ተረፈ ባሮክ 5
5
1ባሮክም ይህን ከተናገረ በኋላ ንስሩ ደብዳቤውን ይዞ በረረ፤ ወደ ባቢሎንም ሄዶ በምድረ በዳ ባለው ቦታ ከከተማ ውጭ ባለ ዛፍ ላይ ዐረፈ። 2ኤርምያስ እስኪያልፍ ድረስ ሌሎችም ወገኖች እስኪያልፉ ድረስ በዚያው ቈየ፤ ኤርምያስም ናቡከደነፆርን ከወገኖች የሞተውን የምቀብርበት ቦታ ስጠኝ ብሎ ለምኗልና፥ እርሱም ሰጥቶታልና ሕዝቡ የሞተውን ሰው ሊቀብሩ በዚያ በኩል ዐለፉ። 3ለሞተውም ሰው እያለቀሱ ሲሄዱ ከንስሩ ፊት ደረሱ። 4ንስሩም በዚያ ቦታ ሆኖ በታላቅ ቃል አሰምቶ ጮኸ፤ “አምላክ የመረጠህ ኤርምያስ ሆይ፥ ለአንተ እነግርሃለሁ፤ ሄደህ ሕዝቡን ሁሉ ሰብስባቸው፤ እኔ#አንዳንድ ዘርዕ “ከባሮክና ከአቤሜሌክ ያመጣሁትን መልካም የምሥራች ...” ይላል። ያመጣሁትን መልካም የምሥራች እስኪሰሙ ድረስ ወደዚህ ይምጡ” አለው።
5ኤርምያስም ይህን ሰምቶ እግዚአብሔርን አመሰገነው፤ ያንጊዜም ሕዝቡን ሁሉ ሚስቶቻቸውንም፥ ልጆቻቸውንም ሰበሰበ፤ እነርሱም ንስሩ ወዳለበት ደረሱ። 6ንስሩም ሬሳው ወዳለበት ወርዶ ረገጠው፤ ሙቱም ተነሣ፤ ይህንም ያደረገ ስለ ተደረገላቸው ተአምራት ሕዝቡ ሁሉ ያምኑና ያደንቁ ዘንድ ነው። 7እነርሱም፥ “ከሙሴ ጋር በምድረ በዳ ሳሉ ለአባቶቻችን የታያቸው አምላካችን እነሆ፥ ይህ ነው፤ ዛሬም በታላቅ ንስር አምሳል ለእኛ የታየን እርሱ ነው” አሉ። 8ንስሩም ኤርምያስን እንዲህ አለው፥ “መጥተህ ይህን ደብዳቤ ከፍተህ ለሕዝቡ አንብብላቸው።” እርሱም ለሕዝቡ አነበበላቸው።
9ሕዝቡም በሰሙ ጊዜ ሁሉም አንድ ሆነው አለቀሱ፤ በራሳቸውም ላይ አመድ ነሰነሱ፤ ኤርምያስንም፥ “ወደ ሀገራችን እንገባ ዘንድ ምን እናድርግ? ንገረን” አሉት። 10ኤርምያስም ተነሥቶ፥ “በደብዳቤ የሰማችሁትን ሁሉ እንደዚሁ አድርጉ ወደ ሀገራችሁም ይመልሳችኋል” አላቸው።
11ኤርምያስም ለባሮክ እንዲህ ብሎ ደብዳቤ ጻፈ፥ “ልጄ ወዳጄ፥ በኀጢአተኛ ንጉሥ ትእዛዝ እስክንወጣ ድረስ ይቅር ይለን ዘንድ፥ ወደ ጎዳናችንም ይመራን ዘንድ ለአምላካችን እየተገዛህ ስለ እኛ መጸለይን ቸል አትበል። 12አንተ ግን ወደ ባቢሎን ተማርከው ከመጡ ወገኖች ጋር ልትመጣ ባልተወህ በአምላክ ፊት ባለሟልነትን አገኘህ። 13አንድ ልጅ እንዳለው አባት፥ ልጁም ይፈረድበት ዘንድ እንደ ተሰጠ፥ የሚያረጋጉት በአባቱ ዘንድ ያሉት ሰዎችም አባቱ በኀዘን ሲጐሰቍል እንዳያዩት ፊታቸውን እንደሚሸፍኑ፥ 14እንደዚሁ አምላክህ አንተን ይቅር አለህ፤ እኛም ወደዚህ ሀገር ከደረስን ጀምሮ እስከ ዛሬ ከኀዘን አላረፍንምና የሕዝቡን መከራ እንዳታይ ወደ ባቢሎን ትመጣ ዘንድ አልተወህም። ወደዚህ ሀገር ከመጣን ጀምሮ ለስድሳ ስድስት ዓመታት ከኀዘን አላረፍንም። 15ወደ ንጉሡ ወደ ናቡከደነፆርም አንጋጠው እያለቀሱ “አቤቱ፥ የሶሮት አምላክ ሆይ፥ ይቅር በለን” የሚሉ ከሕዝቡ አገኘን።
16እኒህ ያዘኑ ሰዎች ሌላውን አምላክ ሲጠሩ “ይቅር በለንም” ሲሉ ይህን ነገር በሰማሁ ጊዜ አዝኜ አለቀስሁ። 17ዳግመኛም እኔ ሳንማረክ በኢየሩሳሌም ያደረግነውን በዓል ዐሰብሁ፤ ይህንም ዐስቤ እየተጨነቅሁና እያለቀስሁ ወደ ቤቴ እመለስ ነበር። 18አሁንም ከፋርስ ሀገር እንዲወጡ ቃሌን ይሰሙ ዘንድ፥ ከአፌ የወጣውንም ነገር ይቀበሉ ዘንድ ስለ ወገኖቻችን አቤሜሌክና አንተ ባላችሁበት ቦታ ፈጣሪያችንን ለምኑ። 19አሁንም በኖርንበት ዘመን ሁሉ “ፈጣሪያችሁ በጽዮን ከሚመሰገንበት ምስጋና ወገን አዲስ ምስጋናን ንገሩን” ብለው ያዙን ብዬ እነግርሃለሁ። 20እኛም፥ “በባዕድ ሀገር ሳለን እንደ ምን እንዘምርላችኋለን?” አልናቸው።
21ኤርምያስም እንደዚሁ አድርጎ ጽፎ ደብዳቤውን በንስሩ አንገት አስሮ “በሰላም ሂድ፤ ጌታም አንተን ይጐብኝህ” አለው። 22ንስሩም ደብዳቤውን ይዞ በርሮ ሄደ፤ ደብዳቤውንም ወደ ባሮክ አደረሰ፤ ባሮክም ደብዳቤውን ከፍቶ አነበበው፤ የሕዝቡንም ኀዘንና መከራ በሰማ ጊዜ አለቀሰ።
23ኤርምያስ ግን ያን በለስ ተቀብሎ በሕዝቡ ዘንድ ላሉ በሽተኞች ሰጣቸው። 24የባቢሎንንም አሕዛብ ርኵሰት እንዳይሠሩ እያስተማራቸው ተቀመጠ። 25እግዚአብሔርም ሕዝቡን ከባቢሎን የሚያወጣባት ቀን በደረሰች ጊዜ፥ 26ጌታ ኤርምያስን እንዲህ አለው፥ “አንተ ተነሥ፤ ወገኖችህም ይነሡ፤ ወደ ዮርዳኖስም ኑ፤ ለሕዝቡም የባቢሎንን ሕዝብ ሥራ ይተዉ ዘንድ ጌታ ይወዳል በላቸው። 27ከእናንተ ሴቶችን ያገባ ወንድን፥ ወንዶችን ያገቡ ሴቶችንም ፈትናቸው፤ ቃልህን የሰሙ ሰዎችን ወደ ኢየሩሳሌም መልሳቸው፤ ያልሰሙህን ሰዎች ግን ወደ እርሷ ይገቡ ዘንድ አትተዋቸው።”
28ኤርምያስም እንዲሁ ይህን ሁሉ አነበበላቸው፤ ሊፈትናቸውም ወደ ዮርዳኖስ አመጣቸው፤ ጌታም ያላቸውን ይህን ነገር ሲነግራቸው ያገቡ ሰዎች ተለያዩ፤ ሊፋቱም አልወደዱም፤ ኤርምያስንም አልሰሙትም።
29“ሚስቶቻችንን ለዘለዓለሙ አንተውም፤ ከእኛ ጋራ ወደ ሀገራችን እንወስዳቸዋለን” ያሉ ሰዎችም ነበሩ፤ ከዮርዳኖስም ተሻግረው ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። 30ኤርምያስና ባሮክ፥ አቤሜሌክም “ከባቢሎን ሴት ያገባ ሰው ሁሉ ወደ ሀገራችን አይገባም” ብለው ተነሡ። 31ሚስት ያገቡ ሰዎችም ባልንጀሮቻቸውን፥ “ተነሡ፤ ወደ ባቢሎን እንመለስ” አሏቸው ወደ ባቢሎንም ተመልሰው ሄዱ። 32የባቢሎንም ሰዎች ባዩአቸው ጊዜ ሊቀበሏቸው ወጡ፤ “እናንተ አስቀድማችሁ እኛን ጠልታችሁናልና ከእኛ ተሰውራችሁ ወጣችሁ” ብለው ወደ ባቢሎን ይገቡ ዘንድ አልተዉአቸውም። 33“ከእኛ ተሰውራችሁ ስለ ወጣችሁ እናንተንና ሴቶች ልጆቻችሁን እንዳንቀበላችሁ በአምላካችን ስም ምለናልና ስለዚህ ነገር በደላችሁ፤ ወደ ሀገራችንም አትገቡም” አሏቸው።
34እንደዚያም ያለውን ቃል ሰምተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በኢየሩሳሌምም አውራጃ ከተማ አቀኑ፤ ያንም ከተማ ሰማርያ አሉት። 35ኤርምያስም “ንስሓ ግቡ፤ እነሆ፥ የጽድቅ መልአክ ይመጣል፤ ለብዙ ዘመንም ወደምትኖሩበት ቦታችሁ ይመልሳችኋል” ብሎ ወደ እነርሱ ላከ። እነርሱም ደስ ብሏቸው ስለ ሕዝቡ መሥዋዕት እየሠዉ ሰባት ቀን ተቀመጡ።
36ይህም ከተደረገ በኋላ በዐሥረኛው ቀን ኤርምያስ ብቻውን ወጣ። 37ኤርምያስም እንዲህ ብሎ ጸለየ፥ “ለሰው በጎ መዓዛ የምትሆን አንተ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ ወደ አንተ እስክደርስ ድረስ ዕውቀትን የምትገልጥልኝ እውነተኛ ዐዋቂ አንተ ነህ። 38ስለ ወገኖችህ ስለ እስራኤልም እለምንሃለሁ፤ ስለ ተወደደው ስለ ሱራፌል ምስጋና፥ በጎ መዓዛ ስላለው ስለ ኪሩቤልም ዕጣን እለምንሃለሁ፤ የጽድቅ ሊቀ መላእክት ሚካኤልም በእውነት አመስጋኝ ነው፤ የሚያበራልኝ፥ ጻድቃንም እስከ ገቡባቸው ድረስ የጽድቅ በሮችን የሚከፍትልኝ እርሱ ነው። 39የሁሉ ጌታ አቤቱ፥ እለምንሃለሁ፤ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አንተ ነህ፤ የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ ፈጥረህ የጨረስህ፥ የተሰወረው ሁሉ፥ ሳይፈጠርም ተሰውሮ የነበረው ሁሉ በአንተ ዘንድ አለ።”
40ይኽንም ጸለየ፤ ጸሎቱንም ከፈጸመ በኋላ ኤርምያስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ#“ወደ መሠዊያው ገብቶ ...” የሚል ዘርዕ አለ። ቆመ፤ ባሮክና አቤሜሌክም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ኤርምያስም ነፍሱ ከሥጋው እንደ ተለየች እንደ አንድ ሰው ሆነ። 41ያንጊዜም ባሮክና አቤሜሌክ ወድቀው በታላቅ ድምፅ ጮሁ፤ “ወዮልን! የአምላክ ካህን አባታችን ኤርምያስ ከእኛ ተለየ” አሉ። 42ሕዝቡም እንዲህ ሰምተው ወደ እርሱ ሮጡ፤ ኤርምያስንም ወድቆ እንደ ሞተም ሆኖ አገኙትና አለቀሱ፤ ልብሶቻቸውንም ቀደዱ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ፤ መራራ ልቅሶንም አለቀሱ።
43የሚቀብሩበትንም ካዘጋጁ በኋላ “ደኅና ነውና ነፍሱም ዳግመኛ ወደ ሥጋው ትመለሳለችና አትገንዙት” የሚል ቃል መጣ። 44ይህንም ቃል በሰሙ ጊዜ ዳግመኛ ነፍሱ ወደ ሥጋው እስክትመለስ ድረስ እየጠበቁት ሦስት ቀን በዙሪያው ተቀመጡ እንጂ አልገነዙትም። 45በሁሉም መካከል እንዲህ የሚል ቃል ተሰማ፤ “በአንድ ቃል አመስግኑት፤ አምላካችንን አመስግኑት፤ ሁላችሁም የአምላክን ልጅ መሢሑን አመስግኑት። 46የዓለሙ ሁሉ ብርሃን የአምላክ ልጅ ኢየሱስም ይፈርድባችኋል። 47የማይጠፋ ብርሃን፥ የሃይማኖትም ሕይወት ነው። 48ከዚህ ዘመን በኋላም ወደ ምድር ለመምጣቱ ሦስት መቶ ሠላሳ ሦስት የቀን ሱባዔ ይሆናል።
49“በገነት መካከል ያለ ያልተተከለ የሕይወት ዛፍ፥ ዛፎችን ሁሉ ፍሬ እንዲያፈሩ፥ የደረቁትም ወደ እርሱ እንዲመጡ ያደርጋቸዋል። 50ፍሬ እንዲያፈሩ፥ እንዲለመልሙና እንዲያድጉም ያደርጋቸዋል፤ ሥሩ ምድርን እንዳልያዘ ተክል ሥራቸው እንዳይደርቅ ለሰማያዊ አምላክ ግብርን እንስጥ፤ ቀይ መልክ ያለው ቀለምም እንደ ባዘቶ ይነጣል። 51የጣፈጠው ውኃ መራራ ይሆናል፤ መራራውም የጣፈጠ ይሆናል፤ በልጁም አንደበት ፍሬን ያፈሩ ዘንድ እግዚአብሔር በታላቅ ሐሤትና ደስታ ደሴቶችን ይመርቃቸዋል። 52እርሱም ራሱ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም ይመጣል፤ እኔ ሰው ሆኖ ያየሁት፥ ከአባቱም ወደዚህ ዓለም የሚላከው፥ ሰው ሆኖም ወደዚህ ዓለም የሚመጣው፥ እርሱ አብሯቸው ይታይ ዘንድ፥ ይገለጥላቸውም ዘንድ ዐሥራ ሁለት ሐዋርያትን ለእርሱ ይመርጣል፤ ወደ ደብረ ዘይትም ይሄዳል፤ የተራበችንም ነፍስ ሁሉ ያጠግባል።” 53ወደዚህ ዓለም እንደሚመጣ ኤርምያስ የአምላክን ልጅ ነገር እንዲህ ተናገረ።
54ሕዝቡም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ኤርምያስ፥ “የአምላክን ልጅ አምላክን አየሁት” ብሎ ስለ ተናገረው ስለዚህ ነገር ተቈጡ፤ እነሆም፥ “በኢሳይያስ እንዳደረግን በእርሱም እናድርግበት፤ ተነሡ” አሉ። እኩሌቶቹ፥ “በደንጊያ ወግረን እንግደለው እንጂ አይሆንም” አሉ። 55ባሮክና አቤሜሌክም፥ “በዚች ሞት አትግደሉት” ብለው ጮሁላቸው፤ ባሮክና አቤሜሌክም ስለ ኤርምያስ አዘኑ። 56ዳግመኛም ያያቸውን የተሰወሩ ምሥጢሮችን ይነግራቸው ዘንድ አልተዉትም፤ ኤርምያስም፥ “ያየሁትን ሁሉ እስካስተምራችሁ ድረስ እኔን መግደል አይችሉምና አታልቅሱ” አላቸው። 57“አሁንም አንዲት ድንጋይ አምጡልኝ፤” አላቸው፥ እነርሱም አንዲት ድንጋይ አመጡለት፤ እርሱም አቆማት፤ “የዘለዓለም ብርሃን ሆይ፥ ይህቺን ድንጋይ እንደ እኔ ትሆን ዘንድ አድርግልኝ” አለ። 58ያንጊዜም ድንጋዩ ኤርምያስን በመልክ የሚመስለው ሆነ፤ ኤርምያስንም መሰላቸውና ድንጋዩን በድንጋይ ይደበድቡ ጀመር፤ ወንጀልንም ጨረሱ። 59ኤርምያስ ግን ያያቸውን ምሥጢሮች ሁሉ ለባሮክና ለአቤሜሌክ ነገራቸው፤ ይህንም ነግሯቸው ከጨረሰ በኋላ ምግብናውን ይፈጽም ዘንድ ወደደ፤ ሄዶም በሕዝቡ መካከል ቆመ።
60ያንጊዜም ያ ድንጋይ፥ “እናንት ሰነፎች የእስራኤል ልጆች፥ ኤርምያስን መስያችሁ በድንጋይ ስለ ምን ትደበድቡኛላችሁ? ኤርምያስስ እነሆ በመካከላችሁ ቁሟል” ብሎ ጮኸ። 61ኤርምያስንም ባዩት ጊዜ ብዙ ድንጋይ ይዘው ወደ እርሱ ሮጡ፤ እርሱም ምስክርነቱን ጨረሰ፤ ባሮክና አቤሜሌክም መጥተው ቀበሩት፤ ያንም ድንጋይ አምጥተው በመቃብሩ አፍ እንደ መዝጊያ አድርገው አኖሩት። 62“የኤርምያስ ረዳቱ እነሆ፥ ይህ ድንጋይ ነው” ብለው በውስጡ ጻፉ፤ የኤርምያስም የቀረች ነገሩ እነሆ፥ በባሮክ መጽሐፍ ተጽፋለች።
Currently Selected:
ተረፈ ባሮክ 5: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ