ከዚህም በኋላ ሐዋርያትና ቀሳውስት ሕዝቡም ሁሉ ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ የሚልኳቸውን ሰዎች ይመርጡ ዘንድ ተስማሙ፤ ከባልንጀሮቻቸው መካከልም የተማሩትን ሰዎች በርናባስ የተባለ ይሁዳንና ሲላስን መረጡ። እንዲህ የምትል መልእክትም በእጃቸው ጻፉ፤ “ከሐዋርያትና ከቀሳውስት ከወንድሞችም በአንጾኪያ፥ በሶርያና በኪልቅያ ለሚኖሩ፥ ከአሕዛብ ላመኑ ወንድሞቻችን ትድረስ፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን፥ ደስ ይበላችሁ። ያላዘዝናቸው ሰዎች ከእኛ ወጥተው፦ ‘ትገዘሩ ዘንድና የኦሪትንም ሕግ ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኋል’ ብለው በነገር እንደ አወኩአችሁና ልባችሁን እንደ አናወጡት ሰምተናል። ሁላችን ከተሰበሰብን በኋላ በአንድ ቃል በየን፤ አንድ ሆነንም ከወንድሞቻችን ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ እናንተ የምንልካቸውን ሰዎች መረጥን። እነርሱም ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡ ሰዎች ናቸው። ይሁዳንና ሲላስን ልከናቸዋልና እነርሱ በቃላቸው ይህን ያስረዱአችኋል። ሥርዐት እንዳናከብድ ሌላም ሸክም እንዳንጨምር መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ነውና፤ ነገር ግን ይህን በግድ ትተዉ ዘንድ እናዝዛችኋለን። ለአማልክት የተሠዋውን፥ ሞቶ የተገኘውን፥ ደምንም አትብሉ፤ ከዝሙትም ራቁ፤ በራሳችሁ የምትጠሉትንም በወንድሞቻችሁ ላይ አታድርጉ፥ ከእነዚህ ሥራዎችም ሰውነታችሁን ብትጠብቁ በሰላም ትኖራላችሁ፤ ደኅና ሁኑ።” እነርሱም ተልከው ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ ሕዝቡንም ሰብስበው የተላከውን ደብዳቤ ሰጡአቸው። እነርሱም አንብበው እጅግ ደስ አላቸው፥ ተጽናኑም። ይሁዳና ሲላስም መምህራን ነበሩና አስተማሩአቸው፤ ወንድሞችንም በብዙ ቃል አጽናኑአቸው። በእነርሱም ዘንድ አያሌ ቀን ከተቀመጡ በኋላ ወንድሞቻቸውን ተሰናብተው በሰላም ወደ ሐዋርያት ተመለሱ። ሲላስ ግን በዚያ ሊቈይ ወደደ። ጳውሎስና በርናባስም በአንጾኪያ ቈዩ፤ ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋርም የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አስተማሩም።
የሐዋርያት ሥራ 15 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 15
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 15:22-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos