በእስራኤልም ንጉሥ በኢዮርብዓም በሃያ ሰባተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ልጅ ዓዛርያስ ነገሠ። ዓዛርያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የዐሥራ ስድስት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። ነገር ግን በኮረብቶች ላይ የነበሩትን መስገጃዎች አላስወገደም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ በነበሩት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። እግዚአብሔርም ንጉሡን በደዌ ዳሰሰው፤ እስከሚሞትበትም ቀን ለምጻም ሆነ፤ በተለየ ቤትም ይቀመጥ ነበር፤ የንጉሡም ልጅ ኢዮአታም በንጉሡ ቤት ላይ ሠልጥኖ ለሀገሩ ሕዝብ ይፈርድ ነበር። የቀረውም የዓዛርያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ዓዛርያስም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። በይሁዳም ንጉሥ በዓዛርያስ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ስድስት ወር ነገሠ። አባቶቹም እንዳደረጉት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልንም ካሳታቸው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአት አልራቀም። የኢያቢስም ልጅ ሴሎም፤ ሌሎችም ከዱት፤ በይብልዓም መትተው ገደሉት፤ በእርሱም ፋንታ ሴሎም ነገሠ። የቀረውም የዘካርያስ ነገር፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ለኢዩ፥ “ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ” ተብሎ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነበረ፤ እንዲሁም ሆነ። በይሁዳም ንጉሥ በዓዛርያስ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የኢያቢስ ልጅ ሴሎም ነገሠ፤ በሰማርያም አንድ ወር ነገሠ። የጋዲም ልጅ ምናሔም ከቴርሳላቅ ወጥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በሰማርያም የኢያቢስን ልጅ ሴሎምን መታ፤ ገደለውም፤ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። የቀረውም የሴሎም ነገር፥ የተማማለውም ዐመፅ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሓፍ የተጻፈ አይደለምን? በዚያ ጊዜም ምናሔም ቴርሳን፥ በእርስዋም ያሉትን ሁሉ፥ ዳርቻዋንም መታ፤ ይከፍቱለትም ዘንድ አልወደዱምና መታት፤ በእርስዋም የነበሩትን እርጉዞች ሁሉ ሰነጠቃቸው። በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ላይ በሰማርያ ዐሥር ዓመት ነገሠ። በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገርን አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአትም አልራቀም። በዘመኑም የአሶር ንጉሥ ፎሐ በምድሪቱ ላይ ወጣ፤ ምናሔምም የፎሐ እጅ ከእርሱ ጋር እንዲሆን አንድ ሺህ መክሊት ብር ሰጠው። ምናሔምም ብሩን ለአሶር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ በእስራኤል ባለጠጎች ሁሉ ላይ በእያንዳንዱ ላይ አምሳ ሰቅል ብር አስገብሮ አወጣ። የአሶርም ንጉሥ ተመለሰ፤ በሀገሪቱም አልተቀመጠም። የቀረውም የምናሔም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ምናሔምም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ፤ ልጁም ፋቂስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። በይሁዳም ንጉሥ በዓዛርያስ በአምሳኛው ዓመት የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ ሁለት ዓመትም ነገሠ። በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአትም አልራቀም። የሠራዊቱም አለቃ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ከዳው፤ በሰማርያም በንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ከአርጎብና ከአርያ ጋር መታው፤ ከእርሱም ጋር ከገለዓዳውያን አምሳ ሰዎች ነበሩ፤ ገደለውም፤ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። የቀረውም የፋቂስያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 15 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 15:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች