የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የጴ​ጥ​ሮስ መል​እ​ክት 1

1
ሰላምታ
1-2የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፥ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስም እንደሚቀደሱ፥ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡት በጳንጦስና በገላትያ በቀጰዶቅያም በእስያም በቢታንያም ለተበተኑ መጻተኞች፤ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
ስለ ሕያው ተስፋ
3-5ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኀይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል። 6-7በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፤ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል። 8-9እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ፥ የእምነታችሁን ፍፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ፥ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል።
10ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤ 11በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ፥ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ፥ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር። 12ለእነርሱም ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን ባወሩላችሁ ነገር እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው፤ ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ።
በቅድስና ለመኖር የቀረበ ጥሪ
13ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ። 14እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። 15-16ዳሩ ግን “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ፤” ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ። 17ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ። 18-19ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። 20-21ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፤ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።
22ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። 23ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ።
24“ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤
ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤
25የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል።”
በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}