ኦሪት ዘፀአት 13
13
በኵር ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ መሆኑ
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“በእስራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም፥ ከእንስሳም መጀመሪያ የተወለደውን ማሕፀንን የሚከፍት በኵር ሁሉ ለእኔ ለይልኝ፤ የእኔ ነው።”
የቂጣ በዓል
3ሙሴም ሕዝቡን አለ፥ “ከባርነት ቤት ከግብፅ የወጣችሁባትን ይህችን ቀን ዐስቡ፤ እግዚአብሔር ከዚህ ቦታ በበረታች እጅ አውጥቶአችኋልና። ስለዚህ የቦካ እንጀራ አትብሉ። 4እናንተ በዚች ቀን በሚያዝያ ወር ወጥታችኋልና። 5እግዚአብሔርም ለእናንተ ይሰጣት ዘንድ ለአባቶቻችሁ ወደማለላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር፥ ወደ ከናኔዎናውያን፥ ወደ ኬጢዎናውያንም፥ ወደ አሞሬዎናውያንም፥ ወደ ኤዌዎናውያን፥ ወደ ኢያቡሴዎናውያንም፥ ወደ ጌርጌሴዎናውያንም፥ ወደ ፌርዜዎናውያንም ምድር በአገባችሁ ጊዜ ይህችን ሥርዐት በዚህ ወር አድርጉ። 6ስድስት ቀን ቂጣ ትበላላችሁ፤ ሰባተኛውም ቀን የእግዚአብሔር በዓል ይሆናል። 7ሰባት ቀንም ሙሉ ቂጣ ትበላላችሁ፤ በእናንተም ዘንድ እርሾ ያለበት እንጀራ አይታይ፤ በአውራጃዎቻችሁ ሁሉ እርሾ አይኑር። 8በዚያም ቀን፦ ‘ከግብፅ በወጣሁ ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ ስለአደረገልኝ ነው’ ስትል ለልጅህ ትነግረዋለህ። 9እግዚአብሔርም በበረታች እጅ ከግብፅ አውጥቶሃልና የእግዚአብሔር ሕግ በአፍህ ይሆን ዘንድ በእጅህ እንደ ምልክት፥ በዐይኖችህም መካከል እንደ መታሰቢያ ይሁንልህ። 10ከቀን ወደ ቀን በየጊዜው ይህን ሕግ ጠብቁት።
11“እግዚአብሔርም ለአባቶችህ እንደማለ ወደ ከነዓናውያን ምድር በአገባህ ጊዜ፥ እርስዋንም ለአንተ በሰጠህ ጊዜ፥ 12ማሕፀንን የሚከፍተውን ሁሉ ለይ፤ ከመንጋህና ከከብትህም መጀመሪያ የሚወለደው ተባት ለእግዚአብሔር ይሆናል። 13የአህያውን በኵር በበግ ትለውጠዋለህ፤ ባትለውጠው ግን ትዋጀዋለህ።#ዕብ. “በጠቦት ትዋጀዋለህ ባቷጀው ግን አንገቱን ትሰብረዋለህ” ይላል። የሰውንም በኵር ሁሉ ከልጆችህ መካከል ትዋጀዋለህ። 14እንዲህም ይሆናል፤ ከዚህ በኋላ ልጅህ፦ ‘ይህ ምንድን ነው?’ ብሎ በጠየቀህ ጊዜ እንዲህ ትለዋለህ፦ እግዚአብሔር በብርቱ እጅ ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር አወጣን፤ 15ፈርዖንም እኛን ለመልቀቅ እንቢ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ከሰው በኵር ጀምሮ እስከ እንስሳ በኵር ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኵር ሁሉ ገደለ፤ ስለዚህ ወንድ ሆኖ ማሕፀንን የከፈተውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሠዋለሁ፤ ነገር ግን የልጆችን በኵር ሁሉ እዋጃለሁ።’ 16እግዚአብሔርም በብርቱ እጅ ከግብፅ አውጥቶሃልና በእጅህ እንደ ምልክት ፥ ከዐይኖችህም እንደማይርቅ ነገር ይሁንልህ።”
የደመና ዐምድና የእሳት ዐምድ
17እንዲህም ሆነ፤ ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ፥ ምንም ቅርብ ቢሆን እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ምድር መንገድ አልመራቸውም፤ እግዚአብሔር፥ “ሕዝቡ ሰልፉን በአየ ጊዜ እንዳይጸጽተው፥ ወደ ግብፅም እንዳይመለስ” ብሎአልና። 18ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን በዙሪያ መንገድ በኤርትራ ባሕር ባለችው ምድረ በዳ መራቸው። የእስራኤልም ልጆች በአምስተኛው ትውልድ ከግብፅ ምድር ወጡ። 19ሙሴም የዮሴፍን ዐጽም ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ “እግዚአብሔር መጐብኘትን በጐበኛችሁ ጊዜ ዐጽሜን ውሰዱ፤ ከእናንተም ጋር ከዚህ አውጡ” ብሎ የእስራኤልን ልጆች አምሎአቸው ነበርና። 20የእስራኤል ልጆችም ከሱኮት ተጓዙ፤ በምድረ በዳውም ዳር በኦቶም#ዕብ. “ኤታም” ይላል። ሰፈሩ። 21እግዚአብሔርም መንገድ ሊያሳያቸው ቀን በዐምደ ደመና፥ ሌሊትም በዐምደ እሳት ይመራቸው ነበር። 22ዐምደ ደመናው በቀን፥ ዐምደ እሳቱም በሌሊት ከሕዝቡ ፊት ከቶ ፈቀቅ አላለም።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 13: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ