መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 8
8
ዳዊት በጦርነት ያገኘው ድል
(1ዜ.መ. 18፥1-17)
1ከዚህም በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን መታ፤ አዋረዳቸውም፤ ዳዊትም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ምርኮን#ዕብ. “ሜቴግ አማ” ይላል። ወሰደ።
2ዳዊትም ሞዓባውያንን መታ፤ በምድርም ጥሎ በገመድ ሰፈራቸው፤ በሁለትም ገመድ ለሞት፥ በአንድም ገመድ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በሁለት ...” ይላል። ለሕይወት ሰፈራቸው፤ ሞዓባውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት።
3ዳዊትም ደግሞ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ግዛት ለማስፋፋት በሄደ ጊዜ የሱባን ንጉሥ የረአብን ልጅ አድርአዛርን መታ። 4ዳዊትም ከእርሱ ሺህ ሰረገላዎችን፥ ሰባት ሺህ ፈረሰኞችን፥ ሃያ ሺህም እግረኞችን ያዘ፤ ዳዊትም የሰረገለኛውን ፈረስ ሁሉ ቋንጃ ቈረጠ፤ ለራሱም መቶ ሰረገላዎችን ብቻ አስቀረ። 5ከደማስቆም ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ሊረዱ መጡ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሃያ ሁለት ሺህ ሰዎችን ገደለ። 6ዳዊትም በደማስቆ ሶርያ ጭፍሮች አኖረ፤ ሶርያውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት፤ እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ጠበቀው። 7ዳዊትም ለሱባን ንጉሥ ለአድርአዛር አገልጋዮች የነበሩትን ጋሻ አግሬዎች ወሰደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጣቸው።#የሚቀጥለው ዐ. ነገር በግሪክ ሰባ. ሊ. ብቻ ነው። እነዚህንም የግብፅ ንጉሥ ሱስቀም በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ዘመን ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ወሰዳቸው። 8ንጉሡም ዳዊት ከሶቤቅና ከተመረጡት ከአድርአዛር ከተሞች እጅግ ብዙ ናስን ወሰደ። በእርሱም ሰሎሞን የብረት ባሕርና ምሰሶዎችን፥ ሰኖችንና ሌሎች ዕቃዎችን ሠራ።
9የሓማትም ንጉሥ ታይ ዳዊት የአድርአዛርን ጭፍራ ሁሉ እንደ መታ ሰማ። 10ታይም የአድርአዛር ጠላት ነበርና ዳዊት አድርአዛርን ስለ ተዋጋውና ስለ ገደለው፥ ታይ ልጁን ኢያዱራን ደኅንነቱን ይጠይቅ ዘንድ፥ ይመርቀውም ዘንድ ወደ ንጉሥ ዳዊት ላከው፤ እርሱም የብርና የወርቅ የናስም ዕቃ ይዞ መጣ፤ 11እርሱንም ንጉሥ ዳዊት ከሀገሮች ሁሉ አምጥቶ ከቀደሰው ከወርቁና ከብሩ ጋር ለእግዚአብሔር ቀደሰ፤ 12ይኸውም ከሶርያ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ኤይም” ይላል። ከሞዓብና ከአሞን ልጆች፥ ከፍልስጥኤማውያንም፥ ከአማሌቅም፥ ከረአብም ልጅ ከሱባ ንጉሥ ከአድርአዛር ምርኮ ያመጣው ነው።
13ዳዊትም በተመለሰ ጊዜ ከኤዶምያስ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች በጨው ሸለቆ ውስጥ በመምታቱ ስሙ ተጠራ። 14መላዋን ኤዶምያስን ይጠብቁ ዘንድ በኤዶምያስ ሁሉ ጭፍሮችን አኖረ፤ ኤዶማውያንም ሁሉ ለንጉሥ ዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ እግዚአብሔርም ዳዊትን በሚሄድበት ቦታ ሁሉ ጠበቀው።
15ዳዊትም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ዳዊትም ለሕዝቡ ሁሉ ፍርድንና ጽድቅን አደረገላቸው። 16የሦርህያ ልጅ ኢዮአብም የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ የአሒሎድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሓፊ ነበረ፤ 17የአኪጦብም ልጅ ሳዶቅ፥ የአቤሜሌክም ልጅ አብያታር ካህናት ነበሩ። አሳም ጸሓፊ ነበረ፤ 18የዮዳሄ ልጅ በናያስም አማካሪ ነበረ፤ ከሊታውያንና፥ ፊሊታውያን፥ የዳዊትም ልጆች የፍርድ ቤት አለቆች ነበሩ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 8: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ