የሐዋርያት ሥራ 19
19
ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ስለ መምጣቱ
1ከዚህም በኋላ አጵሎስ በቆሮንቶስ ሳለ፥ ጳውሎስ ላይ ላዩን ሄዶ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ በዚያም ጥቂት ደቀ መዛሙርትን አገኘ። 2“ካመናችሁ ጀምሮ በውኑ መንፈስ ቅዱስን ተቀብላችኋልን?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም” አሉት። 3እርሱም፥ “እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “በዮሐንስ ጥምቀት” አሉት። 4#ማቴ. 3፥11፤ ማር. 1፥4፤7-8፤ ሉቃ. 3፥4፤ 16፤ ዮሐ. 1፥26-27። ጳውሎስም፥ “ዮሐንስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ እየሰበከ የንስሓ ጥምቀትን አጠመቀ” አላቸው። 5እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ። 6ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ ወረደ፤ ያንጊዜም በሀገሩ ሁሉ ቋንቋ ተናገሩ፤ ትንቢትም ተናገሩ። 7ሰዎቹም ሁሉ ዐሥራ ሁለት ያህሉ ነበር። 8ጳውሎስም ወደ ምኵራብ ገብቶ በግልጥ አስተማረ፤ ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት እያስተማራቸውና እያሳመናቸው ሦስት ወር ቈየ። 9በተሰበሰበውም ሕዝብ ፊት አንዳንዶች በእግዚአብሔር ትምህርት ላይ ክፉ እየተናገሩ ባላመኑ ጊዜ፥ ጳውሎስ ከእነርሱ ተለየ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ይዞ ጢራኖስ በሚባል መምህር ቤት ሁልጊዜ ያስተምራቸው ነበር። 10በእስያም ያሉ አይሁድና አረማውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል እስኪሰሙ ድረስ እንደዚሁ ሁለት ዓመት ኖረ።
ለጳውሎስ ስለ ተሰጠው ሀብተ ፈውስ
11እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ ታላላቅ ሥራን ይሠራ ነበር። 12ከልብሱ ዘርፍና ከመጠምጠሚያዉ ጫፍ ቈርጠው እየወሰዱ በድውያኑ ላይ ያኖሩት ነበር፤ እነርሱም ይፈወሱ ነበር፤ ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። 13ከአይሁድም አስማት እያደረጉ የሚዞሩ ሰዎች ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ “ጳውሎስ በሚያስተምርበት በኢየሱስ ስም እናምላችኋለን” እያሉ የጌታችን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ነበር። 14እኒህ እንዲህ ያደርጉ የነበሩትም የካህናቱ አለቃ የአይሁዳዊው የአስቂዋ ልጆች ናቸው፤ እነርሱም ሰባት ነበሩ። 15ያም ክፉ መንፈስ፥ “በኢየሱስ አምናለሁ፥#ግሪኩ “አውቀዋለሁ” ይላል። ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እንግዲህ እናንተ እነማን ናችሁ?” ብሎ መለሰላቸው። 16ያም ክፉ መንፈስ የያዘው ሰው ተነሣባቸው፤ አየለባቸውም፤ አሸነፋቸውም፤ አቍስሎም ከዚያ ቤት አስወጥቶ አባረራቸው። 17ይህም ነገር በኤፌሶን በሚኖሩ በአይሁድና በአረማውያን ሁሉ ዘንድ ተሰማ፤ ሁሉም ፈሩ፤ የጌታችን የኢየሱስንም ስም ከፍ ከፍ አደረጉ። 18ያመኑትም ሁሉ እየመጡ ስለ ሠሩት ንስሓ ይገቡ ነበር። 19ብዙዎች አስማተኞችም መጽሐፎቻቸውን እየሰበሰቡ እያመጡ በሕዝቡ ሁሉ ፊት በእሳት ያቃጥሉ ነበር፤ ያቃጠሏቸው የመጽሐፎች ዋጋም አምሳ ሺህ ብር ነበር። 20እንዲህም እያለ የእግዚአብሔር ቃል በኀይል ያድግና ይበረታ ነበር።
21ይህም ከተፈጸመ በኋላ ጳውሎስ በመቄዶንያና በአካይያ በኩል አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም ሊሄድ በልቡ ዐሰበ፥ “እዚያም ከደረስሁ በኋላ ሮሜን ላያት ይገባኛል” አለ። 22ከሚያገለግሉትም ሁለቱን ጢሞቴዎስንና አርስጦስን ወደ መቄዶንያ ላከ፤ እርሱ ራሱ ጳውሎስ ግን ብዙ ቀን በእስያ ተቀመጠ።
በኤፌሶን ስለ ተደረገው ሁከት
23በዚያም ወራት ስለዚህ ትምህርት ብዙ ሁከት ሆነ። 24በዚያም ብር ሠሪ የሆነ ድሜጥሮስ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ ለአርጤምስም ከብር የቤተ መቅደስ ምስል ይሠራ ነበር፤ አንጥረኞችንም እያሠራ ብዙ ገንዘብ ይሰጣቸው ነበር። 25አንጥረኞችንና ይህን የመሰለውን ሥራ የሚሠሩትንም ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ጥቅም የምናገኘው በዚህ ሥራችን እንደ ሆነ እናንተ ታውቃላችሁ። 26አሁን ግን እንደምታዩትና እንደምትሰሙት ይህ ጳውሎስ ኤፌሶንን ብቻ ሳይሆን መላውን እስያን አሳተ፤ ብዙ ሕዝብንም መለሰ፤ በሰው እጅ የሚሠሩትንም ሁሉ አማልክት አይደሉም አላቸው። 27አሁን የምንቸገር በዚህ ነገር ብቻ አይደለም፤ እስያና መላው ዓለም የሚያመልካት የታላቋ የአርጤምስም መቅደስ ክብር ይቀራል፤ ገናናነቷም ይሻራል።”
28ይህንም በሰሙ ጊዜ ተቈጡና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፥ “የኤፌሶን አርጤምስ ክብርዋ ታላቅ ነው” አሉ። 29ከተማውም ሁሉ ታወከ፤ የመቄዶንያን ሰዎች የጳውሎስን ወዳጆች ጋይዮስንና አርስጥሮኮስንም ከእነርሱ ጋር እየጐተቱበአንድነት ወደ ጨዋታው ቦታ ሮጡ። 30ጳውሎስም ወደ አሕዛብ መካከል ሊገባ ወድዶ ነበር፤ ነገር ግን ደቀ መዛሙርት ከለከሉት። 31ከእስያም የሆኑ ታላላቆች ወዳጆቹ ወደ ጨዋታው ቦታ እንዳይገባ ልከው ማለዱት። 32በዚያም በጨዋታው ቦታ የነበሩ ሰዎች እየጮኹ ቈዩ፤ በሌላም ቋንቋ የሚጮሁ ነበሩ፤ በጉባኤው ታላቅ ድብልቅልቅ ሆኖ ነበርና፤ ከእነርሱ የሚበዙት ግን በምን ምክንያት እንደ ተሰበሰቡ አያውቁም ነበር። 33በዚያ የነበሩ አይሁድም እስክንድሮስ የሚባል አይሁዳዊ ሰውን ከመካከላቸው አስነሡ፤ እርሱም ተነሥቶ በእጁ ምልክት ሰጠና ለሕዝቡ ሊከራከርላቸው ወደደ። 34አይሁዳዊ እንደሆነም ባወቁ ጊዜ “የኤፌሶን አርጤምስ ክብርዋ ታላቅ ነው” እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ሁሉም በአንድ ድምፅ ጮሁ። 35ከዚህም በኋላ የከተማው ጸሓፊ ተነሥቶ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፥ ስሙ፤ የኤፌሶን ከተማ ታላቂቱን አርጤምስንና ከሰማይ የወረደውን ጣዖትዋን እንደምትጠብቅ የማያውቅ ማነው? 36ስለዚህም እርስዋን መቃወም የሚቻለው ያለ አይመስለኝም፤ አሁንም ይህን በጠብና በክርክር ሳይሆን በቀስታ ልናደርገው ይገባናል። 37የአማልክትን ቤት ያልዘረፉትንና በአማልክቶቻችን ላይ ክፉ ቃልን ያልተናገሩትን እነዚህን ሰዎች እነሆ ወደ እዚህ አምጥታችኋቸዋል። 38ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉ አንጥረኞች ግን በማንም ላይ ጠብ እንዳላቸው እርስ በርሳቸው ይከራከሩ፤ እነሆም በከተማው ውስጥ ፍርድ ቤት አለ፤ ዳኞችም አሉ። 39ነገር ግን ይህ የምትከራከሩበት ነገር ሌላ ከሆነ በሕግ ሸንጎ ይፈታል። 40ዛሬም በደል ሳይኖር በአመጣችሁብን ክርክር እኛ እንቸገራለንና ስለዚህ ክርክር የምንወቃቀሰው ነገር የለም፥” ይህንም ብሎ ሸንጎውን ፈታ።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 19: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ