መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 11
11
የይሁዳ ንግሥት ጎቶልያ
(2ዜ.መ. 22፥10—23፥15)
1የአካዝያስም እናት ጎቶልያ ልጅዋ እንደ ሞተ ባየች ጊዜ ተነሥታ የመንግሥትን ዘር ሁሉ አጠፋች። 2የንጉሡ የኢዮራም ልጅ የአካዝያስ እኅት ኢዮሳቡሄም የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ከተገደሉት ከንጉሡ ልጆች መካከል ሰርቃ ወሰደችው፤ እርሱንና ሞግዚቱንም ወደ እልፍኝ ወሰደች፤ ከጎቶልያም ሸሸገችው፤ አልገደሉትምም። 3በእግዚአብሔርም ቤት ስድስት ዓመት ሸሸገችው። ጎቶልያም በሀገሩ ላይ ነገሠች።
4በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ ልኮ፥ በኮራውያንና በዘበኞች ላይ ያሉትን የመቶ አለቆች ወሰደ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት አገባቸው፤ ከእነርሱም ጋር የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን አደረገ፤ በእግዚአብሔርም ቤት አማላቸው፤ የንጉሡንም ልጅ አሳያቸው። 5እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፥ “እንዲህ አድርጉ፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ በበር ተቀምጣችሁ የንጉሡን ቤት ዘብ ጠብቁ፤ 6ሌላውም ከሦስት አንዱ እጅ በሰፊው መንገድ በበሩ በኩል ተቀመጡ፤ ሦስተኛውም እጅ ከዘበኞች ቤት በኋላ ባለው በር ሁኑ፤ ቤቱንም አጽንታችሁ ጠብቁ፤ 7ከእናንተም በሰንበት ቀን የምትወጡት ሁለቱ እጅ ንጉሥ ያለበትን የእግዚአብሔርን ቤት ጠብቁ። 8ንጉሡንም በዙሪያው ክበቡት፤ የጦር ዕቃችሁም በእጃችሁ ይሁን፤ በሰልፋችሁም መካከል የሚገባ ይገደል፤ ንጉሡም በወጣና በገባ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሁኑ።”
9መቶ አለቆችም ብልሁ ዮዳሄ ያዘዛቸውን ሁሉ አደረጉ፤ ከእነርሱም እያንዳንዱ በሰንበት ይገቡ የነበሩትን፥ በሰንበትም ይወጡ የነበሩትን ሰዎች ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ። 10ዮዳሄም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ሰይፍና ጦር ሁሉ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው። 11ዘበኞቹም ሁሉ እያንዳንዳቸው የጦር ዕቃቸውን በእጃቸው ይዘው በንጉሡ ዙሪያ ከቤቱ ቀኝ እስከ ቤቱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ ቆሙ። 12የንጉሡንም ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነበት፤ ምስክሩንም ሰጠው፤ ቀብቶም አነገሠው፥ “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ” እያሉ በእጃቸው አጨበጨቡ።
13ጎቶልያም ሲሮጡ የሕዝቡን ድምፅ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገባች። 14እነሆም፥ ንጉሡን እንደ ተለመደው በዓምዱ አጠገብ ቆሞ፥ ከንጉሡም ጋር መዘምራንና መለከተኞች ቆመው አየች፤ የሀገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ ብሎአቸው መለከት ይነፉ ነበር። ጎቶልያም ልብስዋን ቀድዳ፥ “ዐመፅ ነው፥ ዐመፅ ነው፥” ብላ ጮኸች። 15ካህኑም ዮዳሄ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን የመቶ አለቆች፥ “ወደ ሰልፉ መካከል አውጡአት፤ የሚከተላትንም በሰይፍ ግደሉት” ብሎ አዘዛቸው፤ ካህኑ፥ “በእግዚአብሔር ቤት አትገደል” ብሎአልና። 16እርስዋንም ይዘው በንጉሡ ቤት አጠገብ ወደ አለ ወደ ፈረሶች መግቢያ መንገድ ወሰዱአት፤ በዚያም ገደሉአት።
ካህኑ ዮዳሄ ያደረገው ለውጥ
(2ዜ.መ. 23፥16-21)
17ዮዳሄም የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔርና በንጉሡ፥ በሕዝቡም መካከል ቃል ኪዳን አደረገ፤ ደግሞም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን አደረገ። 18የሀገሩም ሕዝብ ሁሉ ወደ በዓል ቤት ሄደው ሰበሩት፤ መሠዊያዎቹንም አፈረሱ፤ ምስሎቹንም አደቀቁ፥ የበዓልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። ካህኑ ዮዳሄም ለእግዚአብሔር ቤት ጠባቂዎችን ሾመ። 19መቶ አለቆቹንና ኮራውያንን፥ ዘበኞችንና የሀገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰዳቸው፤ ንጉሡንም ከእግዚአብሔር ቤት አወጣው፤ በዘበኞችም በር መንገድ ወደ ንጉሡ ቤት አመጡት፤ በነገሥታቱም ዙፋን አስቀመጡት። 20የሀገሩም ሕዝብ ደስ አላቸው፤ ከተማዪቱም ፀጥ አለች። ጎቶልያንም በንጉሡ ቤት አጠገብ በሰይፍ ገደሉአት። 21ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 11: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ