በቂሳርያም ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራም የመቶ አለቃ ነበር። እርሱም ጻድቅና ከነቤተ ሰቡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር፤ ለሕዝቡም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ዘወትርም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር። የእግዚአብሔር መልአክም በራእይ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በግልጥ ታየው፤ ወደ እርሱም ገብቶ፥ “ቆርኔሌዎስ ሆይ፥” አለው። ወደእርሱም ተመልክቶ ፈራና፥ “አቤቱ፥ ምንድን ነው?” አለ፤ መልአኩም እንዲህ አለው፥ “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጎአል። አሁንም ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን ይጠሩልህ ዘንድ ወደ ኢዮጴ ከተማ ሰዎችን ላክ። እርሱም ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት እንግድነት ተቀምጦአል። ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።” ያነጋገረውም መልአክ ከሄደ በኋላ ከሎሌዎቹ ሁለት፥ ከማይለዩት ጭፍሮቹም አንድ ደግ ወታደር ጠራ። ነገሩንም ሁሉ ነግሮ ወደ ኢዮጴ ከተማ ላካቸው። በማግሥቱም ሄደው ወደ ከተማዪቱ በር ደረሱ፤ ጴጥሮስም በቀትር ጊዜ ሊጸልይ ወደ ሰገነት ወጥቶ ነበር። በተራበ ጊዜም ምሳ ሊበላ ወደደ፤ እነርሱም እያዘጋጁ ሳሉ ተመስጦ መጣበት። ሰማይም ተከፍቶ በአራቱ ማዕዘን የተያዘ እንደ ታላቅ መጋረጃ ያለ ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ። በውስጡም አራት እግር ያለው እንስሳ ሁሉ፥ አራዊትም፥ የሚንቀሳቀስም፥ የሰማይም ወፎች ነበሩበት። “ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሥና አርደህ ብላ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን፥ “አቤቱ፥ ከቶ አይሆንም፤ ርኩስ፥ የሚያጸይፍም ከቶ በልች አላውቅም” አለው። ዳግመኛም፥ “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ አታርክስ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ። ይህንም ሦስት ጊዜ አለው፤ ወዲያውኑም ዕቃዉ ወደ ሰማይ ተመለሰ። ጴጥሮስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደ ሆነ ሲያወጣና ሲያወርድ ከቆርኔሌዎስ ተልከው የመጡ ሰዎች የስምዖንን ቤት እየጠየቁ በደጅ ቁመው ነበር። ተጣርተውም፦ ጴጥሮስ የተባለ ስምዖን በእንግድነት በዚያ ይኖር እንደ ሆነ ጠየቁ። ጴጥሮስም ስለ ታየው ራእይ ሲያወጣ ሲያወርድ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው፥ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል። ተነሥና ውረድ፤ ምንም ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤ እኔ ልኬአቸዋለሁና።” ጴጥሮስም ወደ እነዚያ ሰዎች ወረደና፥ “እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ ለምን መጥታችኋል?” አላቸው። እነርሱም፥ “የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ጻድቅ ሰው ነው፤ በአይሁድም ወገኖች ሁሉ የተመሰከረለት ነው፤ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አንተን ወደ ቤቱ እንዲጠራህ የምታስተምረውንም እንዲሰማ አዝዞታል፤” አሉት። እርሱም ተቀብሎ አሳደራቸው፤ በማግሥቱም ተነሥቶ አብሮአቸው ሄደ፤ በኢዮጴ ከተማ ከሚኖሩት ወንድሞችም አብረውት የሄዱ ነበሩ። በማግሥቱም ወደ ቂሳርያ ከተማ ገባ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ ይጠብቃቸው ነበር። ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ ከእግሩ በታችም ወድቆ ሰገደለት። ጴጥሮስም፥ “ተነሥ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ” ብሎ አነሣው። ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ወደ እርሱም የመጡ ብዙ ሰዎችን አገኘ። ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፥ “ለአይሁዳዊ ሰው ሄዶ ከባዕድ ወገን ጋር መቀላቀል እንደማይገባው ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን ከሰው ማንንም ቢሆን እንዳልጸየፍና ርኩስ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳየኝ። አሁንም ስለ ላካችሁብኝ ሳልጠራጠር ወደ እናንተ መጣሁ፤ በምን ምክንያት እንደ ጠራችሁኝ እጠይቃችኋለሁ።” ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፥ “የዛሬ አራት ቀን በዘጠኝ ሰዓት በዚች ሰዓት በቤቴ ስጸልይ የሚያንፀባርቅ ልብስ የለበሰ አንድ ሰው በፊቴ ቆሞ ታየኝ። እንዲህም አለኝ፦ ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ፤ ምጽዋትህም ታሰበልህ። አሁንም ወደ ኢዮጴ ከተማ ላክና በባሕር አቅራቢያ ባለችው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት የሚኖረውን ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን ይጥሩልህ፤ እርሱ መጥቶ የምትድንበትን ይነግርሃል። ስለዚህም ወዲያውኑ ወደ አንተ ላክሁ፤ ወደ እኛ በመምጣትህም መልካም አደረግህ፤ አሁንም እግዚአብሔር ያዘዘህን ሁሉ ልንሰማ እነሆ፥ እኛ ሁላችን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን።” ጴጥሮስም አፉን ከፈተና እንዲህ አለ፥ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንደማያዳላ በእውነት አየሁ። ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ እርሱን የሚፈራና እውነትን የሚያደርግ በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው። ቃሉን ለእስራኤል ልጆች ላከ፤ በኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምን ነገራቸው፤ እርሱም የሁሉ ገዢ ነው። ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ የሆነውን ነገር ሁሉ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ በኀይልም እንደ ቀባው፥ እየዞረም መልካም እንደ አደረገ፥ ሰይጣን ያሸነፋቸውንም እንደ ፈወሰ ታውቃላችሁ። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና። በይሁዳና በኢየሩሳሌም ባደረገውም ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በዕንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። እግዚአብሔር ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ በግልጥ እንዲታይም አደረገው። ይኸውም ለሕዝቡ ሁሉ አይደለም፤ ነገር ግን አስቀድሞ ለመረጣቸውና ምስክሮች ለሚሆኑት ብቻ ነው እንጂ፤ የመረጣቸው የተባልንም እኛ ነን፤ ከሙታንም ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን። በእግዚአብሔር ዘንድ በሕያዋንና በሙታን ላይ ፈራጅ ሆኖ የተሾመ እርሱ እንደ ሆነ ለሕዝብ እናስተምር ዘንድ አዘዘን። ለሚያምኑበትም ሁሉ ኀጢአታቸው በስሙ እንደሚሰረይላቸው ነቢያት ሁሉ ምስክሮቹ ናቸው።” ጴጥሮስም ይህን ነገር ሲነግራቸው ይህን ትምህርት በሰሙት ሰዎች ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ከጴጥሮስ ጋር የመጡ ከአይሁድ ወገን የሆኑ ምእመናን ሁሉ ደነገጡ፤ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በአሕዝብ ላይ ወርዶአልና። በልዩ ልዩ ሀገር ቋንቋ ሲናገሩ፥ እግዚአብሔርንም ሲያመሰግኑ ሰምተዋቸዋልና። ጴጥሮስም፥ “እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ እንግዲህ በውኃ እንዳይጠመቁ ውኃን ሊከለክላቸው የሚችል ማነው?” አለ።
የሐዋርያት ሥራ 10 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 10
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 10:1-47
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos