የእግዚአብሔር መልአክም ፊልጶስን ተናገረው፤ እንዲህም አለው፥ “በቀትር ጊዜ ተነሣና በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚያወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ።” ተነሥቶም ሄደ፤ እነሆም፥ የኢትዮጵያ ንግሥት የሕንደኬ ጃንደረባ ከሹሞችዋ የበለጠ፥ በሀብቷም ሁሉ ላይ በጅሮንድ የነበረ፥ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ነበር፤ እርሱም ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። ሲመለስም በሰረገላው ላይ ተቀምጦ የነቢዩ የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። መንፈስ ቅዱስም ፊልጶስን፥ “ሂድ፤ ይህን ሰረገላ ተከተለው” አለው። ፊልጶስም ፈጥኖ ደርሶ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማው፤ ፊልጶስም፥ “በውኑ የምታነበውን ታውቀዋለህን?” አለው። ጃንደረባውም፥ “ያስተማረኝ ሳይኖር በምን አውቀዋለሁ?” አለው፤ ወደ ሰረገላውም ወጥቶ አብሮት ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው። ያነበው የነበረ የመጽሐፉ ቃልም እንዲህ የሚል ነበር፤ “እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሚሸልተው ፊት እንደማይናገር እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዶአልና ትውልዱን ማን ይናገራል?” ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ፥ “ነቢዩ ስለ ማን እንዲህ ይላል? ስለ ራሱ ነውን? ወይስ ስለ ሌላ? እባክህ ንገረኝ” አለው። ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ስለ ኢየሱስም ከዚያው መጽሐፍ ጀምሮ አስተማረው። በመንገድ ሲሄዱም ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፥ “እነሆ፥ ውኃ፥ መጠመቅን ምን ይከለክለኛል?” አለው። ፊልጶስም፥ “በፍጹም ልብህ ብታምን ይገባሃል” አለው፤ ጃንደረባውም መልሶ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እኔ አምናለሁ” አለው። ሰረገላውንም እንዲያቆሙ አዘዘ፤ አቁመውም ፊልጶስና ጃንደረባው በአንድነት ወደ ውኃው ወረዱ፤ አጠመቀውም። ከውኃዉም ከወጡ በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ ፊልጶስን ነጥቆ ወሰደው፤ ጃንደረባዉም ከዚያ ወዲያ አላየውም፤ ደስ እያለውም መንገዱን ሄደ።
የሐዋርያት ሥራ 8 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 8
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 8:26-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos