኞችም በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ። ማዕበልም ከደናቸው፤ ወደ ባሕር ጥልቀት እንደ ድንጋይ ሰጠሙ። አቤቱ፥ ቀኝህ በኀይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቶችን አደቀቀ። በክብርህም ብዛት ጠላቶችህን አጠፋህ፤ ቍጣህን ሰደድህ፤ እንደ ገለባም በላቸው። በቍጣህ እስትንፋስ ውኃው ቆመ፤ ውኃዎች እንደ ግደግዳ ቆሙ፤ ሞገዱም በባሕር መካከል ረጋ። ጠላትም፦ ‘አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፤ ምርኮም እካፈላለሁ፤ ነፍሴንም አጠግባታለሁ፤ በሰይፌም እገድላለሁ፤ በእጄም እገዛለሁ’ አለ። ነፋስህን ላክህ፤ ባሕርም ከደናቸው፤ በብዙ ውኆች ውስጥ እንደ አረር ሰጠሙ። አቤቱ፦ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማን ነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማን ነው? በምስጋና የተደነቅህ ነህ፤ ድንቅንም የምታደርግ ነህ፤ ቀኝህን ዘረጋህ፤ ምድርም ዋጠቻቸው። በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኀይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ ጠራሃቸው። አሕዛብ ሰሙ፤ ተቈጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ምጥ ያዛቸው። ያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ሸሹ፤ የሞዓብንም አለቆች መንቀጠቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ። ፍርሀትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ የክንድህ ብርታትም ከድንጋይ ይልቅ ጸና፤ አቤቱ፥ ሕዝብህ እስኪያልፉ ድረስ፥ የተቤዠሃቸው እኒህ ሕዝብህ እስኪያልፉ ድረስ፤ አቤቱ፥ አንተ ታስገባቸዋለህ፤ በመመስገኛህ ተራራም ትተክላቸዋለህ፤ አቤቱ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ፥ አቤቱ፥ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ፤ እግዚአብሔር ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለምም ይነግሣል። “የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹና ከፈረሰኞቹ ጋር ወደ ባሕር ገቡ፤ እግዚአብሔርም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በየብስ አለፉ፤ ውኃውም ለእነርሱ በቀኝ እንደ ግድግዳ፥ በግራም እንደ ግድግዳ ሆነላቸው።” የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዝማሬ በኋላዋ ወጡ። ማርያምም አስቀድማ ለእግዚአብሔር እንዘምር አለች፥ “ለእግዚአብሔር እንዘምር በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ብሎአልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጥሎአልና።” ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ከኤርትራ ባሕር አውጥቶ ወደ ሱር ምድረ በዳ ወሰዳቸው። በምድረ በዳም ሦስት ቀን ተጓዙ፤ ይጠጡም ዘንድ ውኃ አላገኙም። ወደ ማራም በመጡ ጊዜ ከማራ ውኃ ሊጠጡ አልቻሉም፤ ውኃው መራራ ነበርና፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም “መሪር” ተብሎ ተጠራ። ሕዝቡም፥ “ምን እንጠጣለን?” ብለው በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ዕንጨትን አሳየው፤ በውኃውም ላይ ጣለው፤ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዐትንና ፍርድን አደረገላቸው፤ በዚያም ፈተናቸው። እርሱም፥ “አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥ በፊቱም መልካምን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና” አለ። እነርሱም ወደ ኤሎም መጡ፤ በዚያም ዐሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ነበሩባት፤ በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ።
ኦሪት ዘፀአት 15 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 15:1-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos