ተረፈ ባሮክ 4
4
1አቤሜሌክም ተነሥቶ ከከተማ ወደ ውጭ ከወጣ በኋላ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 2እነሆም፥ መልአክ መጥቶ ወደ ባሮክ መራው፤ በመቃብር ቤትም ተቀምጦ አገኘው። 3ሰላምታም በተሰጣጡ ጊዜ እርስ በርሳቸው ተለቃቅሰው ተሳሳሙ፤ በሙዳዩም ውስጥ በለሱን አይቶ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አቀና። 4እንዲህም ብሎ ጸለየ፤ “ለወዳጆቹ ለጻድቃን ዋጋቸውን የሚሰጣቸው አምላክ ገናና ነው፤ ነፍሴ ሆይ፥ ተዘጋጂ፤ ለቅዱስ ማደሪያሽ ለሥጋ ይህን እየነገርሽ ደስ ይበልሽ፤ ልቅሶሽም ወደ ደስታ ይመለስልሻል። 5ከዚያም በኋላ የታመነው ይመጣል፤ ወደ ሬሳሽም ይመልስሻል፤ ድንግል ወደ ሆነው ወደ ሃይማኖትሽም ተመልከች። 6እንደምትነሺም ወደ እነዚህ በለሶች ተመልከች፤ ከተለቀሙ ስድሳ ስድስት ዓመት ነው፤ አልደረቁም፤ አልተሉምም፤ ነገር ግን ወተታቸው እስከ ዛሬ ገና ይፈስሳል። 7ኀጢአት የለብሽምና፥ የበለሱን ሙዳይ ከጠበቀ ከእውነተኛው መልአክም ዘንድ የታዘዝሺውን ትእዛዝ ጠብቀሻልና ሥጋዬ በአንቺ እንዲህ ያደርጋል፤ እርሱም ዳግመኛ በኀይሉ ይጠብቅሻል።”
8ባሮክም እንዲህ ብሎ ከጸለየ በኋላ አቤሜሌክ መለሰ፤ “እኔን የሰወረ እግዚአብሔር ለኤርምያስ ወደ ባቢሎን የምንጽፋቸውን ቃሎች ይገልጥልን ዘንድ ዳግመኛ ተነሥተህ ጸልይ” አለው። 9ባሮክም ጸለየ፤ እንዲህም አለ፥ “ኀያል አምላክ፥ ብርሃንም ከአፍህ የሚወጣ ጌታ ሆይ፥ እለምንህ ዘንድ እወድዳለሁ፤ 10ለቸርነትህም እገዛለሁ፤ ስምህም ገናና ነው፤ እርሱንም መርምሮ ማወቅ የሚቻለው የለም። 11በልቡናዬ ፈቃድህን ለማድረግ በደግነት የታወቅሁ እሆን ዘንድ፥ ለአገልጋይህ ለኤርምያስም ወደ ባቢሎን ጽፌ እልክ ዘንድ የኔን የባሪያህን ልመና ስማ።” 12ይህንም ሲጸልይ መልአኩ መጥቶ ለባሮክ እንዲህ አለው፥ “ብሩህ ነገርን የምትመክር ባሮክ ሆይ፥ አንተ ወደ ኤርምያስ ትልክ ዘንድ ማንን እልካለሁ? ብለህ አታስብ። 13ነገ ፀሐይ ሲወጣ ንስር ወደ አንተ ይመጣል፤ ወደ ኤርምያስም የምትልከውን ነገር አንተ መርምር፤ በመጽሐፍም ጻፍ።”
14የእስራኤልን ልጆች እንዲህ በላቸው፥ “በእናንተ ዘንድ እንግዳ ሰው ቢኖር እስከ ዐሥራ አምስት ቀን ድረስ ከእናንተ ይለይ። 15ከዚህም በኋላ ወደ ሀገራችሁ አገባችኋለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ እስከ ዐሥራ አምስት ቀንም ድረስ ከባቢሎን ያልተለየ ሰው ቢኖር ኤርምያስ ወደ ከተማ ገብቶ በባቢሎን ያሉ እስራኤልን ይዝለፋቸው፤ ይላል እግዚአብሔር።”
16ይህንም ከተናገረ በኋላ መልአኩ ከባሮክ ዘንድ ሄደ። ባሮክም እስከ አደባባዩ ድረስ ሸኘው፤ ወረቀትና ጥቁር ቀለምም አመጣ። 17የእግዚአብሔር አገልጋዩ ባሮክ እንዲህ ብሎ ደብዳቤ ጻፈ፥ “ስለ ስድባችንና ስለ ጥፋታችን ያዘንን ሆነን እንወጣ ዘንድ ፈጣሪያችን አልተወንምና ወደ ባቢሎን ለተማረከው ለኤርምያስ ደስታና ሐሤት ይሁን። 18ስለዚህ ነገር ጌታችን እንባችንን አይቶ አዘነልን፤ አስቀድሞ ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለይስሐቅ፥ ለያዕቆብም ያጸናውን ቃል ኪዳን ዐሰበ። 19መልአኩንም ወደ እኔ ልኮ ወደ አንተ የላክሁብህን ነገሮች ነገረኝ።
20“ከግብፅ ምድርና ከእሳት ቤቶች ያወጣን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ያደረጋቸው ነገሮች እኒህ ናቸው፤ ልቡናችሁን ከፍ ከፍ አደረጋችሁ፤ በፊቱም አንገታችሁን አደነደናችሁ እንጂ ሕጉን ሁሉ አልጠበቃችሁምና። 21እግዚአብሔር ከወዳጄ ከኤርምያስ አፍ ቃሌን አልሰማችሁም ብሏልና ለባቢሎን አገዛዝ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ ቃሌን የሰሙ ሰዎችን ግን ከባቢሎን አወጣቸዋለሁ፤ ከባቢሎንም ወጥተው በኢየሩሳሌም እንግዳ አይሆኑም። 22መንገዳቸውንም ልታውቅባቸው ብትወድድ በዮርዳኖስ ውኃ ፈትናቸው፤ የዚህን ደብዳቤ ምልክት ያልሰማ ሰው ግን የበለጠ ምልክት ማኅተም አለ።”
23ባሮክም እንዲህ ጽፎ ከመቃብር ቤት ወጣ፤#“ከመቃብሩም ውጭ ንስሩን ተቀምጦ አገኘውና በሰው ቋንቋ አነጋገረው” የሚል ዘርዕ ይገኛል። ንስሩም፥ “ሃይማኖትን የምታስተምር ባሮክ ሆይ፥ ቸር አለህን?” አለው። 24ባሮክም፥ “ከሰማይ አዕዋፍ ሁሉ የተመረጥህ ነህና፥ በዐይኖችህም ብርሃን የታወቅህ ነህና ትናገራለህ። 25አሁንም በዚህ ምን ልታደርግ መጣህ? ንገረኝ” አለው። ንስሩም፥ “የወደድኸውን ሁሉ ልትልከኝ ወደዚህ መጣሁ” አለው። 26ባሮክም፥ “እነዚህን ነገሮች ለኤርምያስ ወደ ባቢሎን ማድረስ ትችላለህን?” አለው፤ ንስሩም፥ “ስለዚህ ተላክሁ” አለው።
27ባሮክም ደብዳቤውን ያዘ፤ ከዚያ አቤሜሌክ ከሰጠው ከበለሱ ሙዳይም ዐሥራ አምስቱን በለስ አምጥቶ በንስሩ አንገት አሰረ። 28“የአዕዋፍ ሁሉ ንጉሣቸው ንስር ሆይ፥ በሰላምና በደኅና ሂደህ ወሬያቸውን አምጣልን እልሃለሁ አለው። 29ኖኅ የላከውን፥ ዳግመኛም ወደ እርሱ መመለስን እንቢ ያለውን ቁራ አትምሰለው። ነገር ግን ለኖኅ ቃሏን ሦስት ጊዜ የመለሰች ርግብን ምሰላት። 30እንደዚሁም ሁሉ ለአንተ በጎ ነገር ይሆንህ ዘንድ እኒህን ያማሩ ነገሮች ለኤርምያስና ከእርሱ ጋራ ላሉ እስራኤል ውሰድ፤ አምላክ ለመረጣቸው ወገኖች ይህን ደስታ ንገራቸው። 31አዕዋፍም ሁሉ ቢከብቡህ፥ ይገድሉህም ዘንድ ወድደው የጽድቅ ጠላቶች ሁሉ ቢከብቡህ ስለ እውነት ቀድመሃቸው ሂድ። 32ጌታም ኀይልን ይሰጥሃል፤ የተወረወረ ፍላጻ ቀንቶ እንዲሄድ አንተም በፈጣሪህ ኀይል ቀንተህ ሂድ እንጂ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል” አለው።
Currently Selected:
ተረፈ ባሮክ 4: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ