ከዚያም በኋላ ዳዊት፥ “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፥ “ውጣ” አለው። ዳዊትም፥ “ወዴት ልውጣ?” አለ። እርሱም፥ “ወደ ኬብሮን ውጣ” አለው። ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቤግያ ጋር ወደዚያ ወደ ኬብሮን ወጣ። ከእርሱም ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ ከቤተ ሰባቸው ጋር ወጡ፤ በኬብሮንም ከተሞች ተቀመጡ። የይሁዳም ሰዎች መጥተው በይሁዳ ቤት ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን በዚያ ቀቡት። ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ናቸው ብለው ለዳዊት ነገሩት። ዳዊትም ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ገዦች መልእክተኞችን ላከ፤ ዳዊትም እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ እግዚአብሔር ለቀባው ለጌታችሁ ለሳኦል ይህን ቸርነት አድርጋችኋልና፥ እርሱንና ልጁን ዮናታንንም ቀብራችኋቸዋልና በእግዚአብሔር የተባረካችሁ ሁኑ። አሁንም እግዚአብሔር ምሕረትንና ጽድቅን ያድርግላችሁ፤ ይህንም ነገር አድርጋችኋልና እኔ ደግሞ ይህን በጎነት እመልስላችኋለሁ። አሁንም ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአልና እጃችሁ ትጽና፤ እናንተም በርቱ፤ የይሁዳም ቤት በእነርሱ ላይ ንጉሥ እሆን ዘንድ ቀብተውኛል።” የሳኦልም ጭፍራ አለቃ የኔር ልጅ አበኔር የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ከሰፈር ወደ መሃናይም አወጣው፤ በገለዓድና በታሲሪ፥ በኢይዝራኤልም፥ በኤፍሬምም፥ በብንያምም፥ በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሠው። የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴም በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ አርባ ዓመት ሆኖት ነበረ፤ ዳዊትን ከተከተሉት ከይሁዳ ወገኖች ብቻ በቀር ሁለት ዓመት ነገሠ። ዳዊትም በይሁዳ ቤት በኬብሮን የነገሠበት ዘመን ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ። የኔር ልጅ አበኔርና የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ብላቴኖች ከመሃናይም ወደ ገባዖን ወጡ። የሶርህያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ብላቴኖች ከኬብሮን ወጥተው በገባዖን ውኃ መቆሚያ አጠገብ ተገናኙአቸው፤ በውኃውም መቆሚያ በአንዱ ወገን እነዚህ፥ በሌላውም ወገን እነዚያ ሆነው ተቀመጡ። አበኔርም ኢዮአብን፥ “ጐልማሶቻችን ይነሡ፤ በፊታችንም ይቈራቈሱ” አለው፤ ኢዮአብም፥ “ይነሡ” አለ። ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ ከብንያም ልጆች ዐሥራ ሁለት፥ ከዳዊትም ብላቴኖች ዐሥራ ሁለት ተቈጥረው ተነሡ። ሁሉም እያንዳንዱ የወደረኛውን ራስ በእጁ ያዘ፤ ሰይፉንም በወደረኛው ጐን ሻጠ፤ ተያይዘውም ወደቁ። የዚያም ስፍራ ስም “በገባዖን የሸመቁ ሰዎች ድርሻ” ተብሎ ተጠራ፤ በዚያም ቀን እጅግ ጽኑ ሰልፍ ሆነ፤ በዳዊትም ሰዎች ፊት አበኔርና የእስራኤል ሰዎች ተሸነፉ። በዚያም ሦስቱ የሦርህያ ልጆች ኢዮአብና አቢሳ፥ አሣሄልም ነበሩ፤ የአሣሄልም እግሮቹ ፈጣኖች ነበሩ፤ እንደ ዱር ሚዳቋም ሯጭ ነበረ። አሣሄልም የአበኔርን ፍለጋ ተከታተለ፤ አበኔርንም ከማሳደድ ቀኝና ግራ አላለም። አበኔርም ወደ ኋላው ተመልሶ፥ “አንተ አሣሄል ነህን?” አለው። እርሱም፥ “አዎ፥ እኔ ነኝ” አለው። አበኔርም፥ “ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ፈቀቅ በል፤ ከብላቴኖቹም አንድ ጐልማሳ ያዝ፤ መሣሪያውንም ለራስህ ውሰድ” አለው። አሣሄል ግን እርሱን ከማሳደድ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ። አበኔርም አሣሄልን፥ “ከምድር ጋር እንዳላጣብቅህ እኔን ከማሳደድ ፈቀቅ በል፤ ወደ ወንድምህ ወደ ኢዮአብ ፊቴን አቅንቼ አይ ዘንድ እንዴት ይቻለኛል? እንደዚህ አይሆንምና ወደ ወንድምህ ወደ ኢዮአብ ተመለስ” አለው። ነገር ግን ከእርሱ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ። አበኔርም በጦሩ ጫፍ ወገቡን ወጋው፤ ጦሩም በኋላው ወጣ፤ በዚያም ስፍራ ወድቆ በበታቹ ሞተ። አሣሄልም ወድቆ በሞተበት ስፍራ የሚያልፍ ሁሉ ይቆም ነበር። ኢዮአብና አቢሳም አበኔርን አሳደዱ፤ ፀሐይም ጠለቀች፤ እነርሱም በገባዖን ምድረ በዳ መንገድ በጋይ ፊት ለፊት እስካለው እስከ አማን ኮረብታ ድረስ መጡ። በአበኔር ኋላ የነበሩ የብንያምም ልጆች ተሰበሰቡ፥ በአንድነትም ሆኑ፤ በአንድ ኮረብታም ራስ ላይ ቆሙ። አበኔርም ኢዮአብን ጠርቶ እንዲህ አለው፥ “ሰይፍ ለድል የምታጠፋ አይደለምን? ፍጻሜዋስ መራራ እንደ ሆነ አታውቅምን? ሕዝቡ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ ይመለሱ ዘንድ ሕዝቡን የማትናገር እስከ መቼ ነው?” ኢዮአብም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ባትናገር ኖሮ ሕዝቡ ሁሉ በጥዋት በወንድሞቻቸው ላይ በወጡ ነበር” አለ። ኢዮአብም ቀንደ መለከት ነፋ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተመለሰ፤ ከዚያም በኋላ እስራኤልን አላሳደዱአቸውም፤ ደግመውም አልተዋጉም። አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ወደ ምዕራብ ሄዱ፤ ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፤ ያን ቀጥተኛ መንገድ ካለፉ በኋላም ወደ ሰፈር መጡ። ኢዮአብም አበኔርን ከማሳደድ ተመለሰ፤ ሕዝቡንም ሁሉ ሰበሰበ፤ የዳዊትንም ብላቴኖች አስቈጠራቸው፤ የሞቱትም ሰዎች ከአሣሄል ሌላ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች ናቸው። የዳዊትም ብላቴኖች ከብንያም እና ከአበኔር ሰዎች ሦስት መቶ ስድሳ ሰዎችን ገደሉ። አሣሄልንም አንሥተው በቤተ ልሔም በአባቱ መቃብር ቀበሩት፤ ኢዮአብና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ፤ ሄዱ፥ በኬብሮንም አነጉ።
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 2 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 2:1-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos