ዘፀአት 15:1-27
ዘፀአት 15:1-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያ ጊዜም ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤ እንዲህም ብለው ተናገሩ፦ “ለእግዚአብሔር እንዘምራለን፤ በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ብሎአልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። እኔን ለማዳን ረዳትና ሰዋሪ ሆነኝ፤ ይህ አምላኬ ነው፤ አመሰግነውማለሁ፤ የአባቴ አምላክ ነው፤ ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ። እግዚአብሔር ጦርነትን ያጠፋል፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው፤ የፈርዖንን ሰረገሎች፥ ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው። በሦስት የተከፈሉ ፈረሰኞችም በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ። ማዕበልም ከደናቸው፤ ወደ ባሕር ጥልቀት እንደ ድንጋይ ሰጠሙ። አቤቱ፥ ቀኝህ በኀይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቶችን አደቀቀ። በክብርህም ብዛት ጠላቶችህን አጠፋህ፤ ቍጣህን ሰደድህ፤ እንደ ገለባም በላቸው። በቍጣህ እስትንፋስ ውኃው ቆመ፤ ውኃዎች እንደ ግደግዳ ቆሙ፤ ሞገዱም በባሕር መካከል ረጋ። ጠላትም፦ ‘አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፤ ምርኮም እካፈላለሁ፤ ነፍሴንም አጠግባታለሁ፤ በሰይፌም እገድላለሁ፤ በእጄም እገዛለሁ’ አለ። ነፋስህን ላክህ፤ ባሕርም ከደናቸው፤ በብዙ ውኆች ውስጥ እንደ አረር ሰጠሙ። አቤቱ፦ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማን ነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማን ነው? በምስጋና የተደነቅህ ነህ፤ ድንቅንም የምታደርግ ነህ፤ ቀኝህን ዘረጋህ፤ ምድርም ዋጠቻቸው። በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኀይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ ጠራሃቸው። አሕዛብ ሰሙ፤ ተቈጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ምጥ ያዛቸው። ያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ሸሹ፤ የሞዓብንም አለቆች መንቀጠቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ። ፍርሀትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ የክንድህ ብርታትም ከድንጋይ ይልቅ ጸና፤ አቤቱ፥ ሕዝብህ እስኪያልፉ ድረስ፥ የተቤዠሃቸው እኒህ ሕዝብህ እስኪያልፉ ድረስ፤ አቤቱ፥ አንተ ታስገባቸዋለህ፤ በመመስገኛህ ተራራም ትተክላቸዋለህ፤ አቤቱ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ፥ አቤቱ፥ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ፤ እግዚአብሔር ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለምም ይነግሣል። “የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹና ከፈረሰኞቹ ጋር ወደ ባሕር ገቡ፤ እግዚአብሔርም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በየብስ አለፉ፤ ውኃውም ለእነርሱ በቀኝ እንደ ግድግዳ፥ በግራም እንደ ግድግዳ ሆነላቸው።” የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዝማሬ በኋላዋ ወጡ። ማርያምም አስቀድማ ለእግዚአብሔር እንዘምር አለች፥ “ለእግዚአብሔር እንዘምር በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ብሎአልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጥሎአልና።” ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ከኤርትራ ባሕር አውጥቶ ወደ ሱር ምድረ በዳ ወሰዳቸው። በምድረ በዳም ሦስት ቀን ተጓዙ፤ ይጠጡም ዘንድ ውኃ አላገኙም። ወደ ማራም በመጡ ጊዜ ከማራ ውኃ ሊጠጡ አልቻሉም፤ ውኃው መራራ ነበርና፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም “መሪር” ተብሎ ተጠራ። ሕዝቡም፥ “ምን እንጠጣለን?” ብለው በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ዕንጨትን አሳየው፤ በውኃውም ላይ ጣለው፤ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዐትንና ፍርድን አደረገላቸው፤ በዚያም ፈተናቸው። እርሱም፥ “አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥ በፊቱም መልካምን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና” አለ። እነርሱም ወደ ኤሎም መጡ፤ በዚያም ዐሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ነበሩባት፤ በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ።
ዘፀአት 15:1-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ሙሴና እስራኤላውያን ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘመሩ፤ “ከፍ ከፍ ብሎ ከብሯልና፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን፣ በባሕር ውስጥ ጥሏልና። “እግዚአብሔር (ያህ) ብርታቴና ዝማሬዬ ነው፤ ድነቴም ሆነልኝ፤ እርሱ አምላኬ ነው፤ አመሰግነዋለሁ፤ የአባቴ አምላክ (ኤሎሂም) ነው፤ እኔም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። እግዚአብሔር (ያህዌ) ተዋጊ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር (ያህዌ) ነው። የፈርዖንን ሠረገሎችና ሰራዊት፣ ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤ ምርጥ የሆኑት የፈርዖን ሹማምት፣ ቀይ ባሕር ውስጥ ሰጠሙ። ቀላያትንም ለበሱ፤ እንደ ድንጋይ ወደ ጥልቁ ወረዱ። አቤቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ቀኝ እጅህ በግርማ ከበረ፤ አቤቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ቀኝ እጅህ ጠላትን አደቀቀ። “በግርማህ ታላቅነት፣ የተቃወሙህን ጣልኻቸው፤ ቍጣህን ሰደድህ፤ እንደ ገለባም በላቸው። በአፍንጫህ እስትንፋስ፣ ውሆች ተቈለሉ፤ ፈሳሾችም እንደ ግድግዳ ቆሙ፤ የጥልቁ ውሃ ባሕሩ ውስጥ ረጋ። ጠላት፣ ‘አሳድዳቸዋለሁ፤ እማርካቸዋለሁ፤ ምርኮን እካፈላለሁ፤ ነፍሴ በእነርሱ ትጠግባለች፤ ሰይፌን እመዝዛለሁ፤ እጄም ትደመስሳቸዋለች አለ።’ አንተ ግን እስትንፋስህን አነፈስህ፤ ባሕርም ከደናቸው፤ በኀያላን ውሆች፣ እንደ ብረት ሰጠሙ። አቤቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ከአማልክት መካከል፣ እንደ አንተ ማን አለ? በቅድስናው የከበረ፣ በክብሩ የሚያስፈራ፣ ድንቆችን የሚያደርግ፣ እንደ አንተ ማን አለ? “ቀኝ እጅህን ዘረጋህ፤ ምድርም ዋጠቻቸው። በማይለወጠው ፍቅርህ፣ የተቤዥሃቸው ሕዝብህን ትመራለህ፤ እነርሱን በብርታትህ፣ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ ትመራቸዋለህ። አሕዛብ ይሰማሉ፤ ይንቀጠቀጡማል፤ የፍልስጥኤምን ሕዝብ ሥቃይ ይይዛቸዋል። የኤዶምም አለቆች ይርዳሉ፤ የሞአብ አለቆች በእንቅጥቃጤ ይያዛሉ፤ የከነዓን ሕዝብ ይቀልጣሉ። አቤቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ሕዝብህ እስከሚያልፉ ድረስ፣ የተቤዠኻቸው ሕዝብህ እስኪያልፉ ድረስ፣ ድንጋጤና ሽብር በእነርሱ ላይ ይመጣል፤ በክንድህ ብርታት፣ እንደ ድንጋይ የማይንቀሳቀሱ ይሆናሉ። እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ማደሪያህ እንዲሆን በሠራኸው ስፍራ፣ ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ እጆችህ በሠሩት መቅደስ፣ በርስትህ ተራራ ላይ፣ ታመጣቸዋለህ፤ ትተክላቸዋለህም። “እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።” የፈርዖን ፈረሶች፣ ሠረገሎቹና ፈረሰኞቹ ወደ ባሕሩ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) የባሕሩን ውሃ በላያቸው ላይ መለሰባቸው፤ እስራኤላውያን ግን በባሕሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ተሻገሩ። ከዚያም የአሮን እኅት ነቢዪቱ ማርያም ከበሮዋን አንሥታ ያዘች፤ የቀሩትም ሴቶች ሁሉ ከበሮ ይዘው እያሸበሸቡ ተከተሏት። ማርያምም፣ “ፈረሱንና ፈረሰኛውን፣ በባሕር ውስጥ ጥሏል፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘምሩ፤ እጅግ ከፍ ከፍ ብሏልና” እያለች ዘመረችላቸው። ከዚያም ሙሴ እስራኤልን ከቀይ ባሕር እየመራቸው ወደ ሱር ምድረ በዳ ሄዱ፤ ለሦስት ቀናት ውሃ ሳያገኙም በምድረ በዳ ተጓዙ። ማራ በደረሱ ጊዜ ውሃው መራራ ስለ ነበር ሊጠጡት አልቻሉም፤ ቦታው ማራ ተብሎ የተጠራውም ከዚህ የተነሣ ነው። ሕዝቡም በሙሴ ላይ በማጕረምረም፣ “ምን እንጠጣ?” አሉ። ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) አንዲት ዛፍ አሳየው፤ ዕንጨቷንም ወደ ውሃው ጣላት፤ ውሃውም ጣፋጭ ሆነ። በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሕግና ሥርዐት አበጀላቸው፤ በዚያም ስፍራ ፈተናቸው። እርሱም አለ፤ “የአምላካችሁን እግዚአብሔር (ያህዌ) ድምፅ በጥንቃቄ ብትሰሙ፣ በፊቱም ትክክል የሆነውን ብትፈጽሙ፣ ትእዛዞቹን ልብ ብትሉና ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቁ፣ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁባቸውን ማንኛውንም ዐይነት በሽታ በእናንተ ላይ አላመጣም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝና።” ከዚያም ዐሥራ ሁለት ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ወዳሉበት ወደ ኤሊም መጡ፤ እነርሱም በውሃው አጠገብ በዚያ ሰፈሩ።
ዘፀአት 15:1-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤ እንዲህም ብለው ተናገሩ፤ “በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ጉልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፤ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፤ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ። እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው፤ የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው፤ የተመረጡት ሦስተኞች በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ። ቀላያትም ከደኑአቸው፤ ወደ ባሕር ጥልቀት እንደ ድንጋይ ሰጠሙ። አቤቱ፥ ቀኝህ በኃይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ። በክብርህም ብዛት የተነሡብህን አጠፋህ፤ ቍጣህን ሰድደህ፤ እንደ ገለባም በላቸው። በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፤ ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤ ሞገዱም በባሕር ውስጥ ረጋ። ጠላትም፥ ‘አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፤ ምርኮም እካፈላለሁ፤ ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፤ እጄም ታጠፋቸዋለች’ አለ። ነፋስህን አነፈስህ፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረር ሰጠሙ። አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው። በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኃይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ አገባሃቸው። አሕዛብ ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ምጥ ያዛቸው። የዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ደነገጡ፤ የሞአብን ኃያላን መንቀጥቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ። አቤቱ፥ ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ የተቤዠኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ ፍርሃትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ በክንድህ ብርታት እንደ ድንጋይ ዝም አሉ። አቤቱ፥ አንተ ታስገባቸዋለህ፥ በርስትህ ተራራም ትተክላቸዋለህ፥ አቤቱ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ፥ አቤቱ፥ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ። እግዚአብሔር ለዘላለሙ እስከ ፍጻሜ ይነግሣል። የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹ ከፈረሰኞቹም ጋር ወደ ባሕር ገቡ፥ እግዚአብሔርም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በየብስ ሄዱ። የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ። ማርያምም እየዘመረች መለሰችላቸው፦ በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ሙሴም እስራኤልን ከኤርትራ ባሕር አስጓዘ፥ ወደ ሱርም ምድረ በዳ ወጡ፤ በምድረ በዳም ሦስት ቀን ሄዱ፥ ውኃም አላገኙም። ወደ ማራም በመጡ ጊዜ የማራ ውኃ መራራ ነበረና ሊጠጡ አልቻሉም፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም ማራ ተብሎ ተጠራ። ሕዝቡም፦ ምን እንጠጣለን? ብለው በሙሴ ላይ አንጎራጎሩ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም እንጨትን አሳየው፥ በውኃውም ላይ ጣለው፥ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤ እርሱም፦ አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና አለ። እነርሱም ወደ ኤሊም መጡ፥ በዚያም አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ነበሩባት፤ በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ።
ዘፀአት 15:1-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ሙሴና የእስራኤል ሕዝብ ከዚህ የሚከተለውን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፦ “ፈረሱንና ፈረሰኛውን ወደ ባሕር በመጣል፥ ክብር የተሞላው ድል ስለ ተጐናጸፈ፥ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ። እግዚአብሔር በመዝሙር የማመሰግነው መከላከያ ኀይሌ ነው፤ ከጠላት እጅ ያዳነኝ ታዳጊዬም እርሱ ነው፤ እርሱ አምላኬ ስለ ሆነ አመሰግነዋለሁ፤ የአባቴም አምላክ ስለ ሆነ፥ ስለ ገናናነቱ እዘምራለሁ። እግዚአብሔር ብርቱ ጦረኛ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው። “የንጉሡን ሠራዊት ከነሠረገላው ወደ ባሕር ጣለ፤ ምርጥ የሆኑት የጦር አዛዦች በቀይ ባሕር ውስጥ ሰጥመው ቀሩ። ጥልቁ ባሕር አሰጠማቸው፤ እንደ ድንጋይም አቈልቊለው ወደ ባሕሩ ጥልቀት ወረዱ። “አምላክ ሆይ፥ የቀኝ እጅህ ኀይል፥ ባለ ግርማ ነው፤ ጠላትን ሰባብሮ ይጥላል፤ ግርማ በተሞላው ድል አድራጊነትህ ጠላትህን ገለበጥህ፤ ቊጣህ እንደ እሳት ስለ ነደደ እንደ ገለባ በላቸው። በቊጣህ እስትንፋስ፥ ውሃው ወደ ላይ ተቈለለ፤ እንደ ግድግዳም ቀጥ ብሎ ቆመ፤ በጥልቅ ስፍራ ያለውም ውሃ፥ ረግቶ ጠጠረ። ‘ጠላትማ አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፤ ሀብታቸውንም እካፈላለሁ፤ የፈለግኹትንም እወስዳለሁ፤ ሰይፌንም መዝዤ አጠፋቸዋለሁ’ ብሎ ነበር፤ ነገር ግን አምላክ ሆይ፥ ከአንተ በተገኘው በአንድ ትንፋሽ ግብጻውያን ሁሉ ሰጠሙ፤ በጥልቅ ባሕር ውስጥ እንደ ተጣለ ብረት ሆነው ቀሩ። “አምላክ ሆይ፥ ከአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማን ነው? በቅድስናስ እንደ አንተ ያለ ባለግርማ ማን ነው? አንተ ያደረግሃቸውን ተአምራትና አስገራሚ ሥራዎች ሊያደርግ የሚችልስ ማን አለ? ቀኝ እጅህን በዘረጋህ ጊዜ ጠላቶቻችንን ምድር ዋጠቻቸው፤ በማይለወጥ ፍቅርህ ያዳንካቸውን ሕዝብ መራህ፤ በብርታትህም ወደ ተቀደሰችው ምድር እንዲገቡ አደረግህ፤ አሕዛብ ሁሉ ይህን ሰምተው በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፤ ፍልስጥኤማውያንም ተሸበሩ፤ የኤዶም መሪዎች ተስፋ ቈረጡ፤ የሞአብም ኀያላን ተንቀጠቀጡ፤ የከነዓንም ሕዝብ ወኔ ከዳቸው። አምላክ ሆይ፥ ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ የተቤዠኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ ፍርሀትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ በሥልጣንህ እንደ ድንጋይ ጸጥ አሉ። አምላክ ሆይ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ፥ ወገኖችህን አንተ ታስገባቸዋለህ፤ በርስትህ ተራራም ትተክላቸዋለህ። እግዚአብሔር ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይነግሣል። “እስራኤላውያን በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻገሩ፤ የፈርዖን ፈረሶች፥ ሠረገሎችና ፈረሰኞቹ ሁሉ ወደ ባሕር በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ውሃውን መለሰባቸው።” የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያም ከበሮዋን አነሣች፤ ሌሎችም ሴቶች ከበሮዎቻቸውን እየመቱና እየጨፈሩ ይከተሉአት ጀመር፤ ማርያምም፥ “ፈረሱንና ፈረሰኛውን ወደ ባሕር በመጣል ክብር የተመላ ድልን ስለ ተጐናጸፈ፥ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” እያለች ዘመረችላቸው። ከዚህ በኋላ ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ከቀይ ባሕር አሳልፎ ወደ ሱር በረሓ መራቸው፤ ሦስት ቀን ሙሉ በበረሓ ተጓዙ፤ ነገር ግን ምንም ውሃ አላገኙም። ከዚህ በኋላ ማራ ወደ ተባለ ስፍራ በደረሱ ጊዜ ውሃው መራራ ስለ ነበረ ሊጠጡት አልቻሉም፤ ማራ ተብሎ የተጠራበትም ምክንያት ይኸው ነበር። ሕዝቡም በሙሴ ላይ በማጒረምረም “እንግዲህ ምን ልንጠጣ ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ሙሴም በብርቱ ጩኸት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አንድ እንጨት አሳየው፤ እርሱንም ወስዶ በውሃው ላይ በጣለው ጊዜ፥ ውሃው ወደጣፋጭነት ተለወጠ። በዚያ ስፍራ እግዚአብሔር የሚተዳደሩበት ደንብና ሥርዓት ሰጣቸው፤ በዚያም ፈተናቸው። እንዲህም አላቸው፤ “በጥሞና ትእዛዞቼን ብታዳምጡና በፊቴ መልካም የሆነውን ነገር በታዛዥነት ብታደርጉ፥ ኅጎቼንም ሁሉ ብትጠበቁ፥ በግብጻውያን ላይ ካመጣሁባቸው በሽታዎች በአንዱ እንኳ አልቀጣችሁም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” ከዚህ በኋላ ወደ ኤሊም መጡ፤ በዚያም ስፍራ ዐሥራ ሁለት የውሃ ምንጮችና ሰባ የተምር ዛፎች ነበሩ፤ ሕዝቡም በዚያ ከውሃው አጠገብ ሰፈሩ።
ዘፀአት 15:1-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያን ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለጌታ ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ፦ “ለጌታ እዘምራለሁ በክብር ከፍ ከፍ ብሏልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ጌታ ኃይሌና መዝሙሬ ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነዋለሁም፥ የአባቴ አምላክ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። ጌታ ተዋጊ ነው፥ ስሙም ጌታ ነው፤ የፈርዖንን ሰረገሎችና ሠራዊቱን በባሕር ጣላቸው፤ የተመረጡት መኮንኖችም በቀይ ባሕር ሰጠሙ። ቀላያትም ከደኑአቸው፤ እንደ ድንጋይ ወደ ባሕር ጥልቀት ወረዱ። ቀኝህ ጌታ ሆይ፥ በኃይል ታላቅ ነው፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጌታ ሆይ፥ ጠላትን አደቀቀ። የግርማህ ታላቅነት አንተን በመቃወም የተነሱብህን ጣላቸው፤ ቁጣህን ሰደድህ፥ እንደ ገለባም በላቸው። በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፥ ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤ ጥልቁም በባሕር ልብ ውስጥ ረጋ። ጠላትም፦ አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ በእነርሱም ፍላጎቴ ይሞላል፥ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች አለ። ትንፋሽህን እፍ አልክባቸው፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ ብረት ሰጠሙ። ከአማልክት መካከል ጌታ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በቅድስና ባለግርማ፥ በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው። በታማኝ ኪዳንህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራሃቸው፤ በኃይልህ ወደ ቅድስናህ ማደሪያ አስገባሃቸው። ሕዝቦች ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ፍርሃት ያዛቸው። የዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ደነገጡ፤ የሞዓብ መሪዎች መንቀጥቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ። ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ ጌታ ሆይ የገዛኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ በኃይልህ ታላቅነት፥ ፍርሃትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፥ እንደ ድንጋይ ቀጥ አሉ። አንተ ታመጣቸዋለህ፥ በርስትህም ተራራ ትተክላቸዋለህ፥ ጌታ ሆይ ለማደሪያህ በሠራኸው ስፍራ፥ ጌታ ሆይ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ። ጌታ ለዘለዓለም ዓለም ይነግሣል።” የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹ ከፈረሰኞቹም ጋር ወደ ባሕር ገቡ፥ ጌታም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በደረቅ ምድር ሄዱ። የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ ከበሮ በመያዝና በጭፈራ በኋላዋ ወጡ። ማርያምም፦ “ለጌታ ዘምሩ በክብር ከፍ ከፍ ብሏልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ” እያለች ዘመረችላቸው። ሙሴም እስራኤልን ከቀይ ባሕር መራ፥ ወደ ሹር ምድረ በዳም ሄዱ፤ በምድረ በዳም ሦስት ቀን ሄዱ፥ ውኃም አላገኙም። ወደ ማራም መጡ፥ የማራንም ውኃ ሊጠጡ አልቻሉም መራራ ነበረና፤ ስለዚህ አንድ ሰው ማራ ብሎ ጠራው። ሕዝቡም፦ “ምን እንጠጣለን?” ብለው በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። እርሱም ወደ ጌታ ጮኸ፤ ጌታም ዛፍ አሳየው፥ በውኃውም ላይ ጣለው፥ ውኃውም ጣፋጭ ሆነ። ጌታም በዚያ ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤ እርሱም፦ “አንተ የጌታ አምላክህን ቃል ብትሰማ፥ በፊቱም ትክክል የሆነውን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላመጣብህም፤ ፈዋሽህ እኔ ጌታ ነኝና” አለ። እነርሱም ወደ ኤሊም መጡ፥ በዚያም ዐሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የተምር ዛፎች ነበሩ፤ በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ።