መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 10
10
ሳሙኤል ሳኦልን ቀብቶ እንደ አነገሠው
1ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በራሱ ላይ አፈሰሰው፤ ሳመውም፤ እንዲህም አለው፥ “በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ትነግሥ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶሃል፤ የእግዚአብሔርንም ሕዝብ ትገዛለህ፤ በዙሪያውም ካሉ ጠላቶቻቸው እጅ ታድናቸዋለህ። እግዚአብሔርም በርስቱ ላይ ትነግሥ ዘንድ እንደ ቀባህ ምልክቱ ይህ ነው። 2ዛሬ ከእኔ በተለየህ ጊዜ በብንያም ግዛት በቤቴል አውራጃ በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች እየቸኰሉ ሲሄዱ ታገኛለህ፤ እነርሱም፦ ልትፈልጉአቸው ሂዳችሁ የነበራችሁላቸው አህዮች ተገኝተዋል፤ እነሆም፥ አባትህ ስለ አህዮቹ ማሰብ ትቶ፦ የልጄን ነገር እንዴት አደርጋለሁ? እያለ ስለ እናንተ ይጨነቃል ይሉሃል። 3ከዚያም ደግሞ አልፈህ፥ ወደ ትልቁ የታቦር ዛፍ ትደርሳለህ፤ በዚያም ሦስት ሰዎች፥ አንዱ ሦስት የፍየል ጠቦቶች ሲነዳ፥ ሁለተኛው ሦስት የዳቦ ስልቻ፥ ሦስተኛውም የወይን ጠጅ አቁማዳ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ታገኛለህ፤ 4ሰላምታም ይሰጡሃል፤ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዳቦዎችም ይሰጡሃል፤ ከእጃቸውም ትቀበላለህ። 5ከዚያም በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፤ በዚያም ፍልስጥኤማዊው ናሴብ አለ፤ ወደዚያም ወደ ከተማዪቱ በደረስህ ጊዜ በገናና ከበሮ፥ እምቢልታና መሰንቆ ይዘው ትንቢት እየተናገሩ ከኰረብታው መስገጃ የሚወርዱ የነቢያትን ጉባኤ ታገኛለህ። 6የእግዚአብሔርም መንፈስ በአንተ ይወርዳል፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ትናገራለህ፤ እንደ ሌላም ሰው ሆነህ ትለወጣለህ። 7እነዚህም ምልክቶች በደረሱህ ጊዜ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና እጅህ የምትችለውን ሁሉ አድርግ። 8በፊቴም ወደ ጌልገላ ትወርዳለህ፤ እኔም እነሆ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀርብ ዘንድ፥ የደኅንነትንም መሥዋዕት እሠዋ ዘንድ ወደ አንተ እወርዳለሁ፤ እኔ ወደ አንተ እስክመጣና የምታደርገውን እስከምነግርህ ድረስ ሰባት ቀን ትቈያለህ።”
9ከሳሙኤልም ዘንድ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ እግዚአብሔር ሌላ ልብ ለወጠለት፤ በዚያም ቀን እነዚህ ምልክቶች ሁሉ ደረሱለት። 10ወደዚያም ኮረብታ በደረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ የነቢያት ጉባኤ አገኙት፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ ወረደ፤ በመካከላቸውም ትንቢት ተናገረ። 11ቀድሞም የሚያውቁት ሁሉ በነቢያት መካከል ባዩት ጊዜ ሕዝቡ እርስ በርሳቸው፥ “በቂስ ልጅ ላይ የሆነው ምንድን ነው? በውኑ ሳኦል ከነቢያት ወገን ነውን?” ተባባሉ። 12ከዚያም ስፍራ ያለ አንድ ሰው፥ “አባቱስ ማን ነው?” ብሎ መለሰ። ስለዚህም “ሳኦል ደግሞ ከነቢያት ወገን ነውን?” የሚል ምሳሌ ሆነ። 13ትንቢት መናገሩንም በፈጸመ ጊዜ ወደ ኮረብታው ወጣ።
14ከቤተ ሰቡም አንዱ እርሱንና ብላቴናውን፥ “ወዴት ሄዳችሁ ኖሮአል?” አላቸው። እነርሱም፥ “አህዮችን ልንፈልግ ሄደን ነበር፤ ባጣናቸውም ጊዜ ወደ ሳሙኤል መጣን” አሉት። 15ያም ቤተ ሰብ፥ “ሳሙኤል ምን አለ? እባክህ! ንገረኝ” አለው፤ 16ሳኦልም ለቤተ ሰቡ፥ “አህዮች እንደ ተገኙ ገለጠልን” አለው፤ ነገር ግን የመንግሥትን ነገር አላወራለትም።
የሳኦል ንጉሥ መሆን በይፋ እንደ ተነገረ
17ሳሙኤልም ሕዝቡን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ወደ መሴፋ እንዲሄዱ አዘዛቸው። 18የእስራኤልንም ልጆች፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እስራኤልን ከግብፅ አወጣሁ፤ ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖንም እጅ፥ ከሚያስጨንቁአችሁም ነገሥታት ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ’ አላቸው። 19ዛሬ ግን ከመከራችሁና ከጭንቃችሁ ሁሉ ያዳናችሁን እግዚአብሔርን ንቃችሁ፦ ‘እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ንጉሥ አንግሥልን’ አላችሁት። አሁንም በየነገዳችሁና በየወገናችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቁሙ” አላቸው። 20ሳሙኤልም የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ አቀረበ፤ ዕጣውም በብንያም ወገን ላይ ወደቀ። 21የብንያምንም ነገድ በየወገናቸው አቀረበ፤ ዕጣውም በማጥር ወገን ላይ ወደቀ፤ የማጥርንም ወገን በየሰዉ አቀረበ፤ ዕጣውም በቂስ ልጅ በሳኦል ላይ ወደቀ፤ ፈለገውም፤ አላገኘውምም። 22ሳሙኤልም፦ ያ ሰው እዚህ ይመጣ እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም፥ “እነሆ፥ በዕቃ መካከል ተሸሽጎአል” ብሎ መለሰ። 23እርሱም ሮጦ ከዚያ አመጣው፤ እርሱም በሕዝቡ መካከል አቆመው፤ ከሕዝቡም ሁሉ ይልቅ ረዥም ነበረ፤ ሕዝቡም ከትከሻው በታች ሆኑ። 24ሳሙኤልም ለሕዝቡ ሁሉ፥ “ከሕዝቡ ሁሉ እርሱን የሚመስል እንደ ሌለ እግዚአብሔር የመረጠውን ታያላችሁን?” አላቸው፤ ሕዝቡም ሁሉ፥ “ንጉሥ ሕያው ይሁን” እያሉ እልልታ አደረጉ።
25ሳሙኤልም የንጉሡን ሥርዐት ነገራቸው፤ በመጽሐፍም ጻፈው፤ በእግዚአብሔርም ፊት አኖረው። ሳሙኤልም ሕዝቡን ሁሉ ወደ እየቤታቸው አሰናበታቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እየቤታቸው ሄዱ። 26ሳኦልም ወደ ቤቱ ወደ ገባዖን ሄደ፤ እግዚአብሔር ልባቸውን የነካው ኀያላንም ከሳኦል ጋር ሄዱ። 27ክፉዎች ሰዎች ግን፥ “ያድነን ዘንድ ይህ ሰው ማን ነው?” ብለው ናቁት፤ እጅ መንሻም አላመጡለትም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 10: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ