መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 7
7
ዳዊት የእግዝ!አብሔርን ቤት ለመሥራት እንደ አሰበ
(1ዜ.መ. 17፥1-15)
1እንዲህም ሆነ፤ ንጉሡ በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ እግዚአብሔርም በዙሪያው ያሉ ጠላቶቹን ሁሉ ባወረሰው ጊዜ፥ 2ንጉሡ ነቢዩ ናታንን፥ “እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጬአለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ተቀምጣለች” አለው። 3ናታንም ንጉሡን፥ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና፥ ሂድና በልብህ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” አለው። 4በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ፤ እንዲህም አለው፦ 5“ሂድ ለባሪያዬ ለዳዊት ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም። 6የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ እሄድና እመላለስ ነበር እንጂ በቤት አልተቀመጥሁምና፥ 7ከእስራኤል ልጆች ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ፦ ስለምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም? ብዬ ሕዝቤን እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን? 8አሁንም ዳዊትን ባሪያዬን እንዲህ በለው፦ ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ፤ 9በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆቹ ስም ስምህን ታላቅ አደረግሁ። 10ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርጋለሁ፤ እተክላቸውማለሁ፤ ብቻቸውን ይቀመጣሉ፤ ከዚያም በኋላ የሚጠራጠሩት የለም፤ እንደ ቀድሞው ዘመን የኀጢአት ልጅ መከራ አያጸናባቸውም። 11በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፈራጆችን በሾምሁ ጊዜ ከጠላቶችህ ሁሉ አሳርፍሃለሁ። እግዚአብሔርም ደግሞ፦ ቤት እንደምትሠራለት ይነግርሃል፤ እሠራለታለሁ ብለሃልና። 12ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ፤ ከአባቶችህም ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ፥ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፤ መንግሥቱንም አዘጋጃለሁ ። 13እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፤ ዙፋኑን ለዘለዓለም አጸናለሁ። 14እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ክፉ ነገርም ቢያደርግ፥ በሰዎች በትርና በሰው ልጆች አለንጋ እገሥጸዋለሁ፤ 15ከፊቴም ከጣልሁት ከሳኦል ቤት እንዳራቅሁ ምሕረቴን ከእርሱ አላርቅም። 16ቤቱ የታመነ ይሆናል፤ መንግሥቱም በፊቴ ለዘለዓለም፥ ዙፋኑም ለዘለዓለም ይጸናል።” 17እንደዚህ ቃል ሁሉ፥ እንደዚህም ራእይ ሁሉ ናታን ለዳዊት እንዲሁ ነገረው።
የዳዊት የምስጋና ጸሎት
(1ዜ.መ. 17፥16-27)
18ንጉሡ ዳዊትም ገባ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፥ “ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህን ያህል የወደድኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው? 19ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እኔ በፊትህ እጅግ ታናሽ ስሆን ስለ ባሪያህ ቤት ደግሞ ለሩቅ ዘመን ተናገርህ፤ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ የሰው ሕግ ነው። 20ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ባሪያህን ታውቃለህና ዳዊትስ ይናገርህ ዘንድ የሚጨምረው ምንድን ነው? 21ለባሪያህም ታስታውቀው ዘንድ ስለ ቃልህ ምክንያትና እንደ ልብህ አሳብ ይህን ታላቅ ነገር ሁሉ አደረግህ። 22ስለዚህም አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እንዳንተ ያለ የለምና፥ በጆሮአችንም እንደ ሰማን ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለምና አንተ ታላቅ ነህ። 23ለእርሱ ለራሱ እንዲሆን ሕዝብን ይቤዥ ዘንድ ለእርሱ ለራሱም ታላቅ ስምን ያደርግ ዘንድ አሕዛብንና ሰፈሮቻቸውን በመበተን ከግብፅ በተቤዠኸው ሕዝብህ ፊት ታምራትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ መራው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ? 24ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘለዓለም ሕዝብ አድርገህ አዘጋጅተኸዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ አምላክ ሆነሃቸዋል። 25አቤቱ ሁሉን የምትገዛ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አሁንም ለባሪያህና ለቤቱ የተናገርኸውን ለዘለዓለም አጽናው፤ አሁንም እንደ ተናገርህ አድርግ። 26ስምህ ለዘለዓለም ታላቅ ይሁን።#ዕብ. “ሁሉን የሚችል የእስራኤል አምላክ ነው ይባል ዘንድ ... የባሪያህ የዳዊት ቤትም በፊትህ የጸና ይሁን” የሚል ይጨምራል። 27አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያህን ጆሮ ከፈትህ። አንተ፦ እኔ ቤት እሠራልሃለሁ አልህ፤ ስለዚህም ባሪያህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ይጸልይ ዘንድ በልቡ አሰበ። 28ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አሁንም አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህም እውነት ነው፤ ይህንም መልካም ነገር ለባሪያህ ተናግረሃል። 29ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ተናግረሃልና አሁን እንግዲህ ለዘለዓለም በፊትህ ይሆን ዘንድ የባሪያህን ቤት እባክህ ባርክ፤ በበረከትህም የባሪያህ ቤት ለዘለዓለም ይባረክ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 7: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ