ጴጥሮስም አፉን ከፈተና እንዲህ አለ፥ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንደማያዳላ በእውነት አየሁ። ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ እርሱን የሚፈራና እውነትን የሚያደርግ በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው። ቃሉን ለእስራኤል ልጆች ላከ፤ በኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምን ነገራቸው፤ እርሱም የሁሉ ገዢ ነው። ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ የሆነውን ነገር ሁሉ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ በኀይልም እንደ ቀባው፥ እየዞረም መልካም እንደ አደረገ፥ ሰይጣን ያሸነፋቸውንም እንደ ፈወሰ ታውቃላችሁ። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና። በይሁዳና በኢየሩሳሌም ባደረገውም ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በዕንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። እግዚአብሔር ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ በግልጥ እንዲታይም አደረገው። ይኸውም ለሕዝቡ ሁሉ አይደለም፤ ነገር ግን አስቀድሞ ለመረጣቸውና ምስክሮች ለሚሆኑት ብቻ ነው እንጂ፤ የመረጣቸው የተባልንም እኛ ነን፤ ከሙታንም ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን። በእግዚአብሔር ዘንድ በሕያዋንና በሙታን ላይ ፈራጅ ሆኖ የተሾመ እርሱ እንደ ሆነ ለሕዝብ እናስተምር ዘንድ አዘዘን። ለሚያምኑበትም ሁሉ ኀጢአታቸው በስሙ እንደሚሰረይላቸው ነቢያት ሁሉ ምስክሮቹ ናቸው።” ጴጥሮስም ይህን ነገር ሲነግራቸው ይህን ትምህርት በሰሙት ሰዎች ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ከጴጥሮስ ጋር የመጡ ከአይሁድ ወገን የሆኑ ምእመናን ሁሉ ደነገጡ፤ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በአሕዝብ ላይ ወርዶአልና። በልዩ ልዩ ሀገር ቋንቋ ሲናገሩ፥ እግዚአብሔርንም ሲያመሰግኑ ሰምተዋቸዋልና። ጴጥሮስም፥ “እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ እንግዲህ በውኃ እንዳይጠመቁ ውኃን ሊከለክላቸው የሚችል ማነው?” አለ። በኢየሱስ ክርስቶስም ስም እንዲጠመቁ አዘዛቸው። ከዚህም በኋላ ጥቂት ቀን አብሮአቸው እንዲቀመጥ ጴጥሮስን ማለዱት።
የሐዋርያት ሥራ 10 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 10
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 10:34-48
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች