የሐዋርያት ሥራ 4
4
ጴጥሮስና ዮሐንስ በካህናት ሸንጎ ፊት
1ሕዝቡንም ሲያስተምሩ ሊቃነ ካህናትና የቤተ መቅደስ ሹም፥ ሰዱቃውያንም መጡ። 2ሕዝቡን ስለ አስተማሩና በኢየሱስም የሙታንን ትንሣኤ ስለ ሰበኩ በእነርሱ ተናደዱ። 3እጃቸውንም ዘርግተው ያዙአቸው፤ ጊዜዉም ፈጽሞ መሽቶ ነበርና እስከ ማግሥቱ ድረስ በወኅኒ ቤት አገቡአቸው። 4ቃሉንም ሰምተው ያመኑ ብዙ ሰዎች ናቸው፤ ያመኑት ወንዶች ቍጥርም አምስት ሺህ ያህል ሆነ።
5በማግሥቱም አለቆቻቸውና ሽማግሎች፥ ጻፎችም በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 6ሊቀ ካህናቱ ሐና፥ ቀያፋም፥ ዮሐንስና እለእስክንድሮስም፥ የሊቀ ካህናቱም ወገን ሁሉ ከእነርሱ ጋር ነበሩ። 7በአደባባይም አቆሙና፥ “እናንተ ይህን በማን ስምና በማን ኀይል አደረጋችሁት?” ብለው መረመሩአቸው። 8ያንጊዜም በጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስ ሞላበትና እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች ሆይ፥ ስሙ፤ 9ዛሬ ለበሽተኛው በተደረገው ረድኤት ምክንያት በእናንተ ዘንድ እኛ የሚፈረድብን ከሆነ እንግዲያ ይህ ሰው በምን ዳነ? 10እንግዲህ እናንተ ሁላችሁ፥ የእስራኤልም ወገን ሁሉ፥ እናንተ በሰቀላችሁት፥ እግዚአብሔርም ከሙታን ለይቶ በአስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ሰው እንደ ዳነና በፊታችሁም እንደ ቆመ በርግጥ ዕወቁ። 11#መዝ. 117፥22። ይህ እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት ድንጋይ ነውና፤ እርሱም የማዕዘን ራስ ሆነ። 12መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለምና።”
13ጴጥሮስና ዮሐንስም ግልጥ አድርገው ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ፥ ያልተማሩና መጽሐፍን የማያውቁ ሰዎች እንደ ሆኑ ዐውቀው አደነቁ፤ ሁልጊዜም ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩ ዐወቁ። 14ያን የዳነውን ሰውም ከእነርሱ ጋር ቆሞ በአዩት ጊዜ የሚሉትን አጡ። 15ከሸንጎውም ጥቂት ፈቀቅ አደረጉአቸውና እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። 16እንዲህም አሉ፥ “እነዚህን ሰዎች ምን እናድርጋቸው? እነሆ፥ በእነርሱ የሚደረገው ተአምር በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ሁሉ ዘንድ ታወቀ፤ ግልጥም ሆነ፤ ልንሰውረውም አንችልም። 17ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ እጅግ እንዳይስፋፋ ዳግመኛ በኢየሱስ ስም ሰውን እንዳያስተምሩ አጠንክረን እንገሥጻቸው።” 18ጠርተውም፦“ በኢየሱስ ስም ፈጽሞ አትናገሩ አታስተምሩም” ብለው አዘዙአቸው። 19ጴጥሮስና ዮሐንስም እንዲህ ብለው መለሱላቸው፥ “እግዚአብሔርን ያይደለ እናንተን ልንሰማ በእግዚአብሔር ፊት ይገባልን? እስኪ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። 20እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም እንል ዘንድ አንችልም።” 21እነርሱንም የሚቀጡበት ምክንያት ስለ አጡባቸው ገሥጸው ለቀቁአቸው፤ ስለ ተደረገው ተአምር ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበርና። 22ይህ የድኅነት ምልክት ለተደረገለት ለዚያ ሰው ከአርባ ዓመት ይበልጠው ነበረና።
23ተፈትተውም ወደ ሰዎቻቸው ሄዱ፤ ሊቃነ ካህናትና ሽማግሌዎችም ያሉአቸውን ሁሉ ነገሩአቸው። 24#ዘፀ. 20፥11፤ ነህ. 9፥6፤ መዝ. 145፥6። ይህንም በሰሙ ጊዜ በአንድነት ቃላቸውን ወደ እግዚአብሔር ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፥ “ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ የፈጠርህ አንተ እግዚአብሔር ሆይ፥ 25አንተ ራስህ በአባታችን በባሪያህ በዳዊት አፍ በመንፈስ ቅዱስ እንዲህ ብለህ የተናገርህ፦ አሕዛብ ለምን ተሰበሰቡ? ሕዝቡስ ለምን ከንቱ ነገርን ተናገሩ? 26#መዝ. 2፥1-2። የምድር ነገሥታት ለምን ተነሡ? አለቆችስ ከእነርሱ ጋር አብረው በእግዚአብሔርና በመሲሑ ላይ ለምን ዶለቱ? 27#ማቴ. 27፥1-2፤ ማር. 15፥1፤ ሉቃ. 23፥1፤ 7፥11፤ ዮሐ. 8፥28-29። በቀባኸው በቅዱስ ልጅህ ላይ ሄሮድስና ጰንጤናዊው ጲላጦስ ከወገኖቻቸውና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በእውነት በዚች ሀገር ላይ ዶለቱ። 28እጅህና ምክርህ እንዲደረግ የወሰኑትን ይፈጽሙ ዘንድ። 29አሁንም አቤቱ፥ ትምክህታቸውን ተመልከት፤ ቃልህንም በግልጥ ያስተምሩ ዘንድ ለባሮችህ ስጣቸው። 30በቅዱሱ ልጅህም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሕሙማንን ትፈውስ ዘንድ ተአምራትንና ድንቅ ሥራንም ታደርግ ዘንድ እጅህን ዘርጋ።” 31ሲጸልዩም በአንድነት ተሰብስበው የነበሩበት ቦታ ተናወጠ፤ በሁሉም ላይ መንፈስ ቅዱስ መላባቸውና የእግዚአብሔርን ቃል በግልጥ አስተማሩ።
ስለ ምእመናን አንድነት
32 #
የሐዋ. 2፥44-45። ያመኑትም ሁሉ አንድ ልብና አንዲት ነፍስ ሆነው ይኖሩ ነበር፤ በውስጣቸውም የሁሉ ገንዘብ በአንድነት ነበር እንጂ “ይህ የእኔ ገንዘብ ነው” የሚል አልነበረም። 33ሐዋርያትም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኀይል ይመሰክሩ ነበር፤ በሕዝቡም ዘንድ ታላቅ ጸጋ ነበራቸው። 34ከእነርሱም አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረም፤ ቤትና መሬት ያላቸውም ሁሉ እየሸጡ ገንዘቡን ያመጡ ነበር። 35አምጥተውም በሐዋርያት እግር አጠገብ ያኖሩት ነበር፤ እነርሱም ለእያንዳንዱ እንደ ፍላጎቱ ይከፍሉት ነበር። 36በሐዋርያትም ዘንድ ትርጓሜዉ የመጽናናት ልጅ የሚሆን በርናባስ የተባለ የሌዊ ወገን ስሙን ዮሴፍ የሚሉት አንድ የቆጵሮስ ሰው ነበር። 37እርሻም ነበረውና ሽጦ ገንዘቡን አምጥቶ በሐዋርያት እግር አጠገብ አኖረው።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 4: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ