መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 19
19
ኢዮአብ ዳዊትን እንደ ወቀሰው
1ለኢዮአብ፥ “ንጉሡ ስለ አቤሴሎም ያዝናል፤ ያለቅሳልም” ብለው ነገሩት። 2በዚያም ቀን፥ “ንጉሡ ስለ ልጁ አዘነ” ሲባል ሕዝቡ ሰምቶአልና በዚያው ቀን#ዕብ. “የዚያ ቀን ድል ...” ይላል። ሕይወት በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ወደ ኀዘን ተለወጠ። 3ከሰልፍ በሸሸ ጊዜ ያፈረ ሕዝብ ተሰርቆ እንደሚገባ በዚያ ቀን ሕዝቡ ተሰርቀው ወደ ከተማ ገቡ። 4ንጉሡም ፊቱን ሸፈነ፤ ንጉሡም በታላቅ ድምፅ፥ “ልጄ አቤሴሎም፥ አቤሴሎም፥ ልጄ” እያለ ይጮህ ነበር። 5ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ቤት ገብቶ እንዲህ አለ፥ “ዛሬ ነፍስህንና የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን ነፍስ፥ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ነፍስ ያዳኑትን የአገልጋዮችህን ሁሉ ፊት በዚች ቀን አሳፍረሃል። 6አንተ የሚጠሉህን ትወድዳለህ፤ የሚወድዱህንም ትጠላለህ፤ አለቆችህና አገልጋዮችህ እንደማይጠቅሙህ እንደምታስብ ዛሬ ገልጠሃልና፤ አቤሴሎምም ድኖ ቢሆን ዛሬ እኛ ሁላችን እንሞት እንደ ነበር አውቃለሁ። ይህ በፊትህ ላንተ ቀና ነበረና። 7አሁንም ተነሥተህ ወጥተህ ለአገልጋዮችህ በልባቸው የሚገባ ነገር ንገራቸው። ዛሬ ወደ እነርሱ ካልወጣህ በዚች ሌሊት አንድ ሰው ስንኳ ከአንተ ጋር የሚያድር እንዳይኖር በእግዚአብሔር እምላለሁ፤ ከሕፃንነትህ ጀምሮ እስከዚች ቀን ድረስ ካገኘህ መከራ ሁሉ ዛሬ የምታገኝህ መከራ እንድትከፋብህ እንግዲህ አንተ ለራስህ ዕወቅ” አለው። 8ንጉሡም ተነሥቶ በበሩ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ ንጉሡ በበሩ ተቀምጧል ብለው ተናገሩ፤ ሕዝቡም ሁሉ በበሩ ወደ ንጉሡ ፊት ወጡ። እስራኤልም እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሽቶ ገብቶ ነበር።
ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ተመለሰ
9ከመላው ነገደ እስራኤል የተሰበሰቡ ሕዝብ፥ “ንጉሡ ዳዊት ከጠላቶቻችን እጅ ታድጎናል፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አድኖናል፤ አሁንም ስለ አቤሴሎም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከአቤሴሎም” ይላል። ከሀገሩና ከመንግሥቱ ሸሸ። 10በላያችን ላይ የቀባነው አቤሴሎምም በጦርነት ሞቶአል፤ አሁንም ንጉሡን ለመመለስ ስለምን ዝም ትላላችሁ?” አሉ፤ የእስራኤልም ቃል ወደ ንጉሥ ደረሰ።#“የእስራኤልም ቃል ወደ ንጉሡ ደረሰ” የሚለው በዕብ. የለም።
11ንጉሡ ዳዊትም ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ልኮ እንዲህ አላቸው፥ “ለይሁዳ ሽማግሌዎች እንዲህ ብላችሁ ተናገሩአቸው፦ የእስራኤል ሁሉ ነገር ወደ ንጉሡ ደርሶአልና ንጉሡን ወደ ቤቱ ከመመለስ ስለምን ዘገያችሁ? 12እናንተ ወንድሞች፥ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቍራጭ ናችሁ፤ እናንተ ንጉሡን ወደ ቤቱ ከመመለስ ስለምን ዘገያችሁ? 13ለአሚሳይም፦ አንተ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቍራጭ አይደለህምን? በዘመንህም ሁሉ በኢዮአብ ፋንታ በፊቴ የሠራዊት አለቃ ሳትሆን ብትቀር ዛሬ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ይህንም ይጨምርብኝ በሉት።” 14የይሁዳንም ሰዎች ሁሉ ልብ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ አዘነበለ፤ ወደ ንጉሡም፥ “አንተና ብላቴኖችህ፥ አገልጋዮችህም ሁሉ ተመለሱ” ብለው ላኩበት።
15ንጉሡም ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ። የይሁዳ ሰዎችም ንጉሡን ሊቀበሉ፥ ንጉሡንም ዮርዳኖስን ሊያሻግሩ ወደ ጌልገላ መጡ። 16ከባውሪም ሀገር የነበረው#ዕብ. “ብንያማዊ” ይላል። የኢያሚን ልጅ የጌራ ልጅ ሳሚም ከይሁዳ ሰዎች ጋር ንጉሥ ዳዊትን ሊቀበል ፈጥኖ ወረደ። 17ከእርሱም ጋራ ከብንያም ወገን የሆኑ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ የሳኦልም ቤት አገልጋይ ሲባ ከእርሱም ጋር ዐሥራ አምስቱ ልጆቹና ሃያው አገልጋዮቹ ነበሩ፤ በንጉሡም ፊት በቀጥታ ወደ ዮርዳኖስ ሄዱ። 18ንጉሡንም የማሻገር ሥራ ሠሩ። የንጉሡንም ቤተ ሰብእ ያነሡ ዘንድ፥ በፊቱም የቀና ሥራን ይሠሩ ዘንድ ወደ ማዶ ተሻገሩ። ንጉሡም ዮርዳኖስን ከተሻገረ በኋላ የጌራ ልጅ ሳሚ በንጉሡ ፊት፦ በግንባሩ ወደቀ።
ዳዊት ለሳሚ ይቅርታ እንደ አደረገለት
19እርሱም ንጉሡን አለው፥ “ጌታዬ! ኀጢአቴን አትቍጠርብኝ፤ ጌታዬ ንጉሡ ከኢየሩሳሌም በወጣህ ቀን ባሪያህ የበደልሁህን አታስብብኝ፤ ጌታዬ ንጉሡም በልብህ አታኑርብኝ። 20እኔ አገልጋይህ በደለኛ እንደ ሆንሁ አውቄአለሁና እነሆ፥ ከዮሴፍ ቤት ሁሉ አስቀድሜ ዛሬ መጣሁ፤ ጌታዬንም ንጉሡን ልቀበል ወረድሁ።” 21የሶርህያ ልጅ አቢሳ ግን፥ “ሳሚ እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና እንግዲህ ሞት የተገባው አይደለምን?” ብሎ መለሰ። 22ዳዊትም፥ “እናንተ የሶርህያ ልጆች! ዛሬ ታስቱኝ ዘንድ በእኔና በእናንተ መካከል ምን አለኝ? ዛሬስ ከእስራኤል የሚሞት አንድ ሰው የለም። ዛሬስ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሥሁ አላውቅምን?” 23ንጉሡም ሳሚን፥ “አትሞትም” አለው። ንጉሡም ማለለት።
ዳዊት ለሜምፌቡስቴ ይቅርታ እንደ አደረገለት
24የሳኦልም የልጅ ልጅ ሜምፌቡስቴ ንጉሡን ሊቀበል ወረደ፤ ንጉሡም ከሄደበት ቀን ጀምሮ በሰላም እስከ ተመለሰበት ቀን ድረስ እግሩን አላነጻም፤ ጥፍሩንም አልቈረጠም፤ ጢሙንም አልላጨም፤ ልብሱንም አላጠበም ነበር። 25ከዚህም በኋላ ንጉሡን ሊቀበለው ከኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፥ “ሜምፌቡስቴ፥ ከእኔ ጋር ስለምን አልወጣህም?” አለው። 26ሜምፌቡስቴም አለ፥ “ጌታዬ፥ ንጉሥ፥ አገልጋዬ አታለለኝ፥ እኔ ባሪያህ አንካሳ ነኝና፦ ከንጉሡ ጋር እሄድ ዘንድ አህያዬን ጫንልኝ፤ እኔም እቀመጥበታለሁ አልሁት። 27እርሱም በእኔ በባሪያህ ላይ ክፉ አደረገ፤ አንተ ጌታዬ ንጉሥ ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነህ፤ በፊትህም ደስ ያሰኘህን አድርግ። 28የአባቴ ቤት ሁሉ በጌታዬ በንጉሥ ዘንድ ሞት የሚገባቸው ነበሩ፤ አንተ ግን እኔን ባሪያህን በገበታህ በሚበሉ መካከል አስቀመጥኸኝ፤ ለንጉሥ ደግሞ ለመናገር ምን መብት አለኝ?” 29ንጉሡም፥ “ነገርህን ለምን ታበዛለህ? አንተና ሲባ የሳኦልን እርሻውን ትካፈሉ ዘንድ ብያለሁ” አለው። 30ሜምፌቡስቴም ንጉሡን፥ “ጌታዬ ንጉሡ በደኅና ወደ ቤቱ ከተመለሰ እርሱ ሁሉን ይውሰደው” አለው።
31ገለዓዳዊውም ቤርዜሊ ከሮግሊም ወረደ፤ በዮርዳኖስም ሊሸኘው ከንጉሡ ጋር ዮርዳኖስን ተሻገረ። 32ቤርዜሊም እጅግ ያረጀ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነበረ፤ እጅግም ትልቅ ሰው ነበረና ንጉሡ በመናሄም ሳለ ይቀልበው ነበር። 33ንጉሡም ቤርዜሊን፥ “አንተ ከእኔ ጋር ዮርዳኖስን ትሻገራለህ፤ በኢየሩሳሌምም ያረጀ ሰውነትህን ከእኔ ጋር እጦረዋለሁ” አለው። 34ቤርዜሊም ንጉሡን አለው፥ “ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እወጣ ዘንድ ከሕይወቴ ዘመን ምን ያህል ቀረኝ? 35ዛሬ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ፥ መልካሙንና ክፉውን መለየት እችላለሁን? እኔ ባሪያህ የምበላውንና የምጠጣውን ጣዕሙን መለየት እችላለሁን? የወንዱንና የሴቲቱን ዘፈን ድምፅ መስማትስ እችላለሁን? እኔ ባሪያህ በጌታዬ በንጉሡ ላይ ለምን እከብድብሃለሁ? 36እኔ ባሪያህ ዮርዳኖስን ተሻግሬ ከንጉሡ ጋር ጥቂት ልሄድ ነበር፤ ንጉሡ እንዲህ ያለ ወረታ ለምን ይመልስልኛል? 37እኔ ባሪያህ ተመልሼ በከተማዬ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ እባክህ! ልሙት፤ ነገር ግን ባሪያህ ከመዓም ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይሻገር፤ በዐይኖችህ ፊት ደስ የሚያሰኝህንም ለእርሱ አድርግ።” 38ንጉሡም፥ “ከመዓም ከእኔ ጋር ይሻገር፤ በፊቴ ደስ የሚያሰኘኝንም አደርግለታለሁ፤ አንተም ከእኔ የምትሻውን ነገር ሁሉ አደርግልሃለሁ” አለው። 39ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ንጉሡም ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ንጉሡም ቤርዜሊን አቅፎ ሳመው፤ መረቀውም፤ ወደ ስፍራውም ተመለሰ።
40ንጉሡም ወደ ጌልገላ ተሻገረ፤ ከመዓምም ከእርሱ ጋር ተሻገረ፤ የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ፥ ደግሞም የእስራኤል ሕዝብ እኩሌታ ከንጉሡ ጋር ተሻገሩ። 41እነሆም፥ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ መጡ፤ ንጉሡንም፥ “ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች ለምን ሰረቁህ? ንጉሡንም ቤተ ሰቡንም ዮርዳኖስን አሻገሩ። የዳዊትም ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ነበሩ” አሉት። 42የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ለእስራኤል ሰዎች መልሰው፥ “ንጉሡ ለእኛ ቅርባችን ነው፤ ስለምን በዚህ ነገር ትቈጣላችሁ? በውኑ ከንጉሡ አንዳች በልተናልን? ወይስ እርሱ በረከት ሰጥቶናልን? ወይስ ጭፍራ አድርጎ ሾመንን?” አሉ። 43የእስራኤልም ሰዎች ለይሁዳ ሰዎች መልሰው፥ “በንጉሡ ዘንድ ለእኛ ዐሥር ክፍል አለን፤ ከእናንተም እኛ እንቀድማለን፤ እኛም በኵር ነን፤ ለዳዊትም ከእናንተ እኛ እንቀርባለን፤ ስለምን ናቃችሁን? ንጉሡንስ እንመልሰው ዘንድ ከእናንተ የእኛ ቃል አይቀድምምን?” አሏቸው። የይሁዳም ሰዎች ቃል ከእስራኤል ሰዎች ቃል ይልቅ ጠነከረ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 19: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ