መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 18
18
አቤሴሎም እንደ ሞተ
1ዳዊትም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፤ የሻለቆችንና የመቶ አለቆችንም በላያቸው ሾመ። 2ዳዊትም ሕዝቡን ከኢዮአብ እጅ በታች ሢሶውን፥ ከኢዮአብም ወንድም ከሶርህያ ልጅ ከአቢሳ እጅ በታች ሢሶውን፥ ከጌት ሰውም ከኤቲ እጅ በታች ሢሶውን ላከ። ዳዊትም ሕዝቡን፥ “እኔ ደግሞ ከእናንተ ጋር እወጣለሁ” አላቸው። 3እነርሱ ግን “አንተ ከእኛ ከሁላችን ይልቅ እንደ ዐሥር ሽህ ሠራዊት ስለሆንህ ብንሸሽ ልባቸው አይከተለንምና፥ እኩሌታችንም ብንሞት ልባቸው አይከተለንምና አትውጣ፤ አሁንም መርዳትን ትረዳን ዘንድ በከተማ ብትኖርልን ይሻለናል” አሉት። 4ንጉሡም፥ “በፊታችሁ መልካም የሚመስላችሁን አደርጋለሁ” አላቸው። ንጉሡም በበሩ አጠገብ ቆመ፤ ሕዝቡም ሁሉ መቶ በመቶ፥ ሺህ በሺህ እየሆኑ ወጡ። 5ንጉሡም ኢዮአብንና አቢሳን ኤቲንም፥ “ለብላቴናው ለአቤሴሎም ስለ እኔ ራሩለት” ብሎ አዘዛቸው። ንጉሡም ስለ አቤሴሎም አለቆቹን ሁሉ ሲያዝዝ ሕዝቡ ሁሉ ሰሙ።
6ሕዝቡም ሁሉ በእስራኤል ላይ ወደ በረሓ ወጡ፤ በኤፍሬምም በረሓ ተዋጓቸው። 7በዚያም የእስራኤል ሕዝብ በዳዊት አገልጋዮች ፊት ወደቁ፤ በዚያም ቀን ታላቅ ውጊያ በዚያ ሆነ፤ ሃያ ሺህ ሰዎችም ሞቱ። 8ከዚያም ጦሩ በሀገሩ ሁሉ ፊት ተበተነ፤ በዚያም ቀን በሰይፍ ከተገደሉት ሕዝብ ይልቅ በበረሓ የሞቱ ይበዛሉ።
9አቤሴሎምም ከዳዊት አገልጋዮች ጋር ተገናኘ፤ አቤሴሎምም በበቅሎ ተቀምጦ ነበር፤ በቅሎውም ብዙ ቅርንጫፍ ባለው በታላቅ ዛፍ በታች ገባ፤ ራሱም በዛፉ ተያዘ፤ በሰማይና በምድርም መካከል ተንጠለጠለ፤ ተቀምጦበትም የነበረው በቅሎ በበታቹ አለፈ። 10አንድ ሰውም አይቶ፥ “እነሆ፥ አቤሴሎም በዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁ” ብሎ ለኢዮአብ ነገረው። 11ኢዮአብም ለነገረው ሰው፥ “እነሆ፥ ካየኸው ለምን በምድር ላይ አልገደልኸውም? ዐሥር ብርና አንድ ድግ እሰጥህ ነበር” አለው። 12ሰውየውም ኢዮአብን፥ “ንጉሡ አንተንና አቢሳን፥ ኤቲንም፦ ብላቴናውን አቤሴሎምን ጠብቁ ብሎ ሲያዝ እኛ በጆሮአችን ሰምተናልና ሺህ ሰቅል ብር በእጄ ላይ ብትመዝን እጄን በንጉሡ ልጅ ላይ አልዘረጋም ነበር። 13እኔም በሰውነቱ ላይ ክፉ ነገር ባደርግ ነገሩ በንጉሡ ዘንድ ባልተሰወረም ነበር፤ አንተም በተነሣህብኝ ነበር” አለው። 14ኢዮአብም፥ “እኔ ከአንተ ጋር እንዲህ እዘገይ ዘንድ አልችልም” ብሎ ሦስት ጦሮች በእጁ ወሰደ፤ አቤሴሎምም ገና በዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ሕያው ሳለ በልቡ ላይ ተከላቸው። 15ዐሥሩም የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች ከበቡት፤ አቤሴሎምንም መትተው ገደሉት።
16ኢዮአብም ሕዝቡን ስለ ራራላቸው መለከት አስነፋ፤ ሕዝቡም እስራኤልን ተከትለው እንዳያሳድዱአቸው መለሳቸው። 17አቤሴሎምንም ወስዶ በበረሓ ባለ በታላቅ ገደል ውስጥ ጣለው፤ እጅግም ታላቅ የሆነ የድንጋይ ክምር ከመረበት፤ እስራኤልም ሁሉ ሸሽተው ወደ ድንኳናቸው ገቡ። 18አቤሴሎምም በሕይወቱ ሳለ፥ “ለስሜ መታሰቢያ የሚሆን ልጅ የለኝም” ብሎ ሐውልት ወስዶ በንጉሥ ሸለቆ ውስጥ ለራሱ በስሙ አቁሞ ነበር፤ ያችም ሐውልት እስከ ዛሬ ድረስ “እደ አቤሴሎም”#ዕብ. “የአቤሴሎም መታሰቢያ” ይላል። ተብላ ትጠራለች።
ዳዊት የአቤሴሎምን ሞት እንደ ሰማ
19የሳዶቅ ልጅ አኪማሖስ ግን፥ “እግዚአብሔር ከጠላቶቹ እጅ እንደ ፈረደለት ፈጥኜ ሄጄ ለንጉሥ የምሥራች ልንገርን?” አለ። 20ኢዮአብም፥ “አንተ በዚች ቀን የምሥራች የምትናገር ሰው አይደለህም፤ ወሬውን በሌላ ቀን ትናገራለህ፤ በዚች ቀን ግን የንጉሡ ልጅ እንደ ሞተ ወሬ አትናገርም” አለው። 21ኢዮአብም ኩሲን፥ “ሂድ፤ ያየኸውንም ሁሉ ለንጉሥ ንገር” አለው። ኩሲም ለኢዮአብ ሰግዶ ወጣ። 22ዳግመኛም የሳዶቅ ልጅ አኪማሖስ ኢዮአብን፥ “የሆነ ሆኖ ኩሲን ተከትዬ፥ እባክህ ልሩጥ” አለው። ኢዮአብም፥ “ልጄ ሆይ፥ ለምን ትሮጣለህ? ተመለስ፤ ብትሄድ ይች ወሬ ለጥቅም አትሆንህምና” አለ። 23እርሱም፥ “እኔ ብሮጥ ምን ይገድዳል?” አለ። እርሱም፥ “ሩጥ” አለው። አኪማሖስም በሰርጥ ጎዳና በኩል ሮጠ፤ ኩሲንም ቀደመው።
24ዳዊትም በሁለት በር መካከል ተቀምጦ ነበር፤ ዘበኛውም በቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደ በሩ ሰገነት ወጣ፤ ዐይኑንም አቅንቶ ብቻውን የሚሮጥ ሰው አየ። 25ዘበኛውም ለንጉሡ ሊነግረው ጮኸ። ንጉሡም፥ “ብቻውን እንደ ሆነ በአፉ ወሬ ይኖራል” አለ። እርሱም ፈጥኖ ቀረበ። 26ዘበኛውም ሌላ ሰው ሲሮጥ አየ፤ ዘበኛውም ለደጅ ጠባቂው ጮኾ፥ “እነሆ፥ ብቻውን የሚሮጥ ሌላ ሰው አየሁ” አለ። ንጉሡም፥ “እርሱ ደግሞ ወሬ ይዞ ይሆናል” አለ። 27ዘበኛውም፥ “የፊተኛው ሩጫ እንደ ሳዶቅ ልጅ እንደ አኪማሖስ ሩጫ ይመስላል” አለ፤ “ንጉሡም፦ እርሱ መልካም ሰው ነው፤ መልካምም ወሬ ያመጣል” አለ።
28አኪማሖስም ጮኾ ንጉሡን፥ “ሰላም ለአንተ ይሁን!” አለው። በንጉሡም ፊት በምድር ላይ በግንባሩ ሰግዶ፥ “በንጉሡ በጌታዬ ላይ እጃቸውን ያነሡትን ሰዎች አሳልፎ የሰጠ አምላክህ እግዚአብሔር ይመስገን” አለ። 29ንጉሡም፥ “ብላቴናው አቤሴሎም ደኅና ነውን?” አለ። አኪማሖስም፥ “ኢዮአብ እኔን ባሪያህንና የንጉሡን ባሪያ በላከ ጊዜ ብዙ ሰዎችን#ዕብ. “ትልቅ ሽብር” ይላል። አይቻለሁ፤ ምን እንደ ሆነ ግን አላወቅሁም” ብሎ መለሰለት። 30ንጉሡም፥ “ፈቀቅ ብለህ ቁም” አለ፤ እርሱም ፈቀቅ ብሎ ቆመ።
31እነሆም፥ ኩሲ መጣ፤ ኩሲም፥ “እግዚአብሔር በላይህ የተነሡትን ሁሉ ዛሬ እንደ ተበቀለልህ ለጌታዬ ለንጉሡ ወሬ አምጥቻለሁ” አለ። 32ንጉሡም ኩሲን፥ “ብላቴናው አቤሴሎም ደኅና ነውን?” አለው። ኩሲም፥ “የጌታዬ የንጉሡ ጠላቶች፥ በክፉም የተነሡብህ ሁሉ እንደዚያ ብላቴና ይሁኑ” ብሎ መለሰለት። 33ንጉሡም እጅግ ደነገጠ፤ በበሩም ላይ ወዳለችው ሰገነት ወጥቶ አለቀሰ፤ ሲሄድም፥ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ፥ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ በአንተ ፋንታ እኔ እንድሞት ቤዛህም እንድሆን ማን ባደረገኝ፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ፥” ይል ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 18: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ