የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያ ሰባተኛው፣ ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ልጅ ዓዛርያስ ነገሠ። በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ዐምሳ ሁለት ዓመት ገዛ። እናቱ ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። እርሱም አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር። እግዚአብሔርም ንጉሡን ቀሠፈው፤ እስከሚሞትበትም ቀን ድረስ ለምጽ ነበረበት፤ በተለየ ቤትም ይኖር ነበር። በዚያ ጊዜ ቤተ መንግሥቱን በኀላፊነት የሚመራውና የአገሩንም ሕዝብ የሚያስተዳድረው የንጉሡ ልጅ ኢዮአታም ነበር። በዓዛርያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? ዓዛርያስ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ በአባቶቹ መቃብር አጠገብ ቀበሩት። ልጁ ኢዮአታምም በምትኩ ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት፣ የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በሰማርያ ከተማ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ስድስት ወርም ገዛ። አባቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም። የኢያቤስ ልጅ ሰሎም በዘካርያስ ላይ አሤረበት፤ በሕዝቡ ፊት አደጋ ጥሎ ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ። በዘካርያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቧል። በዚህም እግዚአብሔር ለኢዩ፣ “ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ” ሲል የተናገረው ቃል ተፈጸመ። የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የኢያቤስ ልጅ ሰሎም በእስራኤል ላይ ነገሠ። በሰማርያ ተቀምጦ አንድ ወር ገዛ። የጋዲ ልጅ ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ወደ ሰማርያ በመሄድ አደጋ ጥሎ የኢያቤስን ልጅ ሰሎምን ገደለው፤ ከዚያም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። በሰሎም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራና የጠነሰሰውም ሤራ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፏል። በዚያ ጊዜም ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ በቲፍሳና በከተማዪቱ ነዋሪዎች ላይ ሁሉ፣ በአካባቢዋም ጭምር አደጋ ጣለ፤ ይህን ያደረገውም የከተማዪቱን በሮች ለመክፈት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ነበር፤ ቲፍሳን መታት፤ የነፍሰጡሮችንም ሆድ ሁሉ ቀደደ። የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት፣ የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያ ተቀምጦም ዐሥር ዓመት ገዛ። በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ በዘመኑም ሁሉ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም። ከዚያም የአሦር ንጉሥ ፎሓ ምድሪቱን ወረረ፤ ምናሔም ርዳታውን ለማግኘትና በመንግሥቱ ላይ ያለውን ይዞታ ለማጽናት ሲል፣ አንድ ሺሕ መክሊት ብር ሰጠው። ምናሔም ገንዘቡ እንዲዋጣ ያደረገው ከእስራኤል ሲሆን፣ ይህንም ያደረገው ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ እያንዳንዱ ሀብታም ዐምሳ፣ ዐምሳ ሰቅል ብር እንዲያዋጣ በማስገደድ ነበር። ስለዚህ የአሦር ንጉሥ በዚያች አገር አልቈየም፤ ተመልሶ ሄደ። በምናሔም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? ምናሔም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ ፋቂስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ ዓዛርያስ በነገሠ በዐምሳኛው ዓመት፣ የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በሰማርያ ከተማ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። ፋቂስያስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም፣ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም። ከጦር አለቆቹ አንዱ የሆነው የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ አሤረበት፤ ዐምሳ የገለዓድ ሰዎች ይዞ በመሄድ፣ ሰማርያ ቤተ መንግሥት ባለው ምሽግ ፋቂስያስን ከአርጎብና ከአርያ ጋራ ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ። በፋቂስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፏል።
2 ነገሥት 15 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ነገሥት 15
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ነገሥት 15:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች