መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 9
9
ኢዩ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሠ
1ነቢዩም ኤልሳዕ ከነቢያት ልጆች አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለው፥ “ወገብህን ታጥቀህ ይህን የዘይት ቀንድ በእጅህ ያዝ፤ ወደ ሬማት ዘገለዓድም ሂድ። 2በዚያም በደረስህ ጊዜ የናሜሲን ልጅ የኢዮሣፍጥን ልጅ ኢዩን ታገኘዋለህ፤ ገብተህም ከወንድሞቹ መካከል አስነሣው፤ ወደ ጓዳም አግባው። 3የዘይቱንም ቀንድ ይዘህ በራሱ ላይ አፍስሰውና፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ በለው፤ ከዚህም በኋላ በሩን ከፍተህ ሽሽ፥ አትዘግይም።” 4እንዲሁም ጐልማሳው ነቢይ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሄደ። 5በገባም ጊዜ፥ እነሆ፥ የሠራዊት አለቆች ተቀምጠው አገኘ፤ እርሱም፥ “አለቃ ሆይ፥ የምናገረው መልእክት አለኝ” አለ። ኢዩም፥ “ከማንኛችን ጋር ነው?” አለ። እርሱም፥ “አለቃ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ነው” አለ። 6ተነሥቶም ወደ ቤቱ ገባ፥ ዘይቱንም በራሱ ላይ አፍስሶ እንዲህ አለው፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ። 7የባሪያዎቼን የነቢያትን ደም፥ የእግዚአብሔርንም ባሪያዎች ሁሉ ደም ከኤልዛቤል እጅና ከአክዓብ ቤት ሁሉ እጅ እበቀል ዘንድ የጌታህን የአክዓብን ቤት ታጠፋለህ። 8የአክዓብን ቤት ሁሉ ታጠፋለህ፤ በእስራኤልም ዘንድ አጥር ተጠግቶ እስከሚሸን የቀረበውን ሁሉና ከእነርሱ የቀረውን ሁሉ ታጠፋለህ። 9የአክዓብንም ቤት እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፥ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ። 10ኤልዛቤልንም በኢይዝራኤል እርሻ ውሾች ይበሉአታል፥ የሚቀብራትም አታገኝም።” በሩንም ከፍቶ ሸሸ።
11ኢዩም ወደ ጌታው ብላቴኖች ወጣ፤ እነርሱም፥ “ደኅና ነውን? ይህ እብድ ለምን ወደ አንተ መጣ?” አሉት። እርሱም፥ “ሰውዬው ፌዝ እንደሚናገር አታውቁምን?” አላቸው። 12እነርሱም፥ “ዋሸኸን፤ ነገር ግን ንገረን” አሉት፤ ኢዩም፦ ለጌታው ልጆች፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ ብሎ እንዲህና እንዲህ ነገረኝ” አላቸው። 13በሰሙም ጊዜ ሁሉም ፈጥነው ልብሳቸውን ወሰዱ፤ በሰገነቱ መውጫ እርከን ላይም ከእግሩ በታች አነጠፉት፥ መለከትም እየነፉ፥ “ኢዩ ነግሦአል” አሉ።
14እንዲሁም የናሜሲ ልጅ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዩ ኢዮራምን ከዳው። ኢዮራምና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል የተነሣ ሬማት ዘገለዓድን ይጠብቁ ነበር። 15ንጉሡ ኢዮራም ግን ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን ያቈሰሉትን ቍስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመልሶ ነበር። ኢዩም ከእርሱ ጋር ለነበሩት እንዲህ አላቸው፥ “ከእኔ ጋር ሰውነታችሁን ለሞት መስጠት ትችላላችሁን? እንግዲህ ማንም የሚያመልጣችሁ፥ ከከተማችሁም የሚወጣ እንዳይኖርና በኢይዝራኤል እንዳያወራ ተጠንቀቁ።” 16የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራምም ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ አረማውያን የሶርያ ሰዎች በሬማት ያቈሰሉትን ቍስል በኢይዝራኤል ይታከም ስለ ነበረ ኢዩ በሰረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ። ጠንካራና ኀይለኛ ሰው ነበርና፤ የይሁዳም ንጉሥ አካዝያስ ኢዮራምን ለማየት ወርዶ ነበር።
17ሰላይም ያያቸው ዘንድ በኢይዝራኤል ግንብ ላይ ቆመ፤ ሲመጡም የእነኢዩን አቧራ አየ። “እነሆም፥ አቧራ አያለሁ” አለ። ኢዮራምም፥ “ይገናኛቸው ዘንድ አንድ ፈረሰኛ ይሂድ፤ እርሱም፦ ሰላም ነውን? ይበላቸው” አለ። 18ፈረሰኛውም ሊቀበላቸው ሄዶ፥ “ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ሰላም ነውን?” አላቸው። ኢዩም፥ “አንተ ከሰላም ጋር ምን አለህ? ወደ ኋላዬ ተመልሰህ ተከተለኝ” አለ። ሰላዩም፥ “መልእክተኛው ደረሰባቸው፥ ነገር ግን አልተመለሰም” ብሎ ነገረው። 19ሁለተኛውንም ፈረሰኛ ሰደደ፤ ወደ እነርሱም ደርሶ ንጉሡ እንዲህ ይላል፥ “ሰላም ነውን?” አላቸው። ኢዩም፥ “አንተ ከሰላም ጋር ምን አለህ? ወደ ኋላዬ ተመልሰህ ተከተለኝ” አለ። 20ሰላዩም፥ “መልእክተኛው ደረሰባቸው፥ ነገር ግን አልተመለሰም፤ የሚመራው ግን እንደ ናሜሲ ልጅ እንደ ኢዩ ይመራል በችኮላ ይሄዳልና” ብሎ ነገረው።
21ኢዮራምም፥ “ሰረገላ አዘጋጁ” አለ፤ ሰረገላውንም አዘጋጁለት። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮራምና የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ሁለቱም በሰረገሎቻቸው ተቀምጠው ወጡ፤ ኢዩንም ሊገናኙት ሄዱ፤ በኢይዝራኤላዊውም በናቡቴ እርሻ ውስጥ አገኙት። 22ኢዮራምም ኢዩን ባየ ጊዜ “ኢዩ ሆይ፥ ሰላም ነውን?” አለ። እርሱም፥ “የእናትህ የኤልዛቤል ግልሙትናዋና መተቷ ሲበዛ ምን ሰላም አለ?” ብሎ መለሰ። 23ኢዮራምም መልሶ ነዳና ሸሸ፤ አካዝያስንም፥ “አካዝያስ ሆይ፥ ዐመፅ ነው” አለው። 24ኢዩም በእጁ ቀስቱን ለጠጠ፤ ኢዮራምንም በጫንቃው መካከል ወጋው ፤ ፍላጻውም በልቡ አለፈ፤ ወደ ሰረገላውም ውስጥ በጕልበቱ ላይ ወደቀ። 25ኢዩም ጋሻጃግሬውን ቢድቃርን እንዲህ አለው፥ “አንሥተህ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ እርሻ ጣለው፤ አንተና እኔ ጎን ለጎን በፈረስ ተቀምጠን አባቱን አክዓብን በተከተልን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ይህን መከራ እንደ ተናገረበት እኔ አስባለሁና አንተም ታውቃለህና፤ 26በእውነት የናቡቴንና የልጆቹን ደም ትናንትና አይቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚህም እርሻ እበቀለዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ቃል ወስደህ በእርሻው ውስጥ ጣለው።”
27የይሁዳም ንጉሥ አካዝያስ ያን ባየ ጊዜ በአትክልት ቤት መንገድ ሸሸ። ኢዩም፥ “እርሱንም ደግሞ አልተወውም” ብሎ ተከተለው። በይብላሄምም አቅራቢያ ባለችው በጋይ አቀበት በሰረገላው ላይ ወጋው። ወደ መጊዶም ሸሸ፥ በዚያም ሞተ። 28ብላቴኖቹም በሰረገላው ጭነው ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፥ በዳዊትም ከተማ በመቃብሩ ቀበሩት።
29በአክዓብም ልጅ በኢዮራም በዐሥራ አንደኛው ዓመት አካዝያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ።
የኤልዛቤል መገደል
30ኢዩም ወደ ኢይዝራኤል ሄደ፤ ኤልዛቤልም ይህን በሰማች ጊዜ ዐይንዋን ተኳለች፤ ራስዋንም አስጌጠች፤ በመስኮትም ዘልቃ ትመለከት ነበር። 31ኢዩም ወደ ከተማ በገባ ጊዜ፥ “ጌታውን የገደለ ዘምሪ ሰላም ነውን?” አለችው። 32ፊቱንም አቅንቶ በመስኮቱ አያት። “አንቺ ማን ነሽ? ወደዚህ ወደ እኔ ውረጂ” አላት። ከዚህም በኋላ ሁለት ጃንደረቦች ወደ እርሱ ተመለከቱ። 33እርሱም፥ “ወደ ታች ወርውሩአት” አላቸው፤ ወረወሩአትም፥ ደምዋም በግንቡና በፈረሶች መግሪያ ላይ#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “በግንቡና በፈረሶቹ ላይ” ይላል። ተረጨ፥ ረገጡአትም። 34ኢዩም ገብቶ በላ፤ ጠጣም፥ ከዝያም በኋላ፥ “ሂዱ፥ ይህችን የተረገመች እዩአት፤ የንጉሥ ልጅ ናትና ቅበሩአት” አለ። 35ሊቀብሩአትም በሄዱ ጊዜ ከአናቷና ከእግርዋ ተረከዝ ከመዳፍዋም በቀር ምንም አላገኙም። 36ተመልሰውም ለኢዩ ነገሩት፤ እርሱም፥ “በባሪያው በቴስብያዊው ኤልያስ እጅ በኢይዝራኤል እርሻ የኤልዛቤልን ሥጋ ውሾች ይበላሉ፥ 37የኤልዛቤልም ሬሳ በኢይዝራኤል እርሻ መሬት ላይ እንደ ፍግ ይሆናልና ማንም፦ ይህች ኤልዛቤል ናት ይል ዘንድ አይችልም ብሎ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው” አለ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 9: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ