መጽሐፈ መክብብ 10
10
1የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል፤ በስንፍናም ካለ ታላቅ ክብር ይልቅ ትንሽ ጥበብ ትበልጣለች።#ዕብ. “እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል” ይላል። 2የጠቢብ ልብ በስተቀኙ ነው፥ የሰነፍ ልብ ግን በስተግራው ነው። 3ደግሞም ሰነፍ በልቡ ፈቃድና መንገድ በሚሄድ ጊዜ አእምሮ ይጐድለዋል፥ የሚያስበውም ሁሉ ሰንፍና ነው።
4ትዕግሥት ታላቁን ኀጢአት ያስተሰርያልና የገዢ ቍጣ የተነሣብህ እንደ ሆነ ስፍራህን አትልቀቅ። 5ከፀሓይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም ከገዢ ባለማወቅ የሚወጣ ስሕተት ነው፥ 6ሰነፍ በታላቅ ማዕርግ ላይ ተሾመ፥ ባለጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ። 7አገልጋዮች በፈረስ ላይ ሲቀመጡ፥ መኳንንትም እንደ አገልጋዮች በምድር ላይ በእግራቸው ሲሄዱ አየሁ።
8ለባልንጀራው ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፥ ቅጥርንም የሚያፈርስን እባብ ትነድፈዋለች። 9ድንጋይን የሚፈነቅል ይታመምበታል፥ ዕንጨትንም የሚፈልጥ ይጐዳበታል። 10ምሣሩ ከዛቢያው ቢወልቅ ሰውየው ፊቱን ወዲያና ወዲህ ይላል፤ ብዙ ኀይልም ያስፈልገዋል። ጥበብ ግን ለብርቱ ሰው ትርፉ ነው፤ 11እባብ ቢነድፍ ባለ መድኀኒትም ባያድን ባለ መድኀኒቱ አይጠቀምም።
12የጠቢብ ሰው የአፉ ቃል ሞገስ ናት፤ የሰነፍ ከንፈሮች ግን ራሱን ይውጡታል። 13የአፉ ቃል መጀመሪያ ስንፍና ነው፥ የንግግሩም ፍጻሜ ክፉ ነው። 14ሰነፍ ነገርን ያበዛል፤ ሰውም የሆነውንና ወደ ፊት የሚሆነውን አያውቅም፤ ከእርሱ በኋላ የሚሆነውንስ ማን ይነግረዋል? 15የሰነፍ ድካሙ ያሠቃየዋል፥ ወደ ከተማ መሄድን አያውቅምና።
16ንጉሥሽ ሕፃን የሆነ፥ መኳንንቶችሽም ማልደው የሚበሉ፥ አንቺ ሀገር ሆይ፥ ወዮልሽ! 17ንጉሥሽ የጌታ ልጅ የሆነ፥ መኳንንቶችሽም ለብርታት በጊዜ የሚበሉ፥ የማያፍሩም፥ አንቺ ሀገር ሆይ፥ የተመሰገንሽ ነሽ። 18በሰዎች ስንፍናና ቦዘኔነት የቤት ጣራ ይዘብጣል፥ በእጆች ስንፍናም ቤት ያፈስሳል። 19ሰነፎች ሰዎች እንጀራን ለሣቅ ያደርጉታል፥ የወይን ጠጅም ሕያዋንን ደስ ያሰኛል፥ ሁሉም ለገንዘብ ይገዛል። 20የሰማይ ዎፍ ቃልህን ያወጣዋልና፥ ክንፍ ያለውም ነገርህን ያወራዋልና በልብህ ዐሳብ እንኳን ቢሆን ንጉሥን አትሳደብ፥ በመኝታ ቤትህም ባለጠጋን አትሳደብ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 10: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ