2 ጴጥሮስ 2:5-22

2 ጴጥሮስ 2:5-22 NASV

የጽድቅ ሰባኪ የነበረውንም ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋራ አድኖ፣ ለቀድሞው ዓለም ሳይራራ በኀጢአተኞች ላይ የጥፋት ውሃ ካመጣ፣ ደግሞም ኀጢአት ለሚያደርጉ ሁሉ ምሳሌ እንዲሆኑ፣ የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ዐመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎ ከፈረደባቸው፣ ጻድቅ የሆነውንና በዐመፀኞች ሴሰኛ ድርጊት እየተሣቀቀ የኖረውን ሎጥን ካዳነ፣ ያ ጻድቅ ሰው በእነርሱ መካከል ሲኖር በሚያየውና በሚሰማው ነገር ነፍሱ ዕለት ዕለት በዐመፀኛ ድርጊታቸው ብትጨነቅም፣ ጌታ፣ በእውነት እያመለኩት የሚኖሩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸውና ዐመፀኞችን እየቀጣ ለፍርድ ቀን እንዴት ጠብቆ እንደሚያቈያቸው ያውቃል። በተለይም በርኩስ ምኞት የሥጋ ፍላጎታቸውን የሚከተሉትንና ሥልጣንን የሚንቁትን ለፍርድ ጠብቆ ያቈያቸዋል። እነዚህ ሰዎች ደፋሮችና እብሪተኞች ስለ ሆኑ ሰማያውያንን ፍጡራን ሲሳደቡ አይፈሩም፤ ነገር ግን መላእክት ከእነርሱ ይልቅ ብርቱና ኀያል ሆነው ሳሉ፣ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብ ቃል አይሰነዝሩም። እነዚህ ሰዎች ግን ምንም በማያውቁት ነገር እየገቡ ይሳደባሉ፤ እነርሱም ለመያዝና ለመገደል እንደ ተወለዱ፣ በደመ ነፍስ እንደሚመሩና አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት የሚጠፉ ናቸው። ለዐመፃቸው የሚገባውን ዋጋ ይቀበላሉ። በጠራራ ፀሓይ ሲፈነጥዙ እንደ ደስታ ይቈጥሩታል፤ በግብዣ ላይ ሳሉ ነውረኞችና ርኩሶች ሆነው ከእናንተም ጋራ በፍቅር ግብዣ ላይ ዐብረው ይበላሉ። ዐይናቸው ቅንዝር የተሞላ በመሆኑ ኀጢአትን ከመሥራት አይቈጠቡም፤ ጽኑ ያልሆኑትን ነፍሳት ያስታሉ፤ ሥሥትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው! ቀናውን መንገድ ትተው፣ የዐመፅን ደመወዝ የወደደውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከትለው ስተዋል፤ እርሱ ግን ስለ መተላለፉ ተገሥጿል፤ መናገር የማይችል አህያ በሰው ቋንቋ ተናግሮ የነቢዩን እብደት ገታ። እነዚህ ሰዎች የደረቁ ምንጮችና በዐውሎ ነፋስ የሚነዱ ደመናዎች ናቸው፤ የሚጠብቃቸውም ድቅድቅ ጨለማ ነው፤ ከንቱ ቃል እየደረደሩ በስሕተት ከሚኖሩት መካከል አምልጠው የመጡትን ሰዎች በሴሰኛ ሥጋዊ ምኞት በማባበል ያታልላሉና። እነርሱ ራሳቸው የጥፋት ባሮች ሆነው ሳሉ፣ ሌሎችን ነጻ ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል፤ ሰው ለተገዛለት ለዚያ ነገር ባሪያ ነውና። ጌታችንንና አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ በኋላ እንደ ገና ተጠላልፈው ቢሸነፉ፣ ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የከፋ ይሆንባቸዋል። የጽድቅን መንገድ ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ኋላ ከሚመለሱ፣ ቀድሞውኑ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት ይሻላቸው ነበር። “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል” እንዲሁም “ዐሣማ ቢታጠብም ተመልሶ በጭቃ ላይ ይንከባለላል” የሚለው ምሳሌ እውን ይሆንባቸዋል።