ኦሪት ዘዳግም 23
23
ከእግዚአብሔር ጉባኤ የሚለይ ሁኔታ
1“ፍሬ ዘሩ የተቀጠቀጠ፥ አባለ ዘሩም የተቈረጠ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይግባ። 2ዲቃላ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይግባ፤#ዕብ. “ዲቃላ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ” ይላል።
3“አሞናዊ ወይም ሞዓባዊ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይግባ፤ እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ ለዘለዓለም ወደ እግዚአብሔር ቤት አይግባ። 4ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ እንጀራና ውኃ ይዘው በመንገድ ላይ አልተቀበሉአችሁምና፥ ከመስጴጦምያ የቢዖርን ልጅ በለዓምን ዋጋ ሰጥተው ይረግማችሁ ዘንድ ተዋውለውባችኋልና። 5ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በለዓምን ይሰማ ዘንድ አልወደደም፤ አምላክህ እግዚአብሔርም ወድዶሃልና ርግማኑን ወደ በረከት ለወጠልህ። 6በዘመንህ ሁሉ ለዘለዓለም ሰላም እንደሚገባቸው አታናግራቸው።
7“ኤዶማዊዉ ወንድምህ ነውና አትጸየፈው፤ ግብፃዊዉንም በሀገሩ ስደተኛ ነበርህና አትጸየፈው። 8ከእነርሱም በሦስተኛው ትውልድ የሚወለዱ ልጆች ወደ እግዚአብሔር ቤት ይግቡ።
ሰፈርን በንጽሕና መጠበቅ
9“ጠላቶችህን ልትወጋ በወጣህ ጊዜ ከክፉ ነገር ሁሉ ሰውነትህን ጠብቅ። 10በእናንተ ውስጥ ሌሊት በሚሆነው ርኵሰት የረከሰ ሰው ቢኖር፥ ከሰፈር ወደ ውጭ ይውጣ፤ ወደ ሰፈርም አይግባ። 11በመሸም ጊዜ ሰውነቱን በውኃ ይታጠብ፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ወደ ሰፈር ይመለስ። 12ወደ ሜዳም ትወጣባት ዘንድ ከሰፈር ውጭ ቦታ ይኑርህ። 13ከመሣርያህም ጋር መቈፈሪያ ያዝ፤ ሜዳም በተቀመጥህ ጊዜ ትምስበታለህ፤ ዞረህም ከአንተ የወጣውን በአፈር ትከድነዋለህ። 14አምላክህ እግዚአብሔር ሊያድንህ፥ ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥህ በሰፈርህ ውስጥ ይሄዳልና ስለዚህ ነውረኛ ነገር እንዳያይብህ፥ ፊቱንም ከአንተ እንዳይመልስ ሰፈርህ የተቀደሰ ይሁን።
ልዩ ልዩ ሕግጋት
15“ከጌታዉ ኰብልሎ ወደ አንተ የተጠጋውን ባሪያ ለጌታው አሳልፈህ አትስጥ። 16ከአንተ ጋር ይኑር፤ በመካከልህም በሚወድዳት በአንዲቱ ስፍራ ይቀመጥ፤ አንተም አታስጨንቀው።
17“ከእስራኤል ሴቶች ልጆች ሴት አመንዝራ አትገኝ፤ ከእስራኤልም ወንዶች ልጆች ወንድ አመንዝራ አይገኝ።#ግእዙ “አልቦ ዘያገብእ ጸባሕተ እምደቂቀ እስራኤል ...” ብሎ ይጨምራል። 18ስለ ተሳልኸው ስእለት ሁሉ የአመንዝራዪቱን ዋጋና የውሻውን ዋጋ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አታቅርብ፤ ሁለቱም በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያጸይፉ ናቸውና።
19“ለወንድምህ በወለድ አታበድር፤ የብር ወይም የእህል፥ ወይም የማናቸውንም ነገር ሁሉ ወለድ አትውሰድ። 20ለእንግዳው በወለድ አበድር፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር በሥራህ ሁሉ ይባርክህ ዘንድ ለወንድምህ በወለድ አታበድር።
21“ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ፈጽሞ ይሻዋልና፥ ኀጢአትም ይሆንብሃልና መክፈሉን አታዘግይ። 22ባትሳል ግን ኀጢአት የለብህም። 23በአፍህ የተናገርኸውን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፈቃድህ ተስለሃልና ከከንፈርህ የወጣውን ታደርግ ዘንድ ጠብቅ።
24“ወደ ባልንጀራህ እርሻ በገባህ ጊዜ እሸቱን በእጅህ ቀጥፈህ ብላ፤#“ብላ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ወዳልታጨደው ወደ ባልንጀራህ እህል ግን ማጭድ አታግባ። 25ወደ ባልንጀራህ የወይን ቦታ በገባህ ጊዜ እስክትጠግብ ድረስ ከወይኑ ብላ፤ ወደ ዕቃህ ግን ከእርሱ ምንም አታግባ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 23: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ