ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኀጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውሃ ካወረደ፥ ኀጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው፥ ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዐመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዐመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ፥ ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል። ደፋሮችና ኵሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፤ ዳሩ ግን መላእክት በኀይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ፥ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም። እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደ ተወለዱ አእምሮ እንደ ሌላቸው እንስሶች ሆነው፥ በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ፤ የዐመፃቸውን ደመወዝ ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኵሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፤ ምንዝር የሞላባቸው ኀጢአትንም የማይተዉ ዐይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው። ቅንን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ የባሶርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ እርሱ የዐመፃን ደመወዝ ወደደ፤ ነገር ግን ስለ መተላለፉ ተዘለፈ፤ ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብድነት አገደ። ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው እነዚህ ውሃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው። ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፤ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ። ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው “አርነት ትወጣላችሁ፤” እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና። በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። ዕውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤” ደግሞ “የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች፤” እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።
የጴጥሮስ መልእክት 2 2 ያንብቡ
ያዳምጡ የጴጥሮስ መልእክት 2 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የጴጥሮስ መልእክት 2 2:5-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች